ለወትሮውም ከጥይት ድምፅ ነፃ ሆኖ ያልከረመው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በይዘቱ ከፍ ያለ ጦርነት በቅርቡ የተደገሰለት ይመስላል፡፡ ቀይ ባህርን ዋነኛ መነሻው ያደረገ የሚመስለው ይህ አለመረጋጋት፣ ከሰሞኑን ደግሞ የእጅ አዙር ጦርነት /Proxy War/ የማካሄድ እቅድ ባላቸው እንደ ግብፅ ባሉ ሀገራት እንቅስቃሴ ውጥረቱ ከፍ ብሏል፡፡
በ 2050 ዓ.ም 1.32 ቢሊዮን ገደማ ሕዝቦች መኖሪያ ይሆናል ተብሎ የሚገመተው የቀይ ባህር ዙሪያ የመላው ዓለም የዓይን ማረፊያ መሆኑ ተደጋግሞ ተገልጧል። ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት የባህር በር የነበራት ኢትዮጵያም በታሪክ አጋጣሚ ባጣችው መተንፈሻ ምክንያት በአካባቢው የነበራት ተፅእኖ ተቀዛቅዞ ቆይቷል።
ይህን ተከትሎ የመጡ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችም ሀገሪቷን ብዙ ዋጋ እያስከፈሏት ነው። ከመረጋጋት በራቀው እና እንደ አልሸባብ ላሉ ሽብርተኛ ቡድኖች መነሃሪያ በሆነው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እንደመገኘቷ፣ ከባህር የሚቃጡ ስጋቶችን ለመከላከል ሆነ በየጊዜው እያደገ የሚሄደውን የሕዝብ ቁጥሯን ተሳቢ ያደረገ እድገት ለማስመዝገብ የባህር በር ያስፈልጋታል። ይህን ታሳቢ በማድረግም እንቅስቃሴዎችን ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡
ይህንን እንቅስቃሴ ወደ ፍሬ ለማብቃት መንግሥት በአካባቢው ለሚገኙ የወደብ ባለቤት ሀገራት ጥሪ አቅርቧል ፤ ጥሪውን ተከትሎም የሶማሌ ላንድ መንግሥት ምላሽ ሰጥቷል ። ምላሹን ተከትሎም የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል። በዚህም በአካባቢው ብሄራዊ ጥቅም አለን የሚሉ ሃይሎች አካባቢውን ወደ ግጭት ለመውሰድ ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ።
ስለ ቀይ ባህር እና ስለ ወደብ፣ ማውራት እንደ ነውር የሚታይባቸውን 27 ዓመታት ተሻግረን አሁን ላይ ፤ አጀንዳውን ሀገራዊ ከዛም ባለፈ ዓለም አቀፋዊ የማድረጉ እውነታ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቷል። ጥያቄው ከሕግ እና ከሞራል አኳያ ትክክል ስለመሆኑም በብዙዎች ዘንድ ግንዛቤ የተያዘበት ጉዳይ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ እውቅናም እያገኘ ነው።
ይህም ሆኖ ግን በአካባቢው ብሄራዊ ጥቅም አለኝ የምትለው ግብጽ ፤ ከጉዳዩ ባለቤቶች በላይ ለጉዳዩ ባለቤት በመሆን ፤ የወደብ ጥያቄውን የዓባይ ውሃ ቀጣይ አጀንዳ በማድረግ፤ አካባቢውን ለማመስ በተለመደው መንገድ መንቀሳቀስ ከጀመረች ውላ አድራለች ።
ጉዳዩን አስመልክቶ አልጀዚራ ባለፈው ወር የግብፅን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫን እማኝ በማድረግ ይዞት በወጣው ዘገባ ፤ ግብፅ ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ ለሶማሊያ መንግሥት የመጀመሪያ ዙር ወታደራዊ ድጋፏ ማድረጓን አስታውቋል ፤ ሁለተኛው ዙር የወታደራዊ ድጋፍ ደግሞ ወደ ሀገሪቱ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ መድረሱን አመልክቷል።
በተመሳሳይ ሮይተርስ የዜና ወኪል በበኩሉ ሁለት የወደብ ሠራተኞች እና ሁለት ወታደራዊ ባለሥልጣናት ነግረውኛል ብሎ እንደዘገበው፤ በሶማሊያ በርካታ መሣሪያዎች ከግብፅ የጦር መርከቦች ተራግፈው ፤ የመከላከያ ሚኒስቴር ህንፃ እና በአቅራቢያው ወዳሉ የጦር ካምፖች መወሰዳቸውን አስታውቋል ፡፡
ግብፅ ቀጣናውን ወዳልተገባ ቀውስ ለመክተት እየሄደች ያለችውን ርቀት የሚያሳየው ሌላኛው የሆርን ኦፍ አፍሪካ ዘገባ ፤ የግብፅ እና የሶማሊያ የነሀሴ ወር ስምምነት እስከ 10,000 / አስር ሺህ / የግብፅ ወታደሮችን በሶማሊያ ማስፈርን ያካተተ ነው ሲል ፅፏል፡፡
የሆርን ዘገባ ሲቀጥልም በሞቃዲሾ ከተማ የሚገኘው የግብፅ ኤምባሲ ማናቸውም የግብፅ ዜጎች ከሶማሊ ላንድ ባስቸኳይ እንዲወጡ እና ወደ አካባቢው ለመጓዝ ያሰቡም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማሳሰቡን ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም ያካተተው የኢንተርናሽናል ፖሊሲ ዳይጀስት ዘገባ በበኩሉ “ኢትዮጵያ ወረራን ለሚያስቡ ሁሉ በጠቅላይ ሚኒስትሯ በኩል ቆራጥ ማስጠንቀቂያ ሰጠች” ሲል አስነብቧል ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያን ለመውረር ያሰበ ማንኛውም ሃይል በቅድሚያ አስር ጊዜ ማሰብ አለበት፡፡” ብለው ተናግረዋል ሲል አስነብቧል፡፡
ዘገባው ቱርክ እና ሌሎች የቀጣናው ሀገራት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ለማደራደር ጥረት ላይ ናቸው ሲል፣ ጅቡቲ ወሳኙን የታጁራ ወደብ ለኢትዮጵያ በጨረታ ለመስጠት ሃሳብ ማቅረቧን በትንታኔው አካትቶ ነበር ፡፡
አሁን ላይ የአፍሪካ ቀንድን እና የቀይ ባህርን ጉዳይ ቆም ብሎ ላጤነው ፣ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ፤ ለቀጣናው ሀገራት አዲስ የግጭት ስጋት ይዞ የመጣ ነው። በተለይም ግብጽ በአካባቢው እያደረገች ያለው ያልተገባ ጣልቃ ገብነት አካባቢውን ወደ አለመረጋጋት ሊያመራው እንደሚችል በስፋት እየተነገረ ነው።
ችግሩን በአግባቡ የተረዱ የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት አካል የሆኑ ክልሎች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት እየሄዱበት ያለው የተሳሳተ መንገድ ለሶማሊያ ሕዝብ አስቸጋሪ ጊዜያትን ከማምጣት ባለፈ ትርጉም ያለው ጥቅም እንደማይኖረው እያሳሰቡ ነው። የተነጣል ርምጃዎችንም እንዲወስዱ እያስገደዳቸው ነው።
የሀገሪቱ ፕሬዚዳን የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት በመከላከያ ሠራዊቱ በኩል ለሶማሊያ ሕዝብ የከፈለውን መስዋእትነት በአደባባይ ለማሳነስ የሚያደርጉትን ጥረት በመቃወም ፤ ከመከላከያ ሃይሉ ጋር ያላቸውን አጋርነት በግልጽ እያሳዩ ፤የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት የክፉ ቀን ወዳጅ መሆኑም እያስታወቁ ነው ።
የሶማሊያ ሕዝብ በአክራሪ እና ጽንፈኛ ሃይሎች ሕይወቱ አደጋ ውስጥ በነበረበት ወቅት የግብፅ መንግሥት የት ነበር ? የግብፅ ወደ ሶማሊያ የማማተሯ እውነታ የዓባይ ወንዝን ጉዳይ ወደ ሶማሊያ ይዞ የመምጣት የጥፋት ስትራቴጂ ነው ፤ይህ ደግሞ የሶማሊያ ሕዝብ አጀንዳ አይደለም የሚሉ ድምጾችን ጎልተው እየተሰሙ ነው።
ዓለም አቀፉ ህብረተሰብም ቢሆን በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን የአክራሪ እና ጽንፈኛ ሃይሎች እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ኢትዮጵያን ያገለለ አካሄድ የማያዋጣ መሆኑን በመግለጽ፤ የሶማሊያ መንግሥት ሁኔታዎችን በስክነት እንዲመለከተው፤ ችግሮች በድርድር እንዲፈቱ እያመላከተ ነው።
የሶማሊያ መንግሥት ኢትዮጵያ የባህር በር በሰላማዊ መንገድ በድርድር ለማግኘት ያላትን የሕግ እና ሞራል መብት ተግባራዊ ለማድረግ እየሄደችበት ያለው መንገድ በአግባቡ ሊያስበው ይገባል ፤ጉዳዩ የማንን ም ጣልቃ ገብነት የማይፈልግ፤ ከሁሉም በላይ የሀገራቱን ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት መሠረት በማድረግ ሊፈታ የሚችል ነው። ለዚህ የሚያስፈልገው ካልተገባ ሆሆይታ ወጥቶ በስክነት እና በወዳጅነት መንፈስ ጉዳዩን ማጤን ነው ።
ዮናታን ጠለለው ብዙነህ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም