ከጃፓን የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የተረፉት የዘንድሮውን የኖቤል የሠላም ሸልማት አሸነፉ

በዓለም ላይ በአሰቃቂነቱ የሚጠቀሰው አሜሪካ በጃፓን የፈጸመችው የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የተረፉ ሰዎችን ያቀፈው ኒሆን ሂዳንክዮ የተሰኘው ድርጅት የዘንድሮው የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ ሆነ።

ከሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የቦምብ ጥቃት የተረፉት ሰዎች ስብስብ የሆነው ይህ ድርጅት በዓለም ላይ ያለውን የኒውክሌር ጦር መሣሪያን ለማስወገድ እያደረገ ላለው ጥረት ከኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ሽልማት ዕውቅና ተሰጥቶታል።

“ድርጅቱ በዓለም ላይ ፀረ-ኒውክሌር እንቅስቃሴ እንዲኖር ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል” ሲሉ የኖቤል ኮሚቴ ሰብሳቢ ጆርገን ዋትን ፍሬድነስ ተናግረዋል።

በአቶሚክ ቦምብ የደረሰውን እልቂት ምስክርነት በመስጠት የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች እንደገና ጥቅም ላይ መዋል እንደሌለበት ከፍተኛ ሥራ መሥራታቸው ተዘክሯል።

በአውሮፓውያኑ 1956 የተመሠረተው ይህ ድርጅት በኒውክሌር ጦር መሣሪያ ምክንያት የደረሱ አሰቃቂ እልቂቶችን እና ስቃይ ምስክርነትን እንዲሰጡ ከጥቃት የተረፉትን ወደተለያዩ ሀገራት በመላክ ይሠራል።

ስብስቡ ሥራቸውን የጀመሩት የሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ውድመት ከደረሰ ከአስር ዓመታት በኋላ ነው።

ቡድኑ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለኖቤል ሽልማት ታጭቶ የነበረ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2005 ከኖቤል ኮሚቴ ልዩ እውቅና እንደተሰጣቸው ድረ-ገጹ ያትታል።

በአውሮፓውያኑ 1945 አሜሪካ የዩራኒየም ቦምብ በሂሮሺማ ከተማ አዘነበች። ዓለም በአሰቃቂነቱ የሚያወሳው የጃፓኖቹ ሂሮሺማና ናጋሳኪ ከተሞች ላይ የአሜሪካ የአውቶሚክ ቦምቦች ዘንበውበታል፣ የሰው ልጅ እንደ ቅጠል ረግፈውበታል።

በእነዚህ የቦምብ ጥቃቶች ምን ያህል ሰዎች እንዳለቁ ትክክለኛ ቁጥር ባይኖርም ከሂሮሺማ 350 ሺህ ሕዝብ ውስጥ 140 ሺዎቹ ሞተዋል። በናጋሳኪም እንዲሁ 74 ሺዎች ተፈጅተዋል።

በአውቶሚክ ቦምቡ ጥቃቱ ምክንያት ጃፓን በ1937 እጅ ሰጥታለች። እንዲሁም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ክፍል የሆነውና በእስያ የነበረውን ጦርነት ማብቂያን ያበሰረ ነው ቢሉም አንዳንዶች በዚህ ሃሳብ አይስማሙም።

የቡድኑ አንደኛው ኃላፊ የሆኑት ቶሺዪኩ ሚማኪ ከሽልማቱ በኋላ ለጋዜጠኞች “በሕልሜም ቢሆን ይህንን አላስብም ነበር” ሲሉ መናገራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ባለፈው ዓመት በእስር ላይ የምትገኘው ኢራናዊቷ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ናርጅስ ሞሃማዲ የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ ነበረች።

ናርጅስ የሽልማቱ አሸናፊ የሆነችው በኢራን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጭቆና በመታገል እንዲሁም ሁሉም ዜጎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተከብሮ እና ነፃነት የሚያገኙበትን ዓለም ለመፍጠር ባደረገችውም ትግል እንደሆነም ኮሚቴው አስታውቆ ነበር።

ከሁለት ዓመት በፊት የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ የነበሩት ሜሞሪያል የተባለ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን፣ ዩክሬናዊ የሰብዓዊ ተሟጋች ማዕከል ‘ሴንተር ፎር ሊበርቲስ ‘ እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኘው የመብት ተሟጋች አሌስ ቢያሊያትስኪ ነበሩ።

ሩስያ በዩክሬን ላይ ወረራ ፈጽማ ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅት ሠላም እንዲሰፍን ላደረጉት ትግልም እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የኖቤል የሠላም ሽልማት ከተቋቋመበት ከአውሮፓውያኑ 1901 ጀምሮ 110 ግለሰቦች እና 30 ድርጅቶች አሸናፊ ሆነዋል።

ከዚህ ቀደም ፓኪስታናዊቷ የትምህርት ተሟጋች ማላላ ዩሳፋዚ እንዲሁም የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሽልማቱ አሸናፊ ሆነዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You