– የፓስፖርት የአገልግሎት ጊዜ ወደ አስር ዓመት ከፍ ይላል
– በሩብ ዓመቱ ከ367 ሺህ በላይ ፓስፖርት ተሰራጭቷል
አዲስ አበባ፡– ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ የኢ-ፓስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ። የፓስፖርት አገልግሎት የጊዜ ገደብም ወደ አስር ዓመት ከፍ እንደሚደረግ ተገልጿል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሠላማዊት ዳዊት ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ የኢ-ፓስፖርት አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።
አሁን ያለውን የፓስፖርት ቡክሌት ወደ ኢ-ፓስፖርት ለመቀየር ምርት መጀመሩን የገለጹት ወይዘሮ ሰላማዊት፣ በመጪው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ወር ኢ-ፓስፖርት መስጠት ይጀመራል ብለዋል።
ኢ-ፓስፖርት ሁሉም የተቋሙን ሥርዓት በዘመናዊ መልኩ የሚቀይር መሆኑን ጠቅሰው፣ የተቋሙን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ፣ የፓስፖርት ኅትመትን ለማቀላጠፍ የሚያስችል ማሻሻያ መሆኑን ገልጸዋል።
እድሜያቸው ከ25 ዓመት በላይ ለሆናቸው ዜጎች የፓስፖርት አገልግሎትን ጊዜ ከአምስት ዓመት ወደ አስር ዓመት ከፍ ሊደረግ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ከዚህ በኋላ የሚታተሙ ፓስፖርቶች የአገልግሎት ጊዜ ገደብ አስር ዓመት ይሆናል ብለዋል።
በ2017 ዓ.ም ሩብ ዓመት ውስጥ 478 ሺህ ቡክሌት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት መቻሉን ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ውስጥ ከ367 ሺህ በላይ ፓስፖርቶች ታትመው ለደንበኞች የተሰራጩ ሲሆን በመደበኛ 344 ሺህ 288፣ በአስቸኳይ 22 ሺህ 403፣ ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት 152፣ ሰርቪስ ፓስፖርት 298 መሆናቸውን አስረድተዋል።
ተቋሙ በኦንላይን (በይነ መረብ) የመቀበል አቅሙን በቀን ከሰባት ሺህ በላይ ማሳደጉን በመግለጽ፣ ለአስቸኳይ ፓስፖርት በቀን 600 ተገልጋዮችን የማስተናገድ አቅም መፍጠር መቻሉንም ተናግረዋል።
በሩብ ዓመቱ በቦሌ አየር ኬላ ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ መንገደኞች አገልግሎት መሰጠቱን ጠቅሰው፣ በዚህም 559 ሺህ 848 መንገደኞች ወደሀገሪቱ መግባታቸውንና 581
ሺህ 704 መንገደኞች ደግሞ ከሀገር መውጣታቸውን ገልጸዋል።
በየብስ ኬላ በኩል ለ237 ሺህ 872 መንገደኞችን አገልግሎት መስጠት ተችሏል ያሉት ዳይሬክተሯ፣ 106 ሺህ 003 ደንበኞች ወደሀገር የገቡ ሲሆን 131 ሺህ 869 ደንበኞች ከሀገር ወጥተዋል ብለዋል።
ተቋሙ በሦስት ወር ውስጥ 259 ሺህ 705 ቪዛዎችን መስጠት መቻሉን በመግለጽ፣ ይህም ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ እንግዶች ብዛት እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በሩብ ዓመቱ በሲቪል ምዝገባ 572 ሺህ 236 ኩነቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ውስጥ 572 ሺህ 114 ተገልጋዮች የምስክር ወረቀት እንዲወስዱ መደረጉንም ተናግረዋል።
በተቋሙ ላይ በተደጋጋሚ ሲነሱ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎች ሲሠሩ እንደነበር ጠቅሰው፣ የአገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቱ በተለይ ተቋማዊ ሪፎርም ማድረግ ከጀመረ በኋላ መጠነ ሰፊ ለውጦችን እያስመዘገበ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በተለይ በተቋሙ ላይ የሚነሳውን የሙስና ሠንሠለትና የተገልጋዮች እንግልት በመቅረፍ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም