የእናት እውነት

ከእኔና ከእማዬ ማን እንደሚበልጥ በቅርብ ነው ያወኩት፡፡ እማዬ እናቴ እንደሆነች የገባኝ ብዙ ዘግይቼ ነው፡፡ ታላቅ እህቴ ነበር የምትመስለኝ፡፡ ጡቷን እየጠባሁ አድጌ፣ በክንዷ ታቅፌ፣ በጀርባዋ ታዝዬም እናቴ አትመስለኝም ነበር፡፡ መንገድ ላይ ከእናቴ ጋር ያየን መንገደኛ እህትማማች እንደሆንን ከማሰብ ባለፈ ምንም ነገር አስቦ አያውቅም፡፡ በቁመት እኩል ነን..ከኔ የዘለለ..እንደ እናት ሩቅ የሆነ ሀሳብ ስታስብ አይቻት አላውቅም፡፡ ግን በኔ ውስጥ የትም ቦታ ነበረች፡፡ የትም ቦታ አገኛታለሁ፡፡ እሷ የሌለችበት ምንም ነገር አልነበረኝም፡፡ እኔም በእናቴ ሁሉም ቦታ አለሁ፡፡ በእኔ ሁሉም ቦታ ውስጥም አለች፡፡

ሩሃማ ነው ስሜ..ሩሃማ ያለችኝ እናቴ ናት፡፡ ምሕረት የሚገባት ሴት ማለት ነው፡፡ እናቴ እሷ በተራመደችበት የዘመን ሰርጥ ውስጥ እንዳልራመድ ስትል ነው ሩሃማ ያለችኝ፡፡ እሷ ያየችውን የዘመን ነውር፣ የጊዜ ኩነኔ እንዳላይ ስትል ነው ሩሃማ ያለችኝ፡፡ በእኔ ሩሃማነት ውስጥ የእሷ ያለፈ ታሪክ ሲታደስ አይቻለሁ፡፡ እኔ ፊት እናቴ ሁልጊዜም አዲስ ናት፡፡ በእኔ ኃጢያት..በእኔ መተላለፍ ልትቆሽሽ የማይገባሽ ነፍስ ነሽ ስትል ሩሃማ..ምሕረት የሚገባሽ ሴት አለችኝ፡፡ የአባት ዕዳ ለልጅ እንደሚባለው የእናቴ የዘመን ጸጸቶች እኔ ላይ አርፈው እንዳያሰቃዩኝ ምሕረት የሚገባት ሴት አለችኝ፡፡

እናቴ ታሪኳን ስትነግረኝ ምን ያክል ስህተት ብትሠራ ነው የዚህን ያክል ትላንትን የተጸየፈችው እያልኩ አስባለሁ፡፡ አንድ ቀን አስራ ሁለተኛ ዓመቴን ባከበርኩበት ሠልስት ድንገት በተኛሁበት ልብሴ በደም ረጥቦ አየሁት..እየጮሁኩ ወደ እናቴ ሮጥኩ፡፡ ትታደገኛለች ብዬ ሳስብ በእኔ መከራ ውስጥ እናቴ ስትስቅ አየኋት፡፡ በእናቴ አዲስ ባሕሪ ነፍሴ ተረበሸች..ሳላውቀው በእናቴ ላይ ተስፋ የቆረጥኩበት የመጀመሪያው ቀን ያን ቀን ነበር፡፡ እናቴን

ሳውቃት ተስፋዬ ነበረች፡፡ ለእግሮቼ የወርቅ ምንጣፍ፣ ለክንዶቼ ጌጣም አልቦ፣ ለሴትነቴ ዘውድና ማዕረግ ስትሆን አይቻት አውቃለሁ፡፡ በደም በጨቀየሁበት ያን ቀን ግን ሳቀችብኝ፡፡ ሳቋ ብዙ አልቆየም..ፊቴ ተንበረከከችና አቀፈችኝ፡፡ ለምን እና እንዴት እንደደማሁ ሳይገባኝና ሳይገባት ‹የኔ ቆንጆ አደግሽልኝ..› ብላ ጉንጮቼን በደስታ ሳመቻቸው፡፡ ሁሉም ነገር ግራ ገብቶኝ ነበር፡፡ ልብሴ ላይ ያለው ደም በየት በኩል እንዴት ሆኖ እንደመጣ ሳላውቅ የእናቴ በደስታ መፍነክነክ ጤንነቷን እንድጠራጠር አደረገኝ፡፡

ፊቷ ላይ አለቀስኩ..እናቴን ፈራኋት፡፡ ያቀፉኝን ክንዶቿን፣ የሳመኝን ከንፈሯን ተጠራጠርኩት፡፡ ለዘላለም ሲራራልኝ የነበረውን እናትነቷን ሰጋሁት፡፡ እቅፏ ውስጥ እያለፉ ልሸሻት ስታገላት ‹የኔ ቆንጆ..ምንም አልሆንሽም እሺ..ይሄ ተፈጥሮ ላንቺና ለእኔ የሰጠችን ፀጋችን ነው› ብላ ድጋሚ ሳመችኝ፡፡

አሁንም አልገባኝም..ስለምን እንደምታወራ አልገባኝም፡፡ ራሴን ከእቅፏ ለማውጣት ተናነኳት ወደ ደረቷ ስባ ይበልጥ እያቀፈችኝ ‹እኔ እያለሁ አንቺ ምንም አትሆኚም..እኔ እያለሁ የሚጎዳሽ ክንድ የለም፡፡ ሩሃማዬ ነሽ፡፡ ነፍስሽ መጽናኛዬ ናት› አለችኝ፡፡

እናቴ እንደዛ ቀን ግራ ገብታኝ አታውቅም፡፡ ምን እንደሆንኩ ትነግረኛለች ብዬ ስጠብቅ ምንም ባልመሰለው እናትነት እቅፏ ውስጥ አስቀረችኝ፡፡ በተንበረከከችበት ወደ ላይ አንጋጣ ዓይኖቼን ፈለገቻቸው፡፡ ዓይኖቼን ስታስተውላቸው ቆይታ እንባ አቀረረች፡፡ ለቅሶዋ አስፈራኝ..ከሳቋ መልስ መነፍረቋ የሆነ ነገር እንደሆንኩ እንዳስብ አደረገኝ፡፡ ለቅሶዋ አስለቅሶኝ ጉያዋ ውስጥ ነፈረኩ፡፡

‹የኔ ቆንጆ ደስታ እኮ ነው የሚያስለቅሰኝ፡፡ ስላደግሽልኝ..ሴት ስለሆንሽልኝ ደስ ብሎኝ እኮ ነው› አለችኝ እያለቀሰ በሚፈግ ፊት፡፡ ተረጋጋሁ..ምንም እንዳልተፈጠረ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ግን ልቤ እየፈራ ነበር፡፡ ልቤ ውስጥ ያለውን አንድ መዓት ጥያቄ ተረድታ ብትመልስልኝ ስል በማሰብ ተረጋጋሁ፡፡

‹ልብስሽን የነካሽ ደም የፀጋ ደም ነው..

ከማለቷ ‹ምንም አልሆንኩም? አልታመምኩም? ስል በፈራ ስሜት ጠየኳት፡፡

‹ምንምአልሆንሽም..የማደግሽ..የመሠልጠንሽ ምልክት ነው፡፡ ሴት ልጅ እንዲህ እንዳቺ ደም ሲደማት ለኃላፊነት፣ ለእናትነት እየተዘጋጀች ነው ማለት ነው፡፡ እናም አሁን አንቺ እናት ለመሆንና ኃላፊነት ለመሸከም ተዘጋጅተሻል ማለት ነው› አለችኝ፡፡

አስራ ሁለት አመቴን ባከበርኩበት ሰልስት በተኛሁበት ያስደነገጠኝ ደም የልዕልና ምልክት እንደሆነ እናቴ ስትነግረኝ..ስለደሜ ለጓደኞቼ ለመናገር ቸኮልኩ፡፡ ከአሁን አሁን ከእናቴ እቅፍ ውስጥ ወጥቼ ወደሚያንጃብቡብኝ ወንዶች በመሄድ በመሽኮርመም ሴት እንደሆንኩና ለእናትነት እንደተዘጋጀሁ ላበስራቸው ተጣደፍኩ፡፡ እናቴ ግን እንዲህ አለችኝ ‹አሁን ተጠንቅቀሽ የምትኖሪበት እድሜ ላይ ነሽ፡፡ ይሄ ደም የክብር ደም ነው፡፡ አለችኝ በደም ወደረጠበው ቀሚሴ እየጠቆመች፡፡

ከእናቴ አፍ አዲስ ነገር ሰማሁ፡፡ እንባዋን አድርቃ ሳቋን አምቃ ለሴትነቴ እንግዳ የሆነ ነገር ትነግረኝ ጀመር፡፡ ለራሴ አዲስ ሆኜ በእናቴ ፊት ራሴን አገኘሁት፡፡

‹ይሄ ደም የሴትነትሽ ጌጥ ነው፡፡ የውበት፣ የአፍላነት አሸንክታብ፡፡ በስሌት ከኖርሽ ወደነገ ያደርስሻል በስሜት ከኖርሽ ደግሞ ነገሽን ይቀማሻል፡፡ ይሄ ደም አንቺን ጠንካራና አስተዋይ የሚያደርግሽ እንጂ የትም ለማንም ራሽን የምትገልጪበት አይደለም፡፡ ይሄ ደም ለባልሽ መልካም ሚስት፣ ለልጆችሽ ጥሩ እናት የሚያደርግሽ የተፈጥሮ ቃል ኪዳንሽ ነው፡፡ ይሄ ደም ከስሜት አርቆ በስሌት ፍኖት ላይ ወደነገሽ፣ ወደምትናፍቂው ሕልምሽ የሚያስጠጋሽ እንጂ ጠልፎ የሚጥልሽ እንዳይሆን ራሽን ጠብቂ፡፡ አለችኝ፡፡

በእናቴ ምክር ነፍሴ በልቤ ውስጥ ገለሞተች፡፡ ሰንኮፌን እየጣልኩ እንደምትለኝ አይነት ሴት እየሆንኩ ራሴን አገኘሁት፡፡ እናቴ ነግራኝ የምሽረው እውነት የለኝም፡፡ በእኔ ውስጥ አለች የለ? በእሷ ውስጥም መኖር እፈልጋለሁ..ያላባራ የእናቴ አደራ ከአሳቤ አደናቀፈኝ፡፡ ወደ ምክሯ ሸፈትኩ፡፡

‹ከዚህ ደም በኋላ አንቺን ሽተው፣ ውበትሽንና ሴትነትሽን ተመኝተው በውሸት አፍ የክብር ቀሚስሽን ለመግለብ በዙሪያሽ የሚያንጃብቡ ወንዶች ብዙ ናቸው፡፡ እኔ አንቺን በአስራ አንድ ዓመቴ የወለድኩሽ ሕይወትን የሚያስተምረኝ መምህር አጠገቤ ስለሌለ ነው፡፡ በዛ የመጀመሪያውን ደሜን ባየሁበት ልጅነቴ ውስጥ ሕይወትን የሚያስተምረኝ ሰው ቢኖር ኖሮ ከሕልሜ ርቄ በምንምነት ውስጥ አልገኝም ነበር፡፡ አሁን አንቺም የምልሽን ስሚ..ከዚህ ደም ቀጥሎ ሌላ ሴትነት፣ ሌላ ክብር አለሽ እዛ ክብርሽ ላይ እስክትደርሺ የማንም ሳትሆኚ የራስሽና የሕልምሽ ብቻ በመሆን እንድትኖሪ አደራ እልሻለሁ፡፡ ያኔ ሩሃማዬ ትሆኛለሽ..ያኔ ያጣሁትን ክብሬን በአንቺ ውስጥ አየዋለሁ› ስትል ያልተሳመ ጉንጬን ሳመችኝ፡፡

በእናቴ መሳም ውስጥ ነፍሴ ያልተረዳችውን አንድ መዓት ጥበብ ሸመተች፡፡ ነፍሴ የተመኘችው እውነት ይሄ ነበር፡፡ ይሄ ደም የኃላፊነት ደም እንደሆነ ገባኝ..ከዛ ደም በኋላ እናቴ እንዳለችኝ ተጠንቅቄ መርገጥና ተጠንቅቄ መኖር ጀመርኩ፡፡

ከዛ ደም በኋላ ከእናቴ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተዋወኩ..

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም

Recommended For You