ማኅበራዊ ሚዲያና የአዕምሮ ጤና

የአዕምሮ ጤና ሰዎች ስለሚያስቡት፣ ስለሚሰማቸው እና በዚህም ስለሚያሳዩት ባህሪ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ የአእምሮ ጤና ሰዎች የሕይወት ውጣውረድን ተቋቁመው እንዲኖሩ፣ ችሎታቸውን እንዲገነዘቡ፣ እንዲማሩና እንዲሰሩ እንዲሁም ለማህበረሰባቸው አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የሚያስችል የአእምሮ ደህንነት ነው።

ይህ የአዕምሮ ጤና ሲቃወስ ደግሞ የግለሰቡን የየዕለት ተግባር፣ ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት እና የሰውነት ሁኔታ ላይም ተጽዕኖ እንዳለው ይገለጻል፡፡ ማህበራዊና የገቢ ሁኔታ፣ ጥሩ ያልሆኑ የልጅነት ልምዶች፣ አፈጣጠርና መሰረታዊ የጤና ሁኔታዎች የአንድን ሰው የአእምሮ ጤንነት ሊወስኑ እንደሚችሉም ነው የሚነገረው። የአእምሮ ሕመም ዓይነቶች ጭንቀት፣ የስሜት መለዋወጥ (መቃወስ) እና ስኪዞፍሬኒያ (ከእውነታው ዓለም መዛባት) ናቸው፡፡ ጭንቀት የተለመደ የአእምሮ ሕመም ነው ይባላል፡፡ ይህ የአዕምሮ ጭንቀት ያጋጠማቸው ሰዎች ከአንዳንድ ነገሮች ወይም ሁኔታዎች ጋር የተያያዘ ከፍተኛ ፍርሃት አለባቸው።

የጭንቀት ምልክቶች ከሚባሉት ውስጥ እረፍት ማጣት፣ ድካም፣ ትኩረት አለማድረግ፣ የጡንቻ ሕመምና የተቆራረጠ እንቅልፍ ይጠቀሳሉ፡፡ የስሜት መለዋወጥ (መቃወስ)፤ ከፍተኛ ደስታና ከፍተኛ ጭንቀት ሲፈራረቅ የሚስተዋል የአዕምሮ ሕመም ዓይነት ነው፡፡

በአዕምሮ ሕመም ተፅዕኖ በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰሩ ጥናቶች ያሳያሉ። ከዓለም የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ተያይዞ ዲጂታል ሚዲያው በአዕምሮ ጤና ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ ብዙዎች ያነሳሉ።

ዲጂታል ሚዲያው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት ያደገ፣ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ በቢሊዮን በሚቆጠሩ የዓለማችን ሰዎች ጥቅም ላይ የሚውል ነው። ይህ ማለት ደግሞ እራሱን የቻለ ማህበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና አዕምሮአዊ ከፍተኛ ጉዳት ይዞ የሚመጣ ነው።

አሁን አሁን የማህበራዊ ሚዲያ ሰፊ ቁጥር ላላቸው ታዳጊዎች የእለት ተእለት ሕይወታቸው አካል እየሆነ መጥቷል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያላቸው ግንዛቤ እና ጥገኝነት ከብዙ ጎልማሶች እጅግ የላቀ ከመሆኑ ባሻገር፣ ማህበራዊ ሚዲያዎችንም በከፍተኛ ፍጥነት እየተጠቀሙ ነው። ዓለም እጅግ ውስብስብና ዲጂታል እየሆነች በምትሄድበት እያንዳንዷ ቅጽበት የታዳጊዎችም ሕይወት እንደዚያ እየሆነ መሄዱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዘግይቶም ቢሆን የአእምሮ ጤና መታወክ ያስከትላል፡፡

እንደ ተመራማሪዎች ጥናት ከሆነ ማህበራዊ ሚዲያ በታዳጊዎች ዘንድ እንደሱስ የመሆን እድሉ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ተመራማሪዎች በጥናታችን መሰረት አንዳንድ የአእምሮ ክፍሎች ታዳጊዎች ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሚያገኟቸው “likes” ንቁ እንደሚሆኑና ይህ ደግሞ በመልሱ የማህበራዊ ሚዲያ ፍላጎታቸው እንዲጨምር እንደሚያደርጋቸው ደርሰንበታል ይላሉ፡፡

ታዳጊዎች በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሚለጥፏቸው የራሳቸው ፎቶዎች ላይ ብዙ (ላይኮችን) በሚመለከቱበት ጊዜ ከበርካታ የአእምሮ ክልሎቻቸው በተጨማሪ አበረታች የአንጎል አካል የሆነው ኒውክሊየስ አክመንስ ንቁ ይሆናል፡፡ ይህ የአንጎል አካባቢ የምንወዳቸውን ሰዎች ፎቶ ስናይ ወይም ገንዘብ ስናሸንፍ ምላሽ የሚሰጠው ተመሳሳይ ክልል ነው፡፡

በነገራችን ላይ ይህ የአእምሮ ክፍል በታዳጊነት ወቅት ይበልጥ ስሜታዊ መሆኑ ስለምን ታዳጊዎች በማህበራዊ ሚዲያ ሱስ እንደሚጠለፉ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ታዳጊዎች ማህበራዊ ግንኙነቶችን ለማስፋት እና ጠቃሚ የቴክኒክ ክህሎቶችን እንዲማሩ ለመርዳት ማህበራዊ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ጥርጥር የለውም፡፡ ጥያቄው ግን እነዚህ ማህበራዊ ሚዲያዎች በታዳጊዎች ጭንቅላት ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ ያሳድራሉ? የሚለው ነው፡፡

ታዳጊዎች ለአእምሮ መጋለጥ የሚዳረጉት ብዙ ጊዜአቸውን ኦንላይን ስለሚያሳልፉ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ኦንላይን የሚሆኑበትን ጊዜ መቆጣጠር ስለማይችሉ በዛ ያለ ጊዜ ኦንላይን ሆነው ባሳለፉ ጊዜ በዚህ በአእምሮ ጭንቀት የመጠቃት እድላቸው ሰፋ ይላል፡፡ ብዙ ጊዜን ኦንላይን ማሳለፍ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ለበርካታ የጤና እክሎች መዳረጉ አይቀሬ ነው፡፡

ጥናቶችን መሰረት በማድረግ ስንመለከት በዓለም አቀፍ ደረጃ አምስት ቢሊዮን የሚሆን ሕዝብ የዲጂታል ሚዲያ ተጠቃሚ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዜጋ የዲጂታል ሚዲያ ተጠቃሚ ነው። ከሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘው ደግሞ በዚህ የሚዲያ ተፅዕኖ ውስጥ ያለ ወጣት በመሆኑ እንደ ሀገር ጉዳቱ ቀላል እንዳልሆነ እሙን ነው።

ከጤና አንፃር ከ10 እስከ 19 ዓመት ያሉት ታዳጊ ሕፃናትና ወጣቶችን ስንመለከት ይህ የዕድሜ ክልል የአዕምሮ ዕድገታቸው የሚያድግበት ግዜ ነው፤ ወቅቱ ታዳጊዎች ነገሮችን የሚያዩበት የአዕምሮ ክፍላቸው የሚያድግበት ሰዓት ነው። ለአብነት ተለዋዋጭ ስሜቶች፣ ከሰው ጋር ያለ መግባባት፣ እያንዳንዱ ባህርያቸው የሚቀያየርበት ወቅት በመሆኑ ትልቅ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት የዕድገት ደረጃ እንደሆነ ይታመናል።

“የወጣትነት ዕድሜ በውስጣችን ያለውን የሚሰማንን ነገር ሁለት ጊዜ ሳናስብ የምናወጣበት ወቅት ነው” የሚሉ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች፤ በባህርይ የእኛነት ስሜት የሚሰማበት፣ ትንሽ ነገር ቶሎ የሚያበረታታበትና በዛው ልክ ጥቂት ነገር ቶሎ የሚያስከፋበት አደገኛ ዕድሜ በመሆኑ ይህንን ተረድቶ ማለፍ የሚያስፈልግ እንደሆነ ያነሳሉ።

የማህበራዊ ሚዲያ ከመጀመሪያው ሲመጣ የንግድ ሀሳብ ይዞ፣ ብዙ ሰዎች ይሳተፉበታል የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት የመጣ ነው። ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር በእጅ ስልካቸው እያቀረበ ገንዘብ ማግኘት ነው ዋና ዓላማው፡፡ ከዚህ አንፃር የሚዲያ አማራጩ ወጣቶችንና ሕፃናትን ዓላማ አድርጎ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ በአጠቃላይ የሚሰጠው ጥቅም እንዳለ ሆኖ የሚያመጣው ችግርም ከፍተኛ ነው።

አንድ ወጣት በማህበራዊ ሚዲያ ቀርቦ እያወራ ወይም ፎቶውን እያጋራ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ደግሞ ያለ ገደብ ማንኛውም ሰው ሊያየው የሚችለው በመሆኑ ተመልካቹ ያንን ሰው ሊያበረታታውም ወይም ሊጎዳው ይችላል፡፡ ሴት ከሆነች ሰውነትሽ አያምርም፣ መልክሽ ቀፋፊ ነው እያለ በቀላሉ ማንኛውም ሰው የክፋት አስተያየት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይህ ከፍተኛ መጨናነቅ፣ ድብርት፣ አለፍ ሲልም እራስን እስከማጥፋት የሚችል የሥነ አዕምሮ ምስቅልቅል ውስጥ የሚከት በመሆኑ ሁሌም ቆንጆ ሆኖ ለመታየት ከአቅም በላይ በሆኑ ነገሮች ላይ ግዜ ማጥፋት ይመጣል ይህም ሌላ የሥነልቦና ጉዳት ይዞ የሚመጣ ይሆናል።

የእኔን ልጥፍ (ፖስት) ብዙ ሰው አየልኝ ወይም ወደደው፣ ወይም ብዙ ሰው አልተመለከተውም የሚለው ነገር ወጣቶቹን በጣም የሚያስጨንቃቸውና ውድድር ውስጥ የሚከታቸው በመሆኑ የራሳቸው ማንነት ያልሆነውን ግን ሰዎች ሊወዱት ይችላሉ ብለው የሚያስቡትን ነገር ማሳየት ይጀምራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ድባቴ ውስጥ በመክተት እራሳቸውን እንዲጎዱ ሊያደርግ የሚችል የአዕምሮ ጤና ችግር ውስጥ የሚያስገባቸው ነው።

እንደ ዘርፉ ባለሙያዎች ገለፃ፤ ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከኮምፒውተር እና ስልካቸው ጋር በመሆኑ ምግባቸውን እንኳ ለመብላት የሚሆን ሰዓት ስለሌላቸው የአመጋገብ ስርዓት መዛባት ይከተላል። ይህንን ተከትሎ ለሚመጡ የአዕምሮ ጤና ችግሮች ተጋላጭ ይሆናሉ።

ለረዥም ሰዓት እንቅልፍ ሳያገኙ የሚቆዩ ወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው፤ አዕምሯችን በተፈጥሮ እንቅልፍ የሚተኛበት ሰዓት ጨለማ የሚሆንበት ወይም ብዙ ብርሃን በማይኖርበት ሰዓት እንደመሆኑ፤ ማህበራዊ ሚዲያው ደግሞ አዕምሯችን መተኛት ባለበት ሰዓት ላይ ጠብቀን እንዳንተኛ ስለሚያደርገን ሕይወታችን እንቅልፍ ማጣትን ተከትሎ ለሚመጡ የጭንቀት፣ የስሜት መራበሽ፣ የሀዘን ስሜቶች ወይም ሕመሞች ተጋላጭ ያደርገናል።

በተጨማሪም ወጣቶች ለብዙ ሰዓት በአንድ ቦታ ተቀምጠው ስለሚውሉ አለመንቀሳቀሳቸው በራሱ እርሱን ተከትለው ለሚመጡ እንደ የልብ ሕመም ላሉ በሽታዎች ተጋላጭ ይሆናሉ። አዕምሮአችን እንቅስቃሴ ባላደርግን ቁጥር የደም ዝውውሮችን የአዕምሮ ንቃታችንን ሊያመጣ ስለማይችል ጫናዎች ተደራራቢ በሆኑ ቁጥር እስከ አዕምሮ ደም መፍሰስ ሊያደርስ የሚችል ሕመም ሊከሰትብን ይችላል።

በሌላ በኩል ወጣቶችና ሕፃናት አብዛኛውን ሰዓት ትምህርታቸውን ከማንበብ ይልቅ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስለሆነ የዕውቀት አድማሳቸው የጠበበ ይሆናል፡፡ ከዛ ባለፈ ትምህርት ቤት ሄደውም በማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ስር ሆነው አካዳሚያዊ ከሆነው ነገር ይልቅ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ስላዩት ወይም ስላጋጠማቸው ነገር በማውራት ነው የሚያሳልፉት፡፡ ይህ እጅግ አደገኛ በመሆኑ የሚያስከትለው ጉዳት እንደ ሀገር በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

የዲጂታል ሚዲያው መቆጣጠር የምንችለው አይደለም የሚሉት ባለሙያዎች፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ሀገራት የሚቸገሩበት ጉዳይ ነው። ታዳጊ ሀገር ላይ ሲሆን ደግሞ ተፅዕኖው ከፍተኛ ይሆናል፤ ወላጆች ስለዲጂታል ሚዲያው የሚኖራቸው ግንዛቤ አነስተኛ ስለሆነና ጉዳትና ጥቅሙን በትክክል የመገንዘብ እጥረት ስላለ ችግሩ የሰፋ ይሆናል ይላሉ።

ይህንን ችግር ለመቀነስ እንደ ሀገር ፖሊሲዎች ሊኖሩን ይገባል የሚሉት የዘርፉ ባለሙያዎች፤ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ፖሊሲ ኖሮ በተለይ ሕፃናት በቀላሉ እንዳይጠቀሙ ወይም ዕድሜያቸውን ባገናዘበ መልኩ መጠቀም እንዲችሉ እንደ ሀገር መመሪያዎች ያስፈልጉናል። ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመውሰድ ተደራሽ መሆን የሌለባቸው የዲጂታል ሚዲያ አማራጮች እንዲገደቡ መንግሥት ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይጠፋ መስራት እንዳለበት ይናገራሉ።

ዲጂታል ሚዲያው ሰዎች በማንነታቸው፣ በቆዳ ቀለማቸው፣ በአፈጣጠራቸውና ባላቸው ተፈጥሮ የሚሰደቡበትና የሚንቋሸሹበት መድረክ በመሆኑ፤ ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የስነልቦና ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው፡፡ ይህንን ለመከላከል እንዲያስችል ሁለት ወገኖች ማለትም ወላጅ እና ልጅ በስምምነት ስለ ጉዳትና ጥቅሙ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር መጠቀም ያለባቸውንና የሌለባቸውን የሚዲያ አይነቶች ላይ ገደብ መጣል የሚቻል በመሆኑ በዚህ መንገድ ቴክኖሎጂው የሚያደርሰውን ከፍተኛ የሆነ ዘርፈ ብዙ ጉዳት መቀነስ ይቻላል።

በስም ከሚታወቁ የማህበራዊ ሚዲያዎች አማራጮች በተጨማሪ በይፋ የማይታወቁ ነገር ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተከታይ ያላቸው የበይነመረብ ሚዲያዎች እንዳሉ ይታወቃል፤ እነዚህ ሚዲያዎች የተቃኙት ሕፃናትና ወጣቶችን መሠረት በማድረግ ስለሆነ የሚለቋቸው የምስል፣ የድምፅና የቪዲዮ መረጃዎች በዚህ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚፈልጉት ግን የማያስፈልጋቸው በመሆኑ፤ በዚህ ከቁጥጥር ውጭ በወጣ የሚዲያ አጠቃቀም ብዙዎች ለስነአዓምሮ ሕመም ተጋላጭ እንደሚሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ።

በጣም በቤት ውስጥ በማህበራዊ ሚዲያ ተገድቦ የሚኖር ልጅ ምን እየሰራ እንደሆነ ወላጆች አብረው ሆነው በየቀኑ በግልፅነት የሚያወሩበት ጊዜ እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት ባለሙያዎች፤ ከዚህ ውጭ ወላጆች ልጆቻቸው በአካል ሄደው ከሰዎች ጋር ማውራት፣ መጫወት እንዲችሉ መንገድ መፍጠር እንዳለባቸው ይመክራሉ።

በተጨማሪም ወላጆች ወጣት ልጆቻቸው በማህበራዊ ሚዲያ ስለሚያገጥሟቸው ነገሮች በግልፅ ከቤተሰብ ጋር እንዲያወሩ ማድረግ አለባቸው፤ ይህ በማህበራዊ ሚዲያ ታዳጊ ወጣቶች የእርቃን ፎቶግራፎቻቸውን እንዲልኩ የሚጠየቁበት ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ይህንን ተከትሎ ከሚመጣ ፈተና ለማምለጥ እንዲችሉ ዕድል ይሰጣቸዋል ይላሉ።

አሁን በኢትዮጵያ ዲጂታል ሚዲያን ተጠቅሞ የሚፈፀም ጥቃት እያደገ የሚሄድ እንጂ የሚቀንስ ባለመሆኑ በዚህ ረገድ መንግሥት የተለያዩ የሕግና የፖሊሲ መመሪያዎችን በማውጣት ያሉትን ደግሞ በማጠናከር የተጠያቂነት ስርዓት እንዲኖር መስራት ይጠበቅበታል።

  • ይህንን ጽሁፍ ስናጠናቅር ከጽሁፍ መረጃዎች ባሻገር የተለያዩ ድረገጾችን እና የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮችን በምንጭነት ተጠቅመናል

 

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም

Recommended For You