አዲስ አበባ፡- በአካባቢያቸው ፍቅርና አንድነትን በመስበክ ለዘላቂ ሠላም መስፈን አበክረው በመሥራት የድርሻቸውን እንደሚወጡ በምዕራብ ጎንደር ዞን የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።
በዞኑ ገንዳ ውኃ ከተማ በሠላም ዙሪያ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል። ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምዕራብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች መምሪያ ኃላፊ ሊቀ ሥዩማን ገብረሥላሴ ገብረማርያም፤ የሠላም ዕሴቶችን መጠበቅ ለዘላቂ ሠላም መስፈን ዓይነተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
ቤተክርስቲያን ፍቅርና አንድነትን በመስበክ ጥላቻና ግጭትን እንደምታወግዝ ጠቅሰው፤ ለሕዝበ ክርስቲያኑ አስፈላጊውን ትምህርት በመስጠት ለፍቅርና ሠላም መስፈን እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
ሠላም ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ሕይወት ላለው ፍጡር ሁሉ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተው፤ የሠላም ባለቤት የሰው ልጅ በመሆኑ ሠላሙን ማስጠበቅ እንዳለበት ተናግረዋል።
የገንዳ ውሃ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አሕመድ ኑርዬ በበኩላቸው፤ ሠላም እንዲሰፍን ማድረግ የሃይማኖት አባቶች ኃላፊነት ጭምር መሆኑን ገልጸዋል። ሃይማኖቶች ሠላምን መሻትና ለሠላም መሥራት እንደሚያስተምሩም አመልክተዋል።
ተጠብቀው የቆዩ የአንድነትና የአብሮነት እሴቶችን ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተው፤ ሕዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች የእምነቱ ተከታዮች ጋር በመሆን ለዞኑ ብሎም ለሀገር ግንባታና ሠላም መሥራት እንዳለበትም ጠቁመዋል። ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ የሀገር ሽማግሌ አቶ ሲሳይ ይመር በበኩላቸው፤ ለሠላም ዘብ መቆም የፀጥታ አካሉ ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ግለሰብ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።
ትውልዱ የሠላምን እሴቶችን እንዲጠብቅ የሃይማኖት አባቶች አስተምህሮ ትልቅ ድርሻ እንዳለው የተናገሩት ደግሞ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የ504ኛ ኮር አስተባባሪ ብርጋዴል ጄኔራል አብደላ ሙሐመድ ናቸው።
ትውልዱ ለዘላቂ ሠላም መስፈን በላቀ ትብብር መሥራት እንደሚገባውም አብራርተዋል። የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አንዳርጌ ጌጡ በበኩላቸው፤ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ችግር በሠላም እንዲፈታ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሕግን ማክበርና ለሕግ ተገዥ መሆን የሀገሪቱ እሴቶች መሆናቸውን ለወጣቱ ትውልድ ማስተማር ያለባቸው መሆኑንም ተናግረዋል። በምክክር መድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም