ዜና ሐተታ
በሰኔ 2012 ዓ.ም ነበር ተመርቆ ማምረት የጀመረው ሸገር የዱቄትና ዳቦ ፋብሪካ፡፡ ይዞ የተነሳው ዓላማም በአዲስ አበባ ከተማ የዳቦ ምርትን በስፋት በማምረት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ነው፡፡ ፋብሪካው በማምረት በመጀመሪያው የሶስት ወራቶች አንዱን ዳቦ በ90 ሳንቲም ለአከፋፋይ ማህበራት ለማድረስ ነው የተስማማው፡፡ እንዲሁም ማህበራቱም ለሸማቹ ማህበረሰብ አንዱን ዳቦ በአንድ ብር ከ10 ሳንቲም ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የአንዱ ዳቦ ዋጋ አምስት ብር መድረሱ ይነገራል፡፡
የሸገር ዳቦ አቅርቦት የኑሮ ውድነት በአነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያስከትለውን ጫና ለማቃለል ታስቦ በተመጣጠኝ ዋጋ ለማቅረብ ዓላማ ያደረገ ነው፡፡በዳቦው የሚስተዋሉ የጥራትና አቅርቦት መጠነኛ ክፍተቶች ተፈትተው ለማህበረሰቡ በስፋት መድረስ እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎች ይጠቁማሉ፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በበኩሉ፤ በአሁኑ ወቅት የሸገር ዳቦ ስርጭት አድማሱን በማስፋት በቀን ከ500 ሺህ እስከ 550 ሺህ ዳቦዎች ተጋግረው በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ከ430 በላይ የሸገር ዳቦ መሸጫ ሼዶች አማካኝነት ለገበያ ይቀርባል፡፡በተለይ የዳቦ አቅርቦቱ ጠዋትና ማታ ከነዋሪዎች በተጨማሪ ለምገባ ማዕከላትና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች እንደሚሰራጭ ይገልጻል፡፡
ወይዘሮ ሳራ ወርቁ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ነዋሪ ናቸው፡፡የሸገር ዳቦን በአቅራቢያቸው ከሚገኘው ቶማስና ጓደኞቹ የሸገር ዳቦ ማከፋፈያ በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዙ እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ፡፡ የሸገር ዳቦ በሌሎች የግለሰብ ሱቆች ከሚሸጡ ዳቦዎች በዋጋው ተመጣጣኝና አነስተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተመራጭ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየባሰ በመምጣቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች መኖር እየከበዳቸው ነው፡፡ ይህን የዳቦ አቅርቦት የበለጠ በማስፋፋትና አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የዳቦ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የበለጠ ትኩረት ተደርጎ ቢሰራ የማህበረሰቡን ፍላጎት ለማሟላት የተሻለ እንደሚሆን ወይዘሮ ሳራ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሌላኛው የሸገር ዳቦ ተጠቃሚ የሆነው ሙጅብ ቃሲም የሸገር ዳቦ አቅርቦት ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለው ጠቀሜታ ጉልህ ነው። መንግሥት ለሕዝቡ አስቦ የሸገር ዳቦን ለነዋሪዎች እንዲቀርብ እያደረገ መሆኑ የሚያስመሰግነው ነው፡፡
እንደ ሙጅብ ገለጻ፤ የሚቀርበው የዳቦ ምርት ላይ በአንዳንድ ወቅቶች እጥረት እየተስተዋለ በመሆኑ ካለው የማህበረሰብ ብዛት አኳያ ተደራሽነቱ ላይ ያሉትን ችግሮች መቅረፍ ቢቻል መልካም ነው፡፡ እንዲሁም በጥራቱ እና በግራሙ ላይም የሚታዩ ክፍተቶች ሊታረሙ ይገባል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የኮሙንኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ እንደሚናገሩት፤ የከተማ አስተዳደሩ ከዳቦ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በሶስት መንገዶች እየሰራ ይገኛል፡፡ በሸገር ዳቦ የማከፋፈያ ሱቆች፣ በከተማ አስተዳደሩና በባለሀብቶች ጥምረት በተገነቡ 20 የዳቦ ፋብሪካዎች፤ እንዲሁም ከአንድ ሺህ 300 በላይ በሆኑ በግል ዳቦ ቤቶች አማካኝነት ለህብረተሰቡ በመሰራጨት ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ አኳያ ቢሮው ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ በሸገር ዳቦ፣ በግል ባለሀብቶችና በመንግሥት አጋርነት በተገነቡ ዳቦ ቤቶች አማካኝነት ከ85 ሚሊዮን በላይ ዳቦዎችን ለህብረተሰቡ እንዲሰራጭ ተደርጓል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በእያንዳንዱ የሸገር ዳቦዎች ላይ ከተማ አስተዳደሩ ድጎማ የሚያደርግባቸው ናቸው፡፡እያንዳንዱ ዳቦ 70 ግራም እንዲሆንና በአምስት ብር እየተሰራጨ እንደሚገኝ ያነሳሉ፡፡
እንደ አቶ ሰውነት ገለጻ፤ የሸገር ዳቦ ምርት የማምረት አቅሙ በቀን አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከ500 ሺህ እስከ 550 ሺህ ዳቦዎች ተጋግረው ከነዋሪዎች በተጨማሪ ለምገባ ማዕከላትና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ይሰራጫሉ፡፡
የሚሰራጨው ቁጥር አነስተኛ የሆነበት ምክንያት የተለያዩ አማራጮች በመኖራቸው ከፍላጎት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ እነኝህ ዳቦዎችም በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ከ430 በላይ የሸገር ዳቦ መሸጫ ሼዶች አማካኝነት ጠዋትና ማታ ለህብረተሰቡ እየቀረቡ መሆኑን ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ የሸገር ዳቦ መሸጫ ሼዶች አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም ከልማት ጋር በተያያዘ ለተነሱ መሸጫዎች አማራጭ ቦታዎችን በማፈላለግ መልሰው የሚደራጁበት ሁኔታ እንደሚኖር ያመላከቱት አቶ ሰውነት፤ የስርጭት መጠኑንና አቅርቦቱን ለማስፋት የሸገር ዳቦን ከሚያመርተው ኩባንያና ምርቱን ተቀብለው ከሚያሰራጩ ማህበራት ጋር የጋራ መድረኮችን በማዘጋጀት ችግሮች እንዲቀረፉ የማድረግ ሁኔታ እንደሚኖር ይጠቁማሉ፡፡
ከሸገር ዳቦ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከጥራትና ግራም ጋርም ላይ ችግሮች አሉ የሚል ትክክለኛ ያልሆኑ እሳቤዎች አሉ፡፡ ስርጭትም ከተካሄደ በኋላ ጥብቅ ቁጥጥሮች እየተደረጉ ነው፡፡ ከሸገር ዳቦዎች በተጨማሪ ሌሎች በርካታ አማራጮች በመኖራቸው በአንዳንድ አካባቢዎች አቅራቢዎች ገበያ እንዳያጡ የሚያነሱበት ሁኔታ መኖሩንም ዳይሬክተሩ ይናገራሉ፡፡
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም