አዲስ አበባ፡– በአዲስ አበባ ለአንድ ወር በሚካሄደው የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የምዝገባ ዘመቻ አንድ ሚሊዮን ነዋሪዎችን ለመመዝገብ መታቀዱን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ ለአንድ ወር የሚቆይ የብሔራዊ መታወቂያ የምዝገባ ዘመቻ ዛሬ ይጀመራል።
ምዝገባው በ119 ወረዳዎች፣ በሁሉም ክፍለ ከተሞች፣ በዋና መሥሪያ ቤትና ቅርንጫፎች ላይ ይካሄዳል ያሉት አቶ ዮዳሄ፤ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው ዘመቻው ለቀጣይ አንድ ወር የሚቆይ ይሆናል ብለዋል፡፡
በሀገር ደረጃ ወጥ የሆነና ተናባቢነት ያለው የመታወቂያ ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ፋይዳ የመታወቂያ ካርዶችን እርስ በእርስ የሚያናብብ መሠረታዊ የሆነ ሥርዓት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአንድ ወሩ የምዝገባ ዘመቻ አንድ ሚሊዮን ነዋሪዎችን ለመመዝገብ መታቀዱን በመግለጽ፤ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባው ክፍያ የሌለው ሲሆን፤ ካርዱን ለመውሰድ የሚከፈለውን ክፍያ ዝቅ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ ከትናንሽ ከተሞች ጀምሮ ከ300 በላይ የክልል ከተሞች ላይ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ፋይዳ የሰነድ መጭበርበርን ለማስቀረት፣ ተቋማትንም ለማናበብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ከዘመኑ ጋር የተናበበና አገልግሎትን ማግኘት የሚያስችል ዲጂታል የመታወቂያ ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ፋይዳ 12 ዲጂት ቁጥር ያለው ከመልክ፣ አሻራ፣ ዓይን ከሚወሰዱ ቁጥሮች የሚመጣ መረጃ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በኢትዮጵያ የዲጂታል ስትራቴጂ 2025 እቅድ አካል መሆኑን በመግለጽ፤ ፋይዳ የሀገሪቱን የሰው ሀብት ለማወቅ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ በበኩላቸው፤ የፋይዳ ምዝገባ በዋናው መስሪያ ቤት፣ በሁለት ቅርንጫፎች፣ በ11 የኤጀንሲው የክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችና በ119 የወረዳ አገልግሎት መስጫ ቅርንጫፎች ላይ ይካሄዳል፡፡
ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በሀገሪቱ ከማንነት አስተዳደር ጋር ተያይዘው ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ሥርዓት ነው ያሉት አቶ ዮናስ፤ በተለይም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ጤናማ እንዲሆኑ የሚያስችል በቂ መረጃ የሚያዝበት ነው ብለዋል፡፡
የምዝገባ ሥራውን ለማሳለጥ የጋራ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ጠቅሰው፤ የትስስር ሥርዓቱ በከተማ ደረጃ የተጀመረውን የዲጂታል አገልግሎት ለማስቀጠል እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ኤጀንሲው የሚያካሂዳቸው የወሳኝ ኩነት ምዝገባዎች ለፋይዳ ሥርዓት መጋቢ እንደሚሆን በመግለጽ፤ የከተማውን ነዋሪ በፋይዳ ሥርዓት ውስጥ መዝግቦ መያዝ የአገልግሎት ቅልጥፍናዎችን ለማሻሻል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የነዋሪነት መታወቂያ የያዙና የተመዘገቡ የከተማው ነዋሪዎች በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መመዝገብ እንደሚኖርበትም ገልጸዋል፡፡
ዘመቻውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በመተባበር እንደሚያካሂዱት ተገልጿል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም