ከመንግስታቱ ማኅበር እስከ ተባበሩት መንግስታት የቀጠለው የኢትዮጵያ ደማቅ ተሳትፎ !

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምስረታ ላይ የተጫወተችው ታሪካዊ ሚና በቀላሉ የሚረሳ አይደለም፡፡ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ በሚማቅቁበት በዚያን ወቅት የአፍሪካውያን ወኪል፣ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ሆና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተጸነበት የሳንፋራንሲስኮው ጉባኤ ልዑኳን በመላክ የመስራችነት ድርሻዋን ተወጥታለች፡፡

በጉባኤው የኢትዮጵያ ልዑካን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተርን በመቅረጽ ከነበራቸው አበርክቶ ባለፈ፤ የአፍሪካ ድምጽ በመሆን በቻርተሩ ላይ የአፍሪካውያን ድምጽ እንዲሰማ አድርገዋል።

የድርጅቱን መርሆዎች እና ዓላማዎች ከመነሻው በመቅረጽ ትርጉም ያለው ተሳትፎ አድርጋለች፤ ይህ ተሳትፎዋም በአፍሪካ ሕብረት ምስረታ ላይ የመሪነት ሚና እንዲኖራት አድርጓታል።

የኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ የነበራት ተሳትፎ የመንግስታቱ ማሕበር (League of Nations) ካላት የመስራችነት አስተዋጽኦ የሚነሳ ቢሆንም፤ ሀገሪቱ በፋሽስቱ የጣሊያን መንግስት ወረራ ሲፈጸምባት፣ ወረራውን አስመልክታ ላቀረበችው አቤቱታ ምላሸ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆን አልቻለም።

በወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ተገኝተው የዓለም መንግስታትን ኢፍትሃዊነት እና የፋሽስቱ ወራሪ በኢትዮጵያ ላይ ስላደረስው አሰቃቂ ግፍ እና በደል ድምጻቸውን አስምተዋል፡፡ ከማሕበሩ አባል ሀገራት ያገኙት ምላሽ ግን ማኅበሩ ከተመሰረተበት ዓላማ አኳያ ትልቅ ግድፈት እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያመላክታሉ።

ይህ የሀገሪቱ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ያላት ተሳትፎ በመንግስታት እና በመሪዎች መቀያየር ሳይለዋወጥ ዛሬም ድረስ ዘልቋል፡፡ ኢፍትሀዊነትን በአደባባይ ከማስተናገድ ጀምሮ፤ በብዙ ጫናዎች ውስጥ እስከ ዛሬዋ እለት ድረስ የቆየና ዘርፈ ብዙ ተሳትፎዎችን ያካተተ ነው።

ሀገሪቱ ሰማንያ ዓመቱን ሊደፍን አንድ ዓመት በቀረው የተባባሩት መንግስታት ድርጅት ረጅም የታሪክ ሂደት ውስጥ ከምስረታው እስከ አሁናዊ ሕልውናው፤ ለድርጅቱ መርሆዎች ተገዥ በመሆን፤ የሚጠበቅባትን እያበረከተች ትገኝለች። በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አትርፋለች፡፡

ለሰላም እና መረጋጋት፤ ከዚህ ለሚመነጭ የዓለም ስርዓት ባላት ቁርጠኝነት የተነሳም ከኮሪያ እስከ ኮንጎ፣ ከሩዋንዳ እስከ ዳርፉር በተለያዩ ጊዚያት መስዋእትነት በሚጠይቁ የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች ወታደሮቿን በመላክ ደማቅ አሻራዋን አስቀምጣለች፡፡

ሀገሪቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የነበራት ሚና በሰላም እና ደህንነት ላይ ብቻ ሳይገደብ እንደ አንድ አባል ሀገር ያላት ተሳትፎ የጋራ ደህንነት እሳቤን (Collective security) በማቀንቀን ለሌሎች ሀገራት አርዕያ የመሆን ተግባራትን አከናውናለች።

በርግጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገና ከጅምሩ የተመሰረተበት/የአሸናፊዎች ሕብረት ጥያቄ ያነገበ፤ የመላው ዓለም ሀገራትን ድምጽ የሚያስተጋባ፤ ለፍትህ እና ለእኩልነት እሳቤዎች የተገዛ እንዲሆን ብዙ ጠያቂ ድምጾችን ሲያስተናግድ የቆየ ነው።

በተለይም አሁንም ድርጅቱ የሀያላን ሀገራት ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቂያ እና በዓለም ሰላም ላይ የተወሰኑ ሀገራት የበላይነት የሚታይበት፣ ኃይል እና ጉልበት ያላቸው ሀገራት በሌሎች ሀገራት ጣልቃ በመግባት የሚፈነጩበት ነባራዊ ሁኔታ መፍጠሩ በዓለም የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ ጎልቶ የሚታይ ሆኗል፡፡ ይህም በድርጅቱ ላይ የሚነሱ የፍትሀዊነት ጥያቄዎች እየበረከቱ እንዲሄዱ እያደረገው ነው።

ለዚህ አሁን ላይ እንደ ዋንኛ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው የተባበሩት መንግስታት አንድ አካል የሆነው የጸጥታው ምክር ቤት ነው:: የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በድርጅቱ ቻርተር የዓለም ሰላም እና ደህንነትን ለማስጠበቅ ቁልፍ ተግባር የተሰጠው ወሳኝ አካል ነው።

ምክር ቤቱ ካሉት ትላልቅ ኃላፊነቶች ውስጥ የዓለም ሰላምን የሚያውኩ ግጭቶችን እና ጦርነቶችን መከላከል እና ማስቆም፣ በተለያዩ የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያቶች የሚነሱ ችግሮችን መቅረፍ፣ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ማድረግ ብሎም ጦርነት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን ማሰማራት በአብይነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የጸጥታው ምክር ቤት ከምስረታ ጀምሮ የመጣባቸው መንገዶች ሁሉ ይህንን ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንዳላስቻሉት ብዙዎች ይሞግታሉ፤ የፍትሀዊነት እና የአሳታፊነት ችግሮች እንዳሉበትም በተጨባጭ የሚታዩ እውነታዎች በአደባባይ እየፈተኑት ነው። የተለያዩ ሀገራትም የጸጥታው ምክር ቤት ውክልና ሁሉንም አሳታፊ እንዲሆን የተደጋገሙ ጥያቄዎችን እያነሱ ነው፡፡

በተለይም ድምጽን በድምጽ የመሻር (Veto power) ያላቸው ሀገራት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ በብቸኝነት መያዛቸው፤ በምክር ቤቱ ያለው ውክልና የሁሉንም ሀገራት ድምጽ ማስተናገድ የማያስችል፤ በተለይም የአፍሪካ እና የላቲን አሜሪካን ሕዝቦች ተገቢው ቋሚ ውክልና እንዳይኖራቸው አድርጓል።

ይህ ፍትሃዊ ያልሆነ ውክልና የምክር ቤቱን ውሳኔዎች የሚያዛባ ከመሆኑም ባሻገር በተለይም አፍሪካውያንን ጉዳያቸው አግባብ ባለው ውክልና እንዳይታይ አድርጎታል። በምክር ቤቱ የሚተላለፉ አፍሪካውያንን በአንድም ይሁን በሌላ በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ ድምጻቸው እንዳይሰማ ፈተና ሆኖባቸዋል። የውሳኔ ሀሳብ ተቀባይ የሆኑበትን ሁኔታ ፈጥሯል።

በዚህም በጸጥታው ምክር ቤት የሚወሰኑ ውሳኔዎች በአፍሪካ ጥቅም ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረሱ ነው። በአህጉሪቱ የሰላም እና የጸጥታ ጉዳዮች ኃያላን ሀገራት ብቻቸውን ውሳኔ እንዲወስኑ በማድረግ፤ የአፍሪካውያን ድምጽ በዓለም አቀፍ ውሳኔዎች ላይ ተሰሚነት እንዳይኖረው አድርጓል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ አሁን ያለው የጸጥታው ምክር ቤት መዋቅር ብዙ የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ግዛት ሥር በነበሩበት ወቅት የነበረውን የኃይል ሚዛን የሚያንጸባርቅ በመሆኑ፤ ምክር ቤቱ በአፍሪካ ላሉ ሰብዓዊ ቀውሶች ፈጣን ምላሽ ከመስጠት አንጻር አዝጋሚ ሄደቶችን እንዲከተል አድርጎታል። ለዚህም ሩዋንዳ እና ዳርፉርን፤ ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አካባቢዎች ለተፈጠሩ ግጭቶች የሠጣቸው ምላሾች ችግሩ ያልተገባ ብዙ ዋጋ እንዲያስከፍል አድርጓል።

ከነዚህ እና ከሌሎች የፍትሀዊነት እና የአሳታፊነት ክፍተቶች አኳያ የጸጥታው ምክር ቤቱ ለውጥ እንዲደረግበት በአፍሪካ ሀገራት መካከል የጋራ መግባባት ላይ ከተደረሰ ውሎ አድሯል። ከአፍሪካ፣ እስያ እና ከላቲን አሜሪካ ተጨማሪ ቋሚ አባላትን በምክር ቤቱ ማካተት እንዳለበት በርካታ ሀሳቦች እና ጫናዎች እየተበራከቱ ነው።

አፍሪካውያን በጸጥታው ምክር ቤት ላይ የሚያነሱት ጥያቄ የውክልና ጉዳይ ብቻ አይደለም። አፍሪካ ከዓለም ሁለተኛዋ የሕዝብ ብዛት የሚኖርባት አህጉር እንደመሆኗ የወደፊቱ ዓለም አቀፉ ስርዓት አፍሪካን እና የአፍሪካ ድምጾችን ተሰሚ ስለማድረጉ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እራሱ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በሚያስችል ቁመና ውስጥ ሆና ማየትን ይፈልጋሉ።

በርግጥ ዓለም በመርህ ደረጃ እየተገዛበት ካለው ፍትሀዊነት አኳያ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ውክልናን ማግኘቷ ይዋል ይደር እንጂ የማይቀር ነው። ቀጣዩ ጥያቄ የሚሆነው አህጉሪቱ ከአፍሪካ ሕብረት ይልቅ በሀገር ትወከል ከተባለ በማን ትወከል፤ አፍሪካን በጸጥታው ምክር ቤት ሊወክሉ የሚችሉ ሀገራት እነማን ይሁኑ የሚለው ነው፡፡

ኢትዮጵያ በጸጥታው ምክር ቤት የአፍሪካን መቀመጫ ለማግኘት እና አህጉሯን ለመወከል በእጩነት የመቅረብ አሳማኝ እና በቂ ምክንያት ያላት ይመስለኛል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር አፍሪካን በጸጥታው ምክር ቤት ለመወከል ተወዳድረው ሊቀርቡ ይችላሉ ከሚባሉት ሀገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ ናይጀሪያ እና አልጀሪያ ይጠቀሳሉ፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በማድረግ ረገድ ያላት ልምድ እና ተሳትፎ፣ ለባለብዙ ወገንተኝነት ያላትን ቁርጠኝነት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ከማዋለድ እስካሁን ድረስ ያላት ጉልህ ሚና ጠንካራ ተወዳዳሪ ያደርጋታል፡፡

ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ለመውጣት ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ለትግሉ ስነልቦናዊ መነቃቃት የነበራት አበርክቶ፤ የትግሉ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ አስተሳሰብ መሰረት የሆነውን የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳስብ በመፍጠር እና በማጎልበት ከዛም ባለፈ ለነጻነት ትግሉ አጋር በመሆን ያበረከተችው አስተዋጽኦ አፍሪካውያን ለመወከል የተሻለች ተመራጭ ያደርጋታል።

በአፍሪካ ውስጥ የነበረውን የቅኝ ግዛት ስርዓት ለወዋጋት የአንድነት እና የወንድማማችነት ሕብረት የሆነውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (OAU) በመመስረት ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም መሆኑዋ፤ በወቅቱ የነበረውን የአፍሪካውያን ፍላጎቶች በማቻቻል አፍሪካዊ ግንባር በመፍጠር፤ የነጻነት ትግሉ ስኬታማ እንዲሆን የነበራት አስተዋጽኦ በምክር ቤቱ አፍሪካን እንድትወክል የሚያስችል በቂ ሀገራዊ ትርክት ነው፡፡

የኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግስት ታሪክ ውስጥ ጎልተው የሚታዩ ስለፍትህ እና ነጻነት የተደረጉ ከሕዝቦቿ ማኅበረሰባዊ ስነልቦና የሚቀዱ የተጋድሎ ታሪኮች፤ የአፍሪካውያንን የፍትህ እና የነፃነት ጥያቄዎች በአግባቡ ለማስተናገድ የሚያስችሉ ዋነኛ ሀገራዊ እሴቶቿ ናቸው።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ ሕብረት መስራች አባል መሆኗ፤ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድርጓ፤ ቀጣናዊ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በማስታረቅ ያላት ልምድ እና በአፍሪካውያን ዘንድ እንደ ሀገር ያላት ከበሬታ ለቦታው እንድትታጭ ተጨማሪ አቅም የሚሆኑ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ያላት ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ፣ በአፍሪካ ትልቅ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገር መሆኗ፤እስካሁን ባለው እውነታ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርሆች ተገዥ፤ ለመርሆቹም ተፈጻሚነት ጠንካራ ተሟጋች መሆኗ፤ በአፍሪካ ካሉ ግዙፍ አምስት ኢኮኖሚዎች ሲታከልበት የጸጥታውን ምክር ቤት መቀመጫ ለማግኘት ቀዳሚ ባለ እድል ያደርጋታል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ የጸጥታው ምክር ቤትን ቋሚ መቀመጫ ማግኘት የቀጣዩን ዘመን የዋጀ፣ የኢትዮጵያን ንቁ ተሳትፎ በዓለም መድረክ ከፍ የሚያደርግ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን እድል በአግባቡ ለመጠቀም የአፍሪካ ሀገራትን ይሁንታ ለማግኘት ከአሁኑ ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን በመስራት የኢትዮጵያን ተሰሚነት ወደ ተሻለ ከፍታ ማድረስ ይገባል፡፡

በኤልያስ ጌትነት

አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You