ለነጻነት ሳይሰዉ፤ ለእድገት ሳይተጉ የሚናፍቋት ሀገር አትገኝም

እውነት ለመናገር ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሀገሩን የሚጠላ ወይንም እድገትና ብልጽግናዋን የማይናፍቅ ያለ አይመስለኝም።ኢትዮጵያውያን ሀገር ጥሪ ስታደርግላቸው ህይወታቸውን ጭምር መስዋዕት በማድረግ ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር ሲገልጹ ኖረዋል፡፡ዛሬም በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ኢትዮጵያን አሳልፈን አንሰጥም የሚሉ እልፍ አእላፍ ኢትዮጵያውን በአራቱም ማዕዘናት አሉ፡፡

የዛሬዋም ኢትዮጵያ የትናንት ጀግኖች የመስዋዕትነት ውጤት ነች፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን በርካቶች የሚያሳሳ ህይወትን ከመገበር ጀምሮ ብዙ መስዋእትነት ከፍለዋል። ደረጃውና ሁኔታው ቢለያይም ዛሬም ለሀገራቸው መስዋእትነት የሚከፍሉ አሉ። በእርግጠኝነት ነገም ይኖራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው።

ያለፉት ጥቂት ዓመታት ከሰላምና ልማት ይልቅ የጦርነትና የጥፋት ዜናዎችን ስንሰማ የቆየንበት ወቅት ሆኗል። በዚህ አይነት ነገሮች አንድ ጊዜ ቀዝቀዝ አንድ ጊዜ ሞቅ እያሉም ዛሬ ላይ ደርሰናል። የሀገር ውስጥ ችግሮቻችንን ለጊዜው ትቼ ወደውጪው ባተኩር እስከ ቅርብ ጊዜ ቀዳሚ የስጋታችን ምንጭ የነበረው የዓባይ ግድብ ጉዳይ ነበር።

ግብጻውያንና ሌሎች የኢትዮጵያ ሉአላዊነት መጠበቅ፤ የሀገሪቱ ማደግና መበልጸግ ስጋት የሆነባቸው የአፍሪካም ሆነ የአውሮፓ ሀገራትና አሜሪካ የዓባይ ግድብ ከዳር እንዳይደርስ ብዙ ተንቀሳቅሰዋል። በተለይም ከዓመታት በፊት በሀገር ውስጥ የነበረውን የስልጣን ሽግግር ተከትሎ በተፈጠረው ውጥረት በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አለች ከመባል ነበረች ወደ መባል መንገድ ላይ ነች ብለው በይፋ ሲያወሩ ነበር። በእጅ አዙር በሀገር ውስጥ ካሉ ባንዳዎች ጋር ሲያደርጉት የነበረው ግንኙነት እንደተጠበቀ ሆኖ።

በመሰረቱ የውጪ ጠላቶቻችን እንቅስቃሴያቸው ሞቅ ቀዝቀዝ ሲል ይቆይ ይሆናል እንጂ መቼም ቢሆን ኢትዮጵያ ሰላም ሆና እንድትኖር የሚፈቅዱ አይሆንም። ለምሳሌ ግብጽ የህልውናዬ መሰረት የምትለው ዓባይ ከምንጩ ጀምሮ በእሷ ፈላጭ ቆራጭነት ስር መውደቁን ካላረጋገጠች ከኢትዮጵያ ላይ አይኗንም እጇንም ታነሳለች ብሎ ማሰብ ዘበት ነው።

ይህን የማነሳው አንዳንድ ሰዎች በዚህ ጉዳይ አስተያየት ሲሰጡ እንዲህ ስለሚሉ ነው። ግብጽ የህዳሴው ግድብ ሙሌት ከተጠናቀቀ በኋላ በግድቡ ዙሪያ የምታነሳው ጥያቄ አይኖርም። ምክንያቱም በአንድ ወገን እስካሁን የምታገኘውን ውሃ በቀጣይም የምታገኝ በመሆኑ ሌላ እሰጥ አገባ ውስጥ አትገባም። በሌላ በኩል በኃይል ለመናድ ብታስብ እንኳን ሌላው ቢቀር በግድቡ መፍረስ የጉዳቱ ቀዳሚ ተጠቂ የምትሆነው ራሷ ግብፅ ናት የሚል ሃሳብ ሲያነሱ ይደመጣሉ ።

በመሠረቱ ግብጽ እስካሁን የምታገኘው የውሃ መጠን በተደጋጋሚ ይገለጽ እንጂ ከዛ በላይ ውሃ አያስፈልገኝም ብላ አታውቅም። በእርግጠኝነትም አቅሟ ከደረጀና ኢኮኖሚዋ ከዳበረ ብዙ የናስር ግድቦችን ገንብታ ሀይቅ እንደምትሰራ መገመት ቀላል ነው። የዓባይ ውሃ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግብጻውያንን በሥራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በፍራፍሬ ምርት የውጪ ምንዛሪ የገቢ ምንጫቸው መሆኑም መዘንጋት የለበትም። ይህ እንግዲህ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።

ሁለተኛው ጉዳይና ምን አልባትም የስምምነቱ አንድ ፈተና የሆነው ግብጽ እስካሁን ስታገኝ የነበረውን የውሃ መጠን ወደ ፊትም እንደማይቀነስ ማረጋገጫ ይሰጠኝ የሚለው ነው። ይህም ቢሆን እኔ ብቻ ብልጥ ልሁን የሚል አይነት የምስሮች የቆየ ጨዋታ ነው። ኢትዮጵያ ግብጽ እስካሁን የምታገኘውን ውሃ አትቀንስም ማለት ኢትዮጵያ ለተፈጥሮ ጥብቅና ትቆማለች አልያም ተፈጥሮን ትቆጣጠራለች ማለት አይደለም።

ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ ላይ የሚኖራት የአቋም ጽናት ጠቀሜታው አሁን እየተገነባ ላለው የህዳሴ ግድብ ብቻ አይደለም። ይልቁንም በአንድ ወገን ከዚህ በኋላ በዓባይ ጉዳይ ከሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ጋር የሚኖርን ግንኙነት መስመር የሚያስይዝ ይሆናል። ከኢትዮጵያ ተነስተው ወደሌሎች ጎረቤት ሀገራት የሚፈሱ ወንዞችን በተመለከተም ምን መሥራት አለበት? እንዴት ማስተዳደር አለብን ለሚለውም የሚያመላክተን ብዙ ነገር ስለሚኖር ነው።

የባህር በር ጉዳይም እንዲሁ ተመሳሳይ መሰረት ያለው ነው። ዛሬ ኢትዮጵያን የከበቧት ባለ ባህር በር ሀገራት እንደ ሀገር ሳይቆሙ ኢትዮጵያ የባህር በሮች ባለቤት ነበረች። በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩ አጋጣሚዎችና የውስጥ ድክመታችን ዛሬ ላለንበት ሁኔታ ዳርጎናል። ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ዛሬ በሰጥቶ መቀበል መርህ እያቀረበች ያለው የባህር በር ጥያቄ ማንንም ለማሸማቀቅ፤ የማንንም ሉአላዊነት ለመድፈር፤ ማንንም ለመውረር ያሰበ አይደለም።

ትንሽ ወደኋላ መለስ ብንል የአንድን ሀገር ሉአላዊነት በመዳፈር ወረራ መፈጸም የለመደው ማን እንደሆነ እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለም ያውቀዋል። በዚህ ረገድ እየቀረቡ ያሉ ዛቻዎች፤ ይመሰረታሉ የተባሉ ጥምረትና ህብረቶችም እኛ እጅ እስካልሰጠንና እስካልተከፋፈልን የትም ሊደርሱ አይችሉም። በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ከግምት በማስገባት ለነጻነቱ ሲል አንድነቱን አስጠብቆ በየዘመኑ ሊከፍላቸው የሚገቡ መስዋእትነቶች እንዳሉ ማወቅ አለበት።

ሁለተኛው ጉዳይ የሀገር ልማት ጥያቄ ነው። አሁን ያለው ነባራዊው ሁኔታ የሚነግረን ልማት የነጻነት መሰረት መሆኑን ነው። ጠንካራ ኃይል ያቋቋመ፤ እርዳታ ብድር የማይጠይቅ፤ መንግሥትና ሕዝብ ነጻነቱን ለድርድር ሊያቀርብ አይችልም። ነጻነቱን የሚገዳደሩ አካላት ቢኖሩ እንኳን አስር ጊዜ ደጋግመው እንዲያስቡ ከመገደዳቸው ባሻገር ለሚወስዱት እርምጃም የሚሰጣቸው ምላሽ ቀላል አይሆንም።

በዚህም ልማት፤ እድገትና ነጻነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን መመልከት እንችላለን። ለዛሬው ጽሁፌ ላነሳ ያሰብኩት ሃሳብ ግን በመንግሥትና ሌሎች ተቋማት በከፍተኛ ወጪ ስለሚገነቡ ትልልቅ ፕሮጀክቶች አይደለም። በእርግጥ እነዚህን ፕሮጀክቶች ሕዝቡ እንደ አይኑ ብሌን ሊንከባከባቸው እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም።

ከዛም ባለፈ የእያንዳንዳችን ሥራ ድምር ውጤት እንደ ሀገር ትልቅ ፋይዳ አለው። እንዴት የሚለኝ ካለ ምላሼ መንግሥት እርዳታ የሚያደርገው ድጎማ የሚያደርገው በግለሰብ ደረጃ ራሳችንን መቻል ስላቃተን ነው። ተፈናቃይ የግጭት ተጎጂ ካልንም ምክንያቱ እኛው እንሆናለን።

በተፈጥሮ አደጋ የደረሰባቸው የሚለኝም ካለ፤ መንግሥት ራሳችንን መቻል ያቃተንን እና በእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ዘለን የምንገባበትን ሁኔታ ብንቀንስለት ለእነዚህ የሚያንስ አቅም ይኖረዋል ብዬ አልገምትም። በመሆኑም ነጻ በሆነች ሀገር ለመኖር መስዋእትነት መክፈል፤ የበለጸገች ሀገር ለማየት በያለንበት ጠንክረን መሥራት የግድ ይለናል።

ራሰወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም

Recommended For You