ዜና ትንታኔ
ሀገራዊ እሴቶችን በማህበረሰቡ ቋንቋ ለየአካባቢው ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑ እሙን ነው። በሌሎች መገናኛ ብዙኃን የማይሸፈኑ አካባቢያዊ መረጃዎችን ለማህበረሰቡ በማድረስ የማህበረሰቡ ወግ፣ ባህልና ቋንቋ እንዲዳብር ከመስራት በተጨማሪ የማህበረሰቡ ትስስር እንዲጠናከርና ሰላም እንዲሰፍን በየአካባቢው ቋንቋ በማህበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ሊፈጥሩ እንደሚገባ ይገለጻል።
ለመሆኑ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች አገልግሎት በኢትዮጵያ ምን ያህል ነው፤ አገልግሎታቸውስ ምን ይመስላል፤ በተለይ ህብረተሰቡን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከማንቃትና ከማሳተፍ አንጻር፤ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ለሬዲዮ ጣቢያዎቹ ምን አይነት ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል?
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ተኮር ሬዲዮ ጣቢያ ጊዜያዊ ተጠሪ አቶ ኤፍሬም አክሊሉ እንደሚገልጹት፤ የሬዲዮ ጣቢያው በድሬዳዋ ከተማና አካባቢው ለሚኖሩ ዜጎች መረጃን ተደራሽ ለማድረግ በ2014 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ ለአንድ ዓመት የሙከራ ስርጭት ካከናወነ በኋላ ወደ መደበኛ ስርጭት መግባት ችሏል።
በአካባቢው የተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎች ቢኖሩም ከእነኝህ ጣቢያዎች በተለየ መልኩ ታችኛውን የማህበረሰብ ክፍል አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚዳሰሱባቸውን መሰናዶዎች በማዘጋጀት ተደራሽ ያደርጋል የሚሉት አቶ ኤፍሬም፤ በዋናነትም የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና ለማሳደግና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉና ከተለመደው መንገድ ለየት ያሉ የጤና፣ የሕግ፣ የስነልቦናና ማህበረሰቡ የተሻለ የኑሮ ደረጃ እንዲኖረው የሚያስችሉ ይዘቶች አየር ላይ እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ።
እንደ ተጠሪው ገለጻ፤ የሬዲዮ ጣቢያው የአየር ሰዓት የማይሸጥ በመሆኑ ለማህበረሰቡ የሚጠቅም የትኛውንም የፕሮግራም ሃሳብ ይዞ ከሚመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነው። ለአብነትም ከሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የቀይመስቀል ድርጅት እንዲሁም ከከተማ አስተዳደሩ ፍትህ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን ‹‹ንቃተ ሕግ›› መሰናዶ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እየተደረገ ይገኛል።
ማህበረሰቡን በማንቃትና አመለካከቱን በመቀየር ምክንያታዊ የሆነ አስተሳሰብ ያላቸውን ዜጎች መቅረጽ ላይ ትኩረት ይደረጋል። አንዱ ብቻ ነጋሪ ሳይሆን ዜጎች እርስ በእርስ የሚማማሩበት፣ ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት፣ ከፖለቲካ ነጻ መድረክ በመፍጠርና በዩኒቪሲቲው በሚገኙ ምሁራን የተሰሩ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ወደማህበረሰቡ ወርደው የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ የሚያስችል ተግባር እንደሚከናወን አቶ ኤፍሬም ያመላክታሉ።
በአሁኑ ወቅት ሬዲዮ ጣቢያው በመምህራን፣ ተማሪዎችና በጎ ፍቃደኞች በመታገዝ እየሰራ እንደሚገኝ የሚያነሱት ተጠሪው፤ በቀጣይም የሰው ሀይል ቅጥር በመፈጸም በአማርኛ፣ አፋን ሱማሌ፣ አፋን ኦሮሞና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች ለመስራትና በሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ወደ ህብረተሰቡ በመድረስ ይህን ጅማሮ በይበልጥ ለማሻሻል እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬዲዮ ሥራ አስኪያጅና የኢትዮጵያ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ማህበር ሥራ አስፈጻሚ አባል አለምሸት ተሾመ እንደሚናገሩት፤ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ከሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎች በተለየ መልኩ በአስተዳደር፣ ፕሮግራም ዝግጅትና በባለቤትነት ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ የተቋቋሙ ናቸው።
እንደ አቶ አለምሸት ገለጻ፤ በየአካባቢው ማህበረሰቡ ከባህል፣ እምነት፣ ቋንቋና አኗኗር ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ታችኛው ማህበረሰብ በችግሮቹ ላይ እንዲወያይና መፍትሄ እንዲያበጅ ግልጋሎት እየሰጡ ነው። ከማህበረሰቡ በተወጣጡ ዜጎች በጣቢያዎቹ የሴቶች፣ የልጆች፣ የአርሶ አደሮችና የመሳሰሉ መሰናዶዎች እንዲዘጋጁ እየተደረገ ነው።
“በጣቢያዎቹ በአዝመራ ወቅት የግብርና ባለሙያዎች አስፈላጊ መረጃዎችን ለአርሶ አደሮች እንዲያደርሱ እየተደረገ ነው። እንዲሁም ከብት የጠፋበት ግለሰብ በሬዲዮ አስነግሮ እስከማግኘት ድረስ እየተገለገለበት ነው” የሚሉት አቶ አለምሸት፤ ሀገራዊ ሚዲያዎች ከጊዜና ከበጀት አኳያ ለሁሉም አካባቢዎች ሽፋን መስጠት የማይችሉ በመሆኑ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ክፍተቱን ለመሙላት እየጣሩ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ጣቢያዎቹ የአቅም ውስንነት፤ የቴክኒክ ብልሽት እና የስርጭት መቆራረጥ፤ የሚዲያ ቁሳቁስ እና የባለሙያ እጥረት ለስራቸው እንቅፋት ሆኖባቸዋል። እንዲሁም ከጊዜው ጋር ለመራመድ የሚያስችል የቴክኖሎጂ እጥረት ቢኖርባቸውም የተቋቋሙበትን ዓላማ ለማሳካት ጥረት እያደረጉ ነው። በጣቢያዎቹ የሚያጋጥሙ የቴክኒክ ችግሮችን ለመፍታትም ሀገር አቀፍ ሚዲያዎች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ይገልጻሉ።
አቶ አለምሸት፤ ጣቢያዎች በርካታ መሰናዶዎች በማዘጋጀት አድማጮችን ካገኙ በኋላ የበጎ ፍቃደኞቻቸውን ወጪ መሸፈን ባለመቻላቸው የፕሮግራሞች ቀጣይነት ማጣት ይስተዋላል። የተወሰኑ ጣቢያዎች ለበጎ ፍቃደኞቹ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ እየሞከሩ እንደሚገኙ ያነሳሉ።
ጣቢያዎቹ ለጋዜጠኝነት ሙያ ማደግም የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን የሚገልጹት አቶ አለምሸት፤ በዩኒቨርሲቲዎች በሚተዳደሩ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች አብዛኞቹ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ያላቸው በመሆኑ የባለሙያ እጥረት እንደሌላቸውና እንዲሁም የሥራ ማስኬጃና ቁሳቁስ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ይላሉ።
በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የመገናኛ ብዙኃን ፍቃድ ምዝገባና እውቅና ዴስክ ኃላፊ ደሴ ከፋለ እንደሚናገሩት፤ መገናኛ ብዙኃን እንደየባህሪያቸውና አገልግሎታቸው መሰረት በተለያየ መልኩ ይከፈላሉ። ከእነኝህም ውስጥ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን ይገኙበታል። ይህም አንድ የጋራ ፍላጎት ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የሚያቋቁሙት የመገናኛ ብዙኃን አይነት ሲሆን፤ ዓላማውም ከማህበረሰቡ ለማህበረሰቡ በሚል እሳቤ ነው። የሚመራውም የሚደገፈውም በማህበረሰቡ ነው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 31 የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች በስርጭት ላይ ይገኛሉ። ስምንቱ ደግሞ ወደስርጭት ለመግባት በዝግጅት ላይ ናቸው የሚሉት አቶ ደሴ፤ ማህበረሰቡ በሚችለው ቋንቋ ተደራሽ የሚሆኑና እስከታች ድረስ በመውረድ በሀገራዊ ሚዲያዎች ሽፋን የማያገኙ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ በመሆናቸው ከሌሎች መገናኛ ብዙኃን ይለያሉ ብለዋል።
የአካባቢ አስተዳደርና ማህበረሰቡ በጋራ የሚያስተዳድሩት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደገፉና ለልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚቋቋሙ የማህበረሰብ ሬዲዮ አይነቶች ተጠቃሽ ናቸው። ለማህበረሰቡ ቅርብ እንደመሆናቸው መጠን የዜጎችን አብሮ የመኖር እሴትና ሰላም ከማጽናት አኳያ ከፍተኛ ሥራ መሥራት የሚጠበቅባቸው በመሆኑ የጀመሩትን ጉዞ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለባቸው ዴስክ ኃላፊው ያስገነዝባሉ።
“በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 272 የሚደርሱ መገናኛ ብዙኃን ይገኛሉ። እነኝህም 60 ቋንቋዎችን ለስርጭት የሚጠቀሙ ሲሆን፤ ከእነዚህም አብዛኞቹ ተግባራዊ የሚደረጉት በማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ነው” የሚሉት ዴስክ ኃላፊው፤ ጣቢያዎቹ መረጃን ከማድረስ በዘለለ ለቋንቋና ባህል እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ ደሴ ገለጻ፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ለማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች በልዩነት የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል። በዚህም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የጋዜጠኞችን አቅም ለማጎልበት የሚረዱ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ የቁሳቁስ ድጋፎችን በማድረግ፣ አቅም ያላቸው ተቋማት ለጣቢያዎቹ ድጋፍ እንዲሰጡ በመገፋፋት እንዲሁም ጥሩ አፈጻጸም ላላቸው ጣቢያዎችም እውቅና በመስጠት ይደግፋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2017 ዓ.ም