የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሁሉም ክልል እና ከተማ አስተዳደር የሚገኙ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖችን በደንብና መመሪያ መሠረት በበላይነት ይመራል፣ ያስተባብራል አብሮ ለእግር ኳስ የሚበጁ ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ ከነዚህ ፌዴሬሽኖች መካከል አንዱ የሆነው የኦሮሚያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በየጊዜው በሀገሪቱ የተለያዩ የሊግ እርከኖች የሚሳተፉ ክለቦችን በማብቃት ይታወቃል፡፡ ሆኖም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የመጣው የክልሉ ጠንካራ ወካይ ክለቦች ተሳትፎ መዋቅር አስተዳደራዊ ችግር እንደሆነበት የክልሉ እግር ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በክልሉ በሚገኙ ፋብሪካዎች ስር ተደራጅተው ሲወዳደሩ የነበሩት ታሪካዊ ክለቦች ፈርሰው ስማቸውም እየተረሳ የመጣበትንም ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከነዚህም ታሪካዊ ክለቦች መካከል ሙገር ሲሚንቶ፣ ፊንጫ፣ ስኳር፣ ወንጂ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በቅርብ ጊዜ የኢትዮጰያ ፕሪሚየርሊግ ተሳተፊ ከነበሩና ከሊጉ ከወረዱት ክለቦች መካከል ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ሰበታ ከነማ፣ ጅማ አባ ቡና እና የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ሻምፒዮኑ ጅማ አባጅፋር ይጠቀሳሉ፡፡
የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፊሮምሳ ለገሠ፣ ክለቦች ሕዝባዊ መሠረት ባለመያዛቸውና በማዘጋጃ ቤት የተመሠረቱ በመሆኑ በስፋት እንደ ችግር የሚነሳው የበጀት እጥረት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ እንደ ኃላፊው ገለፃ፣ ለነዚህ ችግሮች ዋነኛው ምክንያት የመዋቅር፣ በተለይም ከወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር ተያይዞ የማቀናጀት ችግር ነው፡፡ ሃብትን በማቀናጀት ፕሮጀክቶች ላይ መሥራት፣ ተቋማትና ዪኒቨርሲቲዎችን በማሳመን ክለብ እንዲይዙ አለመደረጉም የቅንጅት ችግር ሆኖ መለየቱን ይገልጻሉ፡፡ ከሠላም አለመኖር ጋር በተያያዘ አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ጠንካራ ክለቦች መሳተፍ አልቻሉም፡፡ የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እራሱን ችሎ ለመቆም ቢቸገርም በየጊዜው ለሚገጡሙ ችግሮች መፍትሔዎችን እየሰጠ ግን ይገኛል፡፡
ፌዴሬሽኑ በዋናነት እያከናወነ ከሚገኘው ሥራዎች መካከል በከተሞች፣ በዞኖችና ወረዳዎች በተለያዩ ቡድኖችና እንዲሁም ክለቦች መካከል ውድድሮችን ማካሄድ ነው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ከባለሀብቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በስፋት ሲሠራ በቆየው ውድድር ተኮር እንቅስቃሴ ጥሩ ውጤት ማግኘቱም ተጠቅሷል፡፡ በተለያዩ የውድድር እርከኖች 90 ክለቦችን የሚያሳትፉ ውድድሮች ተካሄደዋል፡፡ በክልሉ የሚገኙ ታዳጊዎች በእግር ኳሱ እንዲሳተፉ ከማድረጉም በላይ በገቢ ምንጭ እራሱን እንዲችል የሚደረገው እንቅስቃሴ ከክለቦች በሚገኘው ገቢ እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚዘጋጁ ውድድሮች የሚሳተፉ ጥቂት ክለቦች እንዳሉ የሚገልጹት ኃላፊው፣ በከፍተኛ ሊግ 7 ክለቦች፣ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንድ ክለብ ብቻ ይገኛልም ይላሉ፡፡ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ክለቦችን በበጀት መደገፍና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም እንደ ክልል ግን ይሄ እየሆነ አይገኝም፡፡
በዚህም ክለቦች በየዓመቱ ከሀገር አቀፍ ውድድሮች በስፋት እየወረዱ ሲሆን በክልሉ የሚደረገው ድጋፍና ክትትል ዝቅተኛ እንደሆነም ያሳያል፡፡ ክለቦችን ከኦሮሚያ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ለማሳደግ ረጅም ጊዜና ከፍተኛ በጀት እየፈሰሰ ነው፡፡ የአስተዳደር ችግር እና የክለቦች ድጋፍ ድክመት ትልቁን ስፍራ የሚይዝ ነውም ይላሉ፡፡ አንድ ክለብ የሚኖረውን መዋቅር የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደሌለው የሚናገሩት አቶ ፊሮምሳ በሦስት ሰዎች ብቻ እንደሚሠራም ይገልጻሉ፡፡ በክለብ ደረጃ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተሠራ መዋቅር ከመሆን የዘለለና ሥራዎችን ለማሳለጥ፣ ክለቦች እንዲያድጉ የበጀት አጠቃቀሙን መከታተልና ሕዝባዊ መሠሰረት ለማስያዝ ትልቅ ችግር በመኖሩ ክለቦቹ ሲመረቱ ተቋም ሳይሆን ሰዎችን ይመስላሉ ባይ ናቸው፡፡ የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደመሆኑ በሀገር ደረጃ በሚወዳደሩ ክለቦች ውሳኔ ለመስጠት የሚቸገር ሲሆን ክለቦችን ለመርዳት ትልቅ ተግዳሮትም ሆኖ ይገኛል፡፡
ከእግር ኳስ መሠረተ ልማቶች ጋር በተያያዘ በክልሉ የሚገኙ ስታድየሞችን በማደስና ወደ ሥራ በማስገባት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውንም ይጠቁማሉ። ፌዴሬሽኑ በሰው ኃይል፣ በበጀት እና በቢሮ እራሱን የቻለ ባይሆንም ከክለቦች በሚገኘው ገቢ ዓመታዊ ውድድሮች ይካሄዳሉ። በዚህም የተነሳ መንግሥት በዓመት የሚያወጣውን 20 ሚሊዮን ብር መቆጠብ ተችሏል።
በክልሉ የሚገኙና ከዚህ ቀደም ክለብ የነበራቸው ተቋማትን መልሶ ክለብ እንዲይዙ ውይይት ማድረጋቸውን የሚያስታውሱት አቶ ፊሮምሳ ከበጀት እና በእግር ኳሱ ውስጥ ያሉ አሻጥሮችን እንደሚያነሱ ይጠቁማሉ። በተለይ እግር ኳሱ የሚጠይቀውን ከፍተኛ ሃብትና ተጫዋቾችን የመቀማማት ሁኔታን እንደ ምክንያት ያነሳሉ። ክለቦችንና ታዳጊዎችን ለመያዝ ያላቸው ፍላጎት አነስተኛ በመሆኑና ተጠሪነታቸው ለፌደራል መንግሥት እንደመሆኑ አስገዳጅ ክለብ ለማስያዝ አቅጣጫ መቀመጥ ይኖርበታል። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ብቻ ከ10 ዓመት ጀምሮ ያሉ ታዳጊዎችን አቅፎ እያሠለጠኑ ይገኛሉ። እንደነፊንጫ አይነት ድርጅቶች በአዲስ መልኩ የተደራጁ ሲሆን አዳዲስ የተከፈቱ ፋብሪካዎችን አንድ ላይ በማደራጀት ክለብ ለማስያዝ መታቀዱንም ያብራራሉ።
በተጨማሪም የተለያዩ የእግር ኳስ ባለሙያዎችን የማብቃት ሥልጠና፣ ታዳጊዎች ላይ መሥራት እና በክልሉ የእግር ኳስ ስፖርት በኅብረተሰቡ እንዲታወቅ፣ ድጋፍ እንዲያገኝ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ አብዛኞቹ ክለቦች በከተማ አስተዳደር፣ በዞን እና ወረዳ ሲመሠረቱ ወጣቶችና ሴቶችን አካተው እንዲመሠረቱ ሲሠራ መቆየቱንም ይጠቁማሉ፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም