የትምህርት እርከኖች የመለያየታቸውን ያህል የትምህርት ፕሮግራሞችም ተመሳሳይ አይደሉም። የትምህርት ደረጃዎች አንድ እንዳልሆኑት ሁሉ የትምህርት አይነቶችም ልዩ ልዩ ናቸው። የትምህርት ተቋማትም እንደዛው የተለያዩ ናቸው።
እቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመሀል አዲስ አበባ፣ ስድስት ኪሎንና መነንን ቀኝና ግራ አድርጎ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ዋና ጊቢ በጀርባው ተደግፎ ፅድትና ደርበብ በማለት ተረጋግቶና ሰፋ ተደርጎ በተያዘለት ይዞታ ላይ “ተገማሽሮ” የሚገኝ የቤተ-ትምህርት አፀድ ነው።
ጽንሰቱን በ1923 ዓ.ም የማስተማር ተግባሩን ደግሞ በ1924 ዓ·ም ላይ አንድ ብሎ የሚጀምረው ይህ አንጋፋና ፀአዳ የትምህርት ተቋም ለመመሥረቱ ምክንያት ዛሬ እየሰጠ ያለው አገልግሎቱ ሲሆን፣ በዘመናት ሂደት፣ በኃይል በሚገለባበጡና ወንበር በሚወራረሱ ሥርዓቶች ምክንያት የአገልግሎት ዘመናቱ ወጣ ገባ እንዲሆኑ፤ የተመሠረተበት ዓላማም ዥንጉርጉር እንዲሆን ተገድዶ እየተንገዳገደም ቢሆን ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ይህ ተቋም እንደ ዓላማና አገልግሎቱ ሁሉ ስሙም በየሥርዓቶቹ ሲፋቅ፣ ሲሰረዝና ሲደለዝ የቆየ ሲሆን፤ ዛሬ ወደ መነሻ፣ ወደ ቀዳሚ የማንነት ስሙና ስያሜው ተመልሶ “እቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ለመሆን በቅቷል። ከእንግዲህም ላይመለስ የአሁን ማንነቱን እንደ ያዘ ይዘልቃል ተብሎ ይገመታል።
በአሁኑ ጊዜ ከመቸውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ የትምህርት ስብራት፣ ቅጭትና ውልቃት የደረሰ ሲሆን፣ ከማንም በላይና በፊት እነዚህን የትምህርት ውልቃት፣ ቅጭትና ስብራት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በመጠገን በኩል ሀገሪቷን እየታደጉ ያሉት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ናቸው።
የባለፈው ዓመትን “አስደንጋጭ” የ”ወደቁ” ዜናን ትተን የዘንድሮውን “5 ነጥብ 3 ብቻ አለፉ”ን ይዘን የሀገሪቱን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ውጤት ብንመለከት ጉዳዩ ወደ ለየለት ዜሮ (0% አለፉ) እየተምዘገዘገ እንዳይወርድ ታኮ ሆነው የያዙት በሀገሪቱ የሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ስለመሆናቸው ነው እየተነገረ ያለው። ተሞክሮውን ያካፍለን ዘንድ ከጎበኘነው “እቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ሆነ ማብሪሪያ ከሰጡን ርእሰ መምህርት የተገነዘብነው ይህንኑ እውነት ነው።
ከፈረሱ አፍ እንዲሉ፣ በመላ ሀገሪቱ ከ50 በላይ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ላይ ነኝ በሚለው፣ በራሱ በትምህርት ሚኒስቴር እንደተገለፀው፣ በሀገሪቱ የሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ አሳልፈዋል። የዛሬው እንግዳችን የሆኑት የእቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህርትም የነገሩን አስደሳች ዜና ቢኖር ተመሳሳይና ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ ማሳለፋቸውን ነው።
የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤትን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለፁት ለሀገር አቀፍ ፈተና ከተቀመጡ 674 ሺህ 823 ተማሪዎች ውስጥ 36ሺህ 409 ወይም 5 ነጥብ 4 በመቶ የማለፊያው ውጤት (በተፈጥሮ ሳይንስ 28ሺህ 158 ወይም 9 በመቶ በማህበራዊ ሳይንስ 8ሺህ 251 ወይም 2 በመቶ) ነው ያገኙት። የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ በ9 ሺህ 114 ተማሪዎች ብልጫ አለው፡፡
በዚህ ዓመት ሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ከአምናው በተሻለ ተማሪዎችን ማሳለፋቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ 1 ሺህ 363 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ አለማሳለፋቸውንም አልሸሸጉም። እውነቱም ይህ ነው።
እዚህ ላይ፣ ትምህርት በሀገራችን የተጋረጠበትን አደጋ ለማሳየት ይቻል ዘንድ፣ በተለያዩ ክልሎች ባሉ ችግሮች ምክንያቶች ከ5ሺህ 500 በላይ ትምህርት ቤቶች የመማር-ማስተማር ሥራቸውን ከማከናወን ውጪ መሆናቸውን፤ በአማራ ክልል ብቻ በ2016 ዓ.ም ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳልሆኑ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።
ሌላው እውነት፣ 1 ሺህ 363 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ አለማሳለፋቸው እንዳለ ሆኖ ሁሉም አዳሪ ትምህርት ቤቶች ያስፈተኗቸውን በሙሉ አሳልፈዋል። እኛም ጉዳዩ ምን ይሆን?፣ የስኬቶቻቸው ምንጭ ምንድን ነው?፣ የተማሪዎቹስ ጀግንነት መሠረቱ ከምን የመጣ ነው? የሚለውን ይዘን፤ ከላይ ወደ ጠቀስነው አዳሪ ትምህርት ቤት በማቅናት በትህትናቸው፣ ገራገርነታቸው፣ የሥራ ትጋታቸውና አመራር ችሎታቸው በብዙዎች እውቅናን ያገኙትን፣ ርእሰ መምህርት ሃና ፀጋዬን አነጋግረናል።
ተማሪዎች ውጤታማ ሲሆኑ ማየት ከሚያስደስታቸው ርእሰ መምህርት ሃና ፀጋዬ ጋር የነበረንን ቆይታ የጀመርነው ከቀላሉ ሲሆን፣ እሳቸውም ይህ ትምህርት ቤት በ2012 ዓ·ም ወደ ነበረበት አዳሪ ትምህርት ቤትነት እንደ ተመለሰ፣ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ከአዲስ አበባና ዙሪያዋ አካባቢዎች ከሚገኙ የመንግሥትና የግል ትምህርት ተቋማት በ8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ከፍተኛ ነጥብ (ከ80 በላይ) ያመጡ ሴት ተማሪዎችን እየተቀበለ እንደሚያስተምር፤ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሚኒስትሪ ማስፈተን መጀመሩን ተከትሎ የ7ኛ ክፍል ተማሪዎችን መቀበል መጀመራቸውን ያስረዳሉ። ከሌሎች መሰል ተቋማት በላይ 624 ተማሪዎችን መቀበላቸውንም ይናገራሉ።
በመምህራን በኩል ያለውን አጠቃላይ ይዞታን በተመለከተም ጠይቀናቸው “መቸም ያለ መምህራን ጥንካሬ ይህንን የመሰለ ውጤት አይመጣም” ካሉ በኋላ መምህራኑ በሙሉ ልጆቹ ሙሉ ለሙሉ ማለፍ ያለባቸው መሆኑ ላይ መግባባት ላይ ደርሰው የሚሠሩ ናቸው። ቁርጠኝነት አላቸው። ደሞዛቸው እንደማንኛውም የመንግሥት ትምህርት ቤት መምህራን ደሞዝ፣ ተመሳሳይ ነው። የተለየ ጥቅም አያገኙም። ነገር ግን ቅዳሜ፣ እሁድ፤ በምሽት፣ በትርፍ ጊዜያቸውም ጭምር ተማሪዎቻቸውን በማገዝ ነው የሚያሳልፉት። ደከመኝ አያውቁም፤ መሰልቸት አይታይባቸውም። የብቃታቸው ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ እየተማሩም አሉ›› ሲሉ ርእስ መምህርቷ ገልፀዋል።
ተማሪዎቻቸውን ከወላጆች ፈርመው እንደሚቀበሉና ሲወጡም አስፈርመው እንደሚሸኙዋቸው፤ ወላጆች የትምህርት ቤቱን ሕገ-ደንብ ጠንቅቀው እንደሚያውቁ የሚናገሩት ርእስ መምህርት ሃና፤ ተማሪዎቹ ልጆች መሆናቸውንና በተለይ ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ መቀበል ከተጀመረ ወዲህ በእድሜያቸው ልጆች የሆኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እየገቡ እንደሆነ ይናገራሉ። ስለዚህ ከፍተኛ አያያዝና ጥንቃቄን የሚፈልጉ መሆናቸውንና አያያዛቸውም የወላጅ ያህል መሆኑን ይጠቁማሉ።
ግንኙነታችን ቤተሰባዊ ነው። ከአመጋገብ ጀምሮ አስፈላጊው እንክብካቤና ጥንቃቄ ይደረግላቸዋል። ትኩረታቸው ትምህርትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲሆን ነው ሥራዎች የሚሠሩት። እርስ በርሳቸው ይግባባሉ። የጋራ ሥራዎች ስላሉዋቸው አብሮነታቸው ጠንካራ ነው። በማናቸውም ጊቢ ውስጥ በሚከናወኑ ተግባራት ተሳትፏቸው ያልተገደበ ነው። ክሊኒክ አለ። መዝናኛዎች አሏቸው። ሱቅ አለ። ፀጉር ቤት አላቸው። በተቻለ መጠን ምንም እንዳይጎድልባቸውና ሙሉ ትኩረታቸው ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲሆን ነው እየተደረገ ያለው።
የትምህርት ግብዓትን በተመለከተም ቤተ ሙከራና ቤተ መጻሕፍት እንዳሉ ሆነው፣ ከአይሲቲ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በተሟላ መልኩ ቀርበውላቸዋል። በፕሮግራምና በመምህራን ክትትልና ድጋፍ ተግባራቸውን ያከናውናሉ። ወደ አልተፈለጉ ማህበራዊ ሚዲያዎች በመሄድ እንዳይዘናጉ ይደረጋል። እንደ ሁኔታው እስከ ምሽቱ 4:00 እና 4:30 ድረስ እንዲጠቀሙ ፕሮግራም ተይዞላቸው ነው የሚሠሩት። ለአንድ ክፍል ሁለት ሁለት መምህራን በአማካሪነት ተመድበውላቸው የምክር አገልግሎት ያገኛሉ። ተማሪዎቹ በእውቀት ብቻ ሳይሆን በመልካም ሥነምግባርም ታንፀው ይወጡ ዘንድ ነው ታስቦበት እየተሠራ ያለው።
ቢሯቸው ውስጥ በነበረን ቆይታ ወቅት ከተመለከትነው ተነስተን ለወይዘሮ ሃና “ይሄ ሁሉ ዋንጫ ምንድን ነው፤ ከየትና እንዴትስ ተገኘ?” ብለናቸው ነበር። ርእሰ መምህርት ሃና እንዳጫወቱን ከሆነ ትምህርታቸውን በሁለት ስትሪም (ማህበራዊ እና የተፈጥሮ ሳይንስ) የሚከታተሉት ተማሪዎቻቸው ከመደበኛው ትምህርት ባሻገር በሌሎች በርካታና ደረጃቸው ከፍ ባሉ ተጓዳኝ ትምህርቶች ያሏቸው ተሳትፎ የላቀ ነው። በተለያዩ ሙያዎች (ለምሳሌ ህክምና) ከመሳተፍና የአፈፃፀም ሪፖርት ከማቅረብ በተጨማሪ፤ በከፍተኛ አመራርና ዲፕሎማሲ ተግባራት ላይ ያተኮሩ ክበባትና እንቅስቃሴዎች ውስጥ ይሳተፋሉ።
ዓባይን በሚመለከቱ መድረኮች ላይ ንቁ ተሳታፊዎች ናቸው። ከአቻ ተቋማት ጋር በምስለ ፍርድ ቤት ውድድሮች አሸናፊዎችና ተሸላሚዎች ናቸው። በሁሉም ተሳትፏቸው መስለው ሳይሆን “ሆነው” ነው የሚሠሩት። የዋንጫዎች ባለቤቶች ለመሆን ያበቃቸውም ይኸው አቅምና ችሎታቸው ነው።
በምስለ ፍርድ ቤት ተሳትፏቸው በአፍሪካ ደረጃ ሳይቀር ሀገራትን ወክለው ሁሉ ይሠራሉ። የተመደቡበትን ዘርፍ ሳያቅማሙ መቀበል፤ ተቀብሎም አስፈላጊና ሙሉ ዝግጅት (በተለይም በንባብ) በማድረግ ማቅረብ የተካኑት ክሂል ነው። ለምሳሌ ማሊን ወክላ የምትከራከር ተማሪ ከማቅረቢያ ጠረጴዛና መቀመጫ ወንበሯ ጀምሮ ከፊት ለፊቷ “ማሊ” የሚል ጽሑፍ ያለበትና በትክክል የማሊ “ተወካይ” ሆና ነው የምታቀርበው ሲሉም ርእሰ መምህርቷ ነግረውናል። ሁሉም በብሔራዊ ፈተናው ለማለፋቸው እነዚህ ተግባራቶቻቸው ሁሉ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
እንደ ተቋሙ አስተዳደር፣ ከመማር-ማስተማር ሥራው በተጓዳኝ ሌሎች ሥራዎች እየተሠሩ ካሉ በሚል ላነሳንላቸው ሃሳብም፣ ልጆች በምግብ እንዳይጎዱ፣ ጤናቸው እንዲጠበቅ፤ ንፅህናቸው እንዳይጓደል ወዘተ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ። ልጆች ወተት እንዳያንሳቸው የወተት ላሞች እናረባለን፤ ዶሮ ርባታ አለ፤ ተሸጠው ገቢ ያስገኙ ዘንድ ታስቦ እየተሠራ ያለ አሳማ እርባታ አለ። ሌሎችም የሚሠሩ ሥራዎች አሉ ሲሉ አስረድተውናል፤ ሥራውንም አንድ በአንድ አስጎብኝተውናል።
የተማሪዎችን መውደቅ በተመለከተ ጥልቅ ኀዘናቸውን የሚገልፁት፣ በተለይም ከራሱ ከተማሪው፣ ከወላጅ፣ ከመምህራን፤ እንዲሁም ከሀገርና አጠቃላይ የትምህርት ባለ ድርሻ አካላት አኳያ ሲታይ “በጣም የሚያሳዝን” መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ሃና “ዋናው ጠንክሮ መሥራት ነው፤ ከተሠራ የማይለወጥ ነገር የለም። ሁሉም ነገር በሥራ ይለወጣል። ይህ ደግሞ ታይቷል። ያለ ሥራ ግን ምንም የሚሆን ነገር የለም። በማቀድ ብቻ፣ በመናገር ብቻ የሚሆን ነገር የለም።” የሚሉት ርእሰ መምህርት ሃና “ያጋጠመንን የትምህርት ስብራት ለመጠገንና የትምህርት ሥርዓታችንን ለማሻሻል ቁርጠኝነት ያስፈልጋል።” ሲሉም ነው በአፅንኦት የተናገሩት።
እንደ እሳቸው አገላለፅ “ከተሠራ ለውጥ ማምጣት የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም። የሁሉም ነገር ውጤት በተሠራው ልክ ነውና ከተሠራ ለውጥ የግድ ይመጣል። እኛም የዘንደሮው ሙሉ ለሙሉ የማሳለፋችን ምስጢር መሥራታችን ብቻ ነው። ባቀድነውና ባለምነው መሠረት ሠራን፤ ውጤት አገኘን።” የሚያስፈልገው በቁርጠኝነት ስትራተጂዎችን ነድፎ መሥራት ብቻ ነው።
ርእሰ መምህርቷ እንደሚሉት ብዙ ነገር ተደርጓል። እየተደረገም ነው። አዲስ ተቋም እንደ መሆኑ መጠን የተጀመሩ የማስፋፊያ ሥራዎች አሉ፤ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ የትምህርት ተቋማትና ወላጆች ጋርም በቅርበት ለመሥራት እየሞከርን ነው። ለልጆች የአንድ ዓመት የንፅህና መጠበቂያ የሚሆን ሞደስ ሁሉ ለማግኘት ችለናል። የጊቢ ውስጥ ኮብልስቶን የተነጠፉ መንገዶችን የሠሩልን አንድ ግለሰብ ናቸው። የወተት ላሞች የገዙልንም አሉ። ደጋግመን ስናንኳኳ የከፈቱልን አሉ። ይህንን፣ ከባለ ድርሻዎች ጋር አብሮ የመሥራቱን ጉዳይ አጠናክረን የምንቀጥለው ይሆናል፤ እንደሚተባበሩንም ተስፋ አለኝ። እዚህ ላይ ቢደረግ የምለው ከመምህራን አኳያ ነው።
መምህራን ሙሉ ጊዜያቸውን ለሥራቸውና ለልጆቹ የሰጡ ናቸው። እስከ ምሽቱ 2 ሰአት ከ30 ድረስ፤ አንዳንዴም ከዚያ በላይ ከልጆች ጋር፤ ልጆቹን ሲያግዙ ያመሻሉ። የብዙዎቹ ቤታቸው ሩቅ ነው። ይመሽባቸዋል። ትራንስፖርት ከፍለው ነው የሚሄዱት። ከሌሎች ችግሮችም አኳያ እንደው፣ እዚሁ ጊቢ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ተሠርቶ እዚሁ የሚኖሩበት ሁኔታ ቢፈጠር የተሻለ ይሆናል። በማለት ከባለሙያነታቸውና ሃላፊነታቸው አኳያ “ቢደረግ ጥሩ ነው” ያሉትን ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።
የእቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህርት ሃና ፀጋዬ፣
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም