ኢትዮጵያ የብዙ ሺህ ዓመታት የዳበረ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ባለቤት ፣ ከሁሉም በፊት የነቃች፣ የሰው ዘር መገኛና የሰው ልጆች ስልጣኔ መነሻ እርሾን የጣለች አኩሪ ታሪክ ያላት ታላቅ ሀገር ነች ኢትዮጵያ። ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶቿ መካከል አንዳንዶቹ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከምትኮራባቸው ድንቅ እሴቶቿ መካከል አንዱ የኢሬቻ በዓል ነው። ኢሬቻ ጭጋጋማው የክረምት ወቅት አልፎ ብርሃን ሲፈነጥቅ፤ ምድር በልምላሜና በአበቦች ስትፈካ፣ ከብቶች ጉንጫቸውን የሚሞላ ለምለም ሳር ሲግጡ፣ ሰዎች አዝመራቸውን እያዩ በተስፋ ሲደሰቱ፣ የሰማይ ነጎድጓድ ጋብ ሲልና ወንዞች ጎድለው ሰዎች ከወንዝ ማዶ እየሄዱ የናፈቋቸውን ዘመዶቻቸውን ሲጠይቁ የሚከበር በዓል ነው፡፡ ሰዎች አስፈሪውን የክረምት ወቅት አልፈው ለዓይን ደስ ወደሚለው የመጸው ወቅት የሚሸጋገሩበት በመሆኑ በተለይም የኦሮሞ ሕዝቦች ለዚህ ያደረስከን ፈጣሪ (ዋቃ) ምስጋና ላንተ ይሁን በማለት ይህን የሽግግር ወቅት ኢሬቻ በሚባል የምስጋና በዓል ያከብሩታል፡፡
ኢሬቻ ፈጣሪ የሚመሰገንበት ታላቅ ሥነ ሥርዓት በመሆኑ ሰዎች ከጸብ እና ከቂም ነጽተው፤ የፍቅር፣ የወንድማማችነት፣ የሰላም የአንድነትና የመከባባር መንፈስ ተላብሰው የሚያከብሩት በዓል ነው። በኢሬቻ በዓል ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ራሱን ብቻ ሳይሆን መላውን የሰው ልጅ ወክሎ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ስላደረገው መልካም ነገር ሁሉ ምስጋና ያቀርባል፤ በቀጣይም ስለሰላሙና ደኅንነቱ ፈጣሪውን (ዋቃን) ይለምናል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናትና ምርምሮችን ያደረጉት የኦሮሞ ባሕልና ታሪክ ተመራማሪና ፀሐፊ ድሪቢ ደምሴ ፣ ኢሬቻ ማለት ኦሮሞ ለምለም ሳርና አበባ ይዞ ፈጣሪን የሚያመስግንበት ክዋኔ ሲሆን በሐይቅ ፣ በወንዝ ፣ በምንጭ ወይም በውሃ ዳርና በተራራ ብቻ የተወሰነ ግን አይደለም። ኢሬቻ አንድነት፣ ፍቅር፣ ይቅርታና ምስጋና የሚፈፀምበት የኦሮሞ ማኅበረሰብ የይቅርታና የመልካም ምኞት መግለጫ እሴት ነው ሲሉ ይገልጹታል።
ኢሬቻ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ በዓመት ሁለት ጊዜ ይከናወናል። የመጀመሪያው በበልግ ወቅት በተራራ ላይ ወጥቶ አምላክን የሚያመሰግንበትና ዝናብ የሚለማመንበት ሲሆን ይህም ቱሉ ኢሬቻ ይሰኛል። ኢሬቻ በተለያዩ ስያሜዎች ይጠራል፤ በቱለማዎች ኢሬቻ፣ በመጫዎች ኢሬስ፣ በሐረርጌ ኢሬሳ፣ እንደሚባልና ሌሎች ስያሜዎችም እንዳሉት ይገልጻሉ።
ይሁንና በተለያዩ ስያሜዎች ይጠራ እንጂ የሚፈጸሙት ሥርዓቶች ግን አንድ ዓይነት ናቸው። የኦሮሞ ማኅበረሰብ የይቅርታና የመልካም ምኞት መግለጫ እሴት የሆነው ኢሬቻ በውስጡ ከሚገኙ እሴቶች መካከል ሀገራዊ አንድነትን ለማምጣት፣ እርቅ ለማውረድ፣ ሰላምን ለማምጣት ከፍተኛ ቦታ አለው። እነዚህን የኢሬቻ መልካም ዕሴቶች ከሀገራችን ነባራዊ አንጻር መመልከት ያስፈልጋል።
ሰላም እና ኢሬቻ
ኢሬቻ ለፈጣሪ (ዋቃ) የሚቀርብ የምስጋና ሥርዓት ሲሆን ለኢሬቻ ወደ መልካ የሚሄዱ ርጥብ ሳር በእጃቸው ይዘው የኢሬቻ ሥርዓትን ከመከወናቸው በፊት ሦስት ጥያቄዎችን መመለስ አለባቸው። የገዳ አባቶች “በመካከላችሁ ሰላም አለ?” “ለፈጣሪስ ሰላማዊ ናችሁ?” “ከተፈጥሮስ ጋር ሰላም ናችሁ?” ብለው ይጠይቃሉ። ወደ መልካ ለኢሬቻ የሄደው የበዓሉ አክባሪም መልካውን በርጥብ ሣር ከመንካቱ በፊት ሰላም ነው ብሎ ይመልሳል። ምክንያቱም ሰላም ማውረድ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው።
ቂምና በቀል፣ አለመግባባትና ጥላቻ ያለው ማንኛውም ግለሰብ ጥላቻውን ሳይሽር፣ እርቅ ሳያወርድ፣ የገደለ ሳይክስ፣ እጁ ንፁህ ያልሆነ ግለሰብ ወደ ኢሬቻ ክብረ በዓል አይሄድም። ኢሬቻ ከመድረሱ በፊት አባ ገዳዎች በየአካባቢያቸው፤ በየደረጃው ባለው መዋቅር ያሉትን ችግሮች ይፈታሉ። የተጣላውን ያስታርቃሉ፤ የበደለ እንዲክስ ያደርጋሉ። ይህም የሚሆነው ኢሬቻ ካለው እሴት መካከል ሰላምና እርቅ አንዱና ትልቁ ስለሆነ ነው። ስለዚህ በኢሬቻ በዓል ሰላም ይታወጃል፤ ይወደሳል። በኢሬቻ በዓል ስለ ሰላም ይሰበካል።
ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት፣ ከሰፊው ሕዝብ፣ ከፈጣሪና ከፍጡር ጋር በሰላም አብሮ መኖር እንደሚገባ ይታወጃል። ኦሮሞ በአባባሉ ‹‹Yoo namni walitti araarame, Waaqnis namaaf araarama›› ‹‹ሰው እርስ በርሱ ከታረቀ እግዚአብሔርም ሰዎችን ይታረቃል›› የሚለው ለዚህ ነው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ነባራዊ ሁኔታ ፍጹም መድኃኒት ነው። ሀገራችን ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ የጭንቅ ጊዜያትን አሳልፋለች። በብሔርና በኃይማኖት ሰበብ ልዩነት እየፈጠሩና እያሰፉ ሀገር ለማፍረስ በሚጥሩ እኩይ ኃይሎች ተፈትናለች።
ሰላሟን የማይፈልጉ ኃይሎች ቀዳዳዎችን እየፈለጉ ሊያፈርሷት ሞክረዋል። ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን በመሳሪያ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሕዝብን ሰላም እየነሱ ይገኛሉ። በሀገራችን ሰላምን ለማጽናት ጥረት ከማድረግ ቦዝኖ የማያውቀው መንግሥት ለእነዚህ ኃይሎች ተደጋጋሚ የሰላም አማራጭ በማቅረብ ጥሪ አድርጓል።
ይህም መሳካት የቻለው በጥቂቱ በመሆኑ ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ ወጥቶ ለመግባት አስጊ ሆኗል። ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለመሥራት እየተቸገሩ ይገኛሉ። በሕዝብ ስም በሚነግዱ ሽፍቶችና የታጠቁ ኃይሎች የሚፈጸሙት የመታገት፣ የመዘረፍ፣ የመገደል ወንጀሎች ተደጋግመው የሚሰሙ ሆነዋል። ሰዎች ሰላምን የሚናፍቁ ስለመሆናቸውም በተለያዩ ሁኔታዎች ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተፈጠረን አንድ ባሕላዊ የተማጽኖ ሥነ ሥርዓት ማስታወስ ይገባል።
በሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ሰላም ናፋቂዎች እንደ በሬ ቀምበር የተሸከሙ ወጣቶች፣ የተለጎሙ ፈረሶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች በአደባባይ ወጥተው ስለ ሰላም ሲማፀኑ ታይተዋል። ይህ ዓይነት ትዕይንት የኦሮሞ ማህበረሰብ ካሉት ባሕላዊ እሴቶች አንዱ ነው። ማህበረሰቡ እንደዚህ ዓይነት ተማጽኖ የሚደረገው ለፈጣሪ ብቻ ነው።
ከፍተኛ የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት፤ ዝናብ ሲጠፋ፣ ድርቅ ሲበረታ፣ የበሽታ ወረርሽኝ ሲከሰት እና መሰል የተፈጥሮ ፈተና ሲበዛም ይደረጋል። አሁን ግን ዝናብ አልጠፋም። ድርቅም አልተከሰተም። የበሽታ ወረርሽኝም አልታየም። ስለዚህ ይህ ልመና እና ተማጽኖ ለፈጣሪ አይደለም፤ ይልቁንም ልመናው እና ተማጽኖው እየቀረበ ያለው ለሰው ልጅ ነው።
ለራሱ ልጆች በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ማህበረሰቡ መሬቱን አርሶ መብላት አልቻለም። ገበያ ሄዶ መሸጥ መግዛት ቅንጦት ሆኖበታል። ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አልቻለም። የታመመ ሰው ሆስፒታል የመሄጃው መንገድ ጠፍቶታል፡፡ የሞተ ሰው የቀብር ወግ አጥቷል፡፡ አባቶችና እናቶች በገዛ ልጆቻቸው ለስቃይ ተዳርገዋል፤ ሕፃናት በገዛ ወገኖቻቸው በሚደርስባቸው በደልና እንግልት ምነው ባልተፈጠርን ብለዋል፡፡
ይህ በጠራራ ፀሐይ ጨለማ የዋጠው ማህበረሰብ በሬዎቹን እና ልጆቹን በቀንበር አድርጎ፣ ፈረሶቹን በልጓም አውሎ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ወጥቶ የገዛ ልጆቹን እየተማጸነ ይገኛል። ጦርነት እንዲቆም፣ ያለው አለመግባባት በንግግርና በእርቅ ተፈትቶ በሰላም መኖር እንዲፈቀድለት እስከ መማጸን ደርሷል።
መሰል ችግሮች በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ይከሰታሉ። ይህ የሚያሳየው የኢሬቻ ታላቅ እሴቶች ከመተረክ ባሻገር በተግባር መኖር እንደሚያስፈልግ ነው። እንደ ኢሬቻ በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘን በመጓዝ መሰል ችግሮችን መሻገር ይኖርብናል።
አንድነትን ከኢሬቻ
ኢሬቻ የአንድነት በዓል ነው። ሴት ወንድ ሳይል፤ ሀብታም ከድሃ ሳይለይ ሁሉም በአንድነት ኢሬቻን ያከብራል። በኢሬቻ አንድነት እንጂ ልዩነት ቦታ የለውም። እንደ ኢሬቻ መርህ በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዞ መጓዝ ቢቻል በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው ዓይነት ችግር ሊኖር አይችልም ነበር። ማህበረሰቡ በገዛ ልጆቹ ሰላሙን አጥቶ አርሶ እንዳይበላ፤ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ፣ ነግዶ እንዳያተርፍ እንቅፋት ሊሆኑበት አይችሉም ነበር።
ስለሆነም እኛ ኢትዮጵያውያን ከእጃችን የወጣውን ሰላም ለመመለስ የኢሬቻ እሴት የሆነውን አንድነት መሳሪያ አድርገን በመጠቀም የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶችን ልንመክት ይገባል። ለዚህ ደግሞ እጅ ለእጅ ተያይዘን ጥላቻን አስወግደን ይቅርታን አስቀድመንና ፍቅርን አንግበን ኢትዮጵያን ከማማዋ ላይ ለመመለስ መጣር ይኖርብናል።
ኢትዮጵያውያን ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፤ ከመጠፋፋት ይልቅ መደጋገፍን ፤ ከማፍረስ ይልቅ መገንባትን መርሆዎችን ከኢሬቻ መማርና መተግበር ያስፈልገናል። ሀገራችን በተለያዩ ዘርፎች የተጀመሩ የልማት ስኬቶች ማስመዝገብ ችላለች። ነገር ግን የውጭ እና የውስጥ ጠላቶች ተቀናጅተው ጅማሮዋን ለማክሸፍ የሚደረጓቸውም ጥረቶች አሉ።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት በተባበረ ክንድ በመጓዝ ሴራውን ማክሸፍ እና ጅማሮው በማስቀጠል ጉዞውን ወደ ጠንካራ ብልጽግና እንዲደርስ ማድረግ ያስፈልጋል። ኢሬቻ ከጨለማ ወደ ብርሃን የመውጫ ምልክት በመሆኑ፤ እነዚህ ጨለማን አመላካች የሆኑ ችግሮች በአንድነት አሸንፈን ወደ ብርሃን መሻገር ይኖርብናል።
ኢሬቻን በተግባር
የኢሬቻ በዓል ሲከበር ያለፈው ጎርፍ አልፎ በአዲስ ውኃ፣ ደረቁ ሳርም ረግፎ በአዲስ ለምለም ሳር ነው። ያለፈው ይበቃል የሚል ነው መልዕክቱ። እውነት ነው ያለፈው ይበቃል። የደረቁ ሳሮችንና የደፈረሱ ጅረቶች በቃችሁን ብለን በአዲስ ለምለም ሳር በዓሉን እናከብረዋለን። ነባሩ ምድር አዲስ ሳር ያበቅላል። አዲስ የጠራ ምንጭ ኩልል ብሎ ይወርድበታል። ኢትዮጵያም ከላይ የተጠቀሱት ፈተናዎችን አልፋ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድትሸጋገር የኢሬቻ ዕሴቶች ያስፈልጓታል።
ስለዚህ የኢሬቻን ትውፊት እና ዕሴቶች በመላበስ ሀገራችን ከጦርነት፤ ከግጭት፤ ከአለመረጋጋት ተላቃ ሰላሟ የተረጋገጠባት፤ ሰዎች በሰላም ወጥተው የሚገቡባት፤ አርሰው የሚበሉባት፤ ነግደው የሚያተርፉባት ምቹ መኖሪያ እንድትሆን ሕዝብና መንግሥት ቃል የሚገቡበት ዕለት ሊሆንም ይገባል። የኢሬቻ ታላቅ እሴቶች ከመተረክ ባሻገር በትክክል በመኖር፤ ልክ እንደ ኢሬቻ ሁሉ ጨለማው አልፎ በብርሃን መተካት እንችላለን።
ከሁሉም በላይ የኢሬቻን በዓል በዓመት አንድ ጊዜ በአደባባይ ማክበር ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ኑሯችን መተርጎም ይኖርብናል። ስለዚህ አያት ቅድም አያቶቻችን ያወረሱንን ባሕል ከማክበር ባለፈ እንኑረው። በልካቸው እንገኝ። ሃይማኖታዊም ይሁኑ ባሕላዊ እሴቶቻችን ልካቸው ሰላም ፣ እርቅ፣ ይቅርታ፣ መከባበር ፣ መግባባት ፣ አብሮነት ፣ አንድነት እንጂ ጸብና አምባጓሮ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሰላም ተምሳሌት የሆነውን ኢሬቻን እንደ መርሆዎቹ የምንተረጉመው ከሆነ የየትኛውንም ሀገር እገዛና ድጋፍ ሳንፈልግ የእኛ ናቸው የምንላቸውን እሴቶች በማክበር ብቻ ሰላማችንን ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ብቻ አባቶቻችን ላወረሱንና ገንቢ ናቸው ለምንላቸው ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶቻችንን ቦታ እንስጥ፤ የአበውን አደራ እንጠብቅ ያን ጊዜ የጠፋው ሰላማችን በራችንን ሳያንኳኳ ዘው ብሎ ይገባል፡፡
መልካም የኢሬቻ በዓል!!!
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም