ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የደመቁበት- “ሆራ-ፊንፊኔ”

ዜና ሐተታ

የአዲስ አበባ ጎዳናዎች አዲስ ዓመት ‹‹ሀ›› ብሎ ከገባ ጀምሮ ባተሌ ሆነዋል፡፡ እንቁጣጣሽ ሥፍራውን ለመስቀል ሲለቅ አሁን ደግሞ ኢሬቻ በተራው ብቅ ብሏል፡፡ አዲስ አበቤዎችም እንግዳ እና በዓላትን ተራ በተራ በመቀበል ላይ ናቸው፡፡

ኢሬቻ ሚሊዮኖች የሚታደሙበት የአደባባይ በዓል ሲሆን ትናንት ከማለዳው ጀምሮ በርካቶች ወደመሐል ከተማ በቡድን ሆነው ሲተሙ ተስተውሏል፡፡ ባሕላዊ አልባሳት ለብሰው እና የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችን በማሰማት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ሽር ብትን እያሉ በዓሉን አክብረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጎዳናዎችም በአባገዳ ሰንደቅ ዓላማዎች በግራ ቀኝ ተሰቅሎባቸው ይታያሉ፡ ባሕላዊ አልባሳትን የሚሸጥባቸው የጎዳና ዳር ድንኳኖች፣ የመስተንግዶ ቤት ደጃፍ ቄጤማ ተጎዝጉዟል፡፡ የአስተናጋጆች ጥድፊያ እና የተስተናጋጆች ውክቢያ ሁሉ የበዓሉ አይረሴ ገጽታ ናቸው፡፡ በባሕላዊ አልባሳት ያጌጡ ወጣቶች እና ቆነጃጅቶች በከተማዋ አራቱም አቅጣጫዎች ባሕላዊ ውዝዋዜዎችንና ትዕይንቶችን እያሳዩ ነው። የአዲስ አበባ ሠላማዊ ድባብ የሚያስቀና ነው፡፡ ከምሽት እስከ ንጋት የበዓሉ ታዳሚዎች እየተንሸራሸሩባት ‹‹ያ! ዋቃ›› እያሉ የፈጣሪያቸውን ስም እየጠሩ ስለሠላም እየለመኑ ነው።

የበዓሉ ታዳሚዎች በማለዳው የኢሬቻ ሥነ-ሥርዓት በሚከናወንበት ‹‹በሆራ-ፊንፊኔ›› ተገኝተዋል።

በዓሉ ከሚከበርበት ‹‹ሆራ- ፊንፊኔ›› አቅራቢያ በመስቀል አደባባይ ያለው የወጣቶች አለባበስ እና አጋጌጥ የሰዎችን ቀለብ ይስባል፡፡ ከዚያም ባለፈ በዓሉ የብሔር ብሔረሰቦችን ደማቅ ቀለም የተላበሰ ሲሆን ከሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫ ተሳታፊዎች የበዙበት ነው፡፡

ወጣት ብሩክ መላኩ ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ነው፡፡ የመጣው ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከሐድያ ብሔረሰብ ሲሆን የዘንድሮ ኢሬቻ በዓል ልዩ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ወጣት ብሩክ እንደሚለው፤ በአትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ብሔረሰቦች በየራሳቸው የባሕል አልባስ አምረውና አጊጠው በመገኘታቸው ለበዓሉ ውበት ሠጥውታል፡፡

በዘመናዊ መንገድ በተሰሩ ባሕላዊ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች፣ ዜማና ጭፈራዎች የበዓሉን መልካም እሴት አጉልቶ ማሳየቱን ይገልጻል፡፡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች በበዓሉ መገኘታቸውን የሚገልጸው ወጣት መላኩ፤ ይህም ለበዓሉ ተጨማሪ ድምቀት አላብሶታል ብሏል፡፡

አንዱ ብሔር በሌላኛው ብሔር በዓል ላይ ተገኝቶ ማክበር መቻሉ ፍቅርን፣ ኅብረትንና ማኅበራዊ መስተጋብርን እንደሚያጠናክር ያስረዳል፡፡

በበዓሉ የሚስተዋሉ የተለያዩ አልባሳትም የየአካ ባቢውን ባሕል እንዲያቁና ለሌላ ብሔር ተወላጆች ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እንዳደረገም ይናገራል፡፡

ሌላኛው የበዓሉ ታዳሚ ወጣት በእምነት ዮሴፍ ስትሆን የመጣቸው ከሲዳማ ክልል ነው፡፡ የሲዳማ ባሕል ልብስን ለብሳና ብሔሩን ወክላ የኢሬቻ በዓልን በማክበሯ ትልቅ ደስታ እንደተሰማት ገልጻለች፡፡ በዓሉ ከአምናው የዘንድሮ ደማቅ መሆኑን ትናገራለች፡፡

የጋሞ ብሔርን በመወከል በበዓሉ የተገኘው አቶ ሞናዬ ሞናሴ በበኩሉ ወንድም ሕዝብ ከሆነው የኦሮሞ ብሔር ጋር በዓሉን ማክበር በመቻሉ ደስታ እንደተሰማው ይገልጻል፡፡

የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች የጋሞ ዘመን መለወጫ ‹‹ዮ›› መስቀላን በአንድ ላይ ማክበራቸውን አውስቶ ይህም በዓሉ የሕዝቦችን አንድነትና ሠላም ለማጠናከር የጎላ ሚና አለው ብሏል፡፡

ወጣት ዋሲሁን ለማ ይባላል ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወላይታ ብሔርን በመወከል የኢሬቻ በዓልን ለማክበር መገኘቱን ጠቅሶ፤ ኢሬቻ የሕዝቦች አብሮነት የሚጠናከርበት፤ የሰው ልጆች ሁሉ በእኩልነት እንዲታዩ እንዲሁም እንዲረዳዱ የሚያስተምር ነው ሲልም ያስረዳል፡፡

የእርቅ፣ የይቅርታ፣ የሠላምና የወንድማማችነት እሴቶች መገለጫ የሆነው የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በኢሬፈና ሥነ ሥርዓት አባገዳዎች፣ ሃዳ ስንቄዎች፣ ወጣቶችና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የበዓሉ ተሳታፊዎች በተገኙበት በትናትናው ዕለት ተከብሯል፡፡

በአማን ረሺድ እና ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You