ቀድመው የሚደርሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ ከሁለት ሺህ በላይ ኮምባይነሮች ዝግጁ ሆነዋል

– ከ29 ሺህ በላይ ሁለገብ መውቂያ መሣሪያዎችም ተዘጋጅተዋል

አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ በተለያዩ ቆላማ አካባቢዎች ቀድመው የሚደርሱ ስብሎችን ወቅታቸውን ጠብቆ ለመሰብሰብ ሁለት ሺህ 700 ኮምባይነሮች ዝግጁ መሆናቸውን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሰብሎችን በጊዜያቸው ሰብስቦ ለመውቃትም ከ29 ሺህ በላይ ሁለገብ መውቂያ መሣሪያዎች መዘጋጀታቸውን ተጠቁሟል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና መካናይዜሽን መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ እሸቱ ሁንዴ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ በተለያዩ ቆላማ አካባቢዎች ቀድመው የሚደርሱ ሰብሎችን ጊዜያቸውንና ወቅታቸውን ጠብቆ ለመሰብሰብ ከሁለት ሺህ በላይ ኮምባይነሮችና ከ29 ሺህ በላይ ሁለገብ መውቂያ መሣሪያዎች ዝግጁ ተደርገዋል፡፡

የግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦትን በማስፋፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ እየተሠራ ባለውም ሥራም በኢትዮጵያ የተለያዩ ቆላማ አካባቢዎች ቀድመው የሚደርሱ ሰብሎችን ዝናብ ጉዳት ሳይደርስባቸው ሰብስቦ ለመውቃት ሁለት ሺህ 700 ኮምባይነሮችና 29 ሺህ 400 ሁለገብ መውቂያ መሣሪያዎች ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል፡፡

በቆላማ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በወቅታቸው ጠብቀው እንዲሰበሰቡ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የሚያገኙበት መንገድን የማመቻቸት ማለትም የኮምባይነርና የሁለገብ መውቂያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የዝግጅት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ክልሎች እንዳላቸው እምቅ ሀብትና ለመካናይዜሽን አጠቃቀም የመልክዓ ምድር ምቹነት አኳያ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ እሸቱ፤ የልማት ድርጅቶችና ባለሀብቶች ያላቸውን ኮምባይነር ለአርሶ አደሮች በቀጥታ በኪራይ እንዲያቀርቡ የማድረግ ሥራም እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የግብርናውን ዘርፉን በቴክኖሎጂ ድጋፍ ምርታማነት ለማሳደግ እየተሠራ ቢሆንም ቴክኖሎጂን በማቅረብ በኩል እየተሠራ ያለው ሥራ በቂ አይደለም፤ ገና ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ13 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ለመካናይዜሽን ምቹ የሆነ መሬት አላት፤ ይህንንም በቴክኖሎጂ አስደግፎ በማልማት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ባለው ሥራ 19 ሺህ 692 ትራክተሮች፤ ሁለት ሺህ 700 ኮምባይነሮች፤ 29 ሺህ 400 ሁለገብ መውቂያ መሣሪያዎች ማቅረብ ማቻሉን አመልክተዋል።

የቀረበው ቴክኖሎጂ ካለው ፍላጎት አንፃር በቂ አይደለም ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ ሀገሪቱ ከ68 ሺህ በላይ ትራክተር፤ 20 ሺህ ኮምባይነር ማቅረብ ይጠበቅባታል፡፡ ይህን ፍላጎት ለማሟላትም ቴክኖሎጂዎችን ከቀረጥ ነፃ የማስገባትና በሀገር ውስጥ የማምረት ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

ቴክኖሎጂዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የጥራት መጓደል፤ የመለዋወጫ መሣሪያዎች እጥረት፤ በአገልግሎት ወቅት የሚከሰቱ ችግሮች፤ የኮምባይነሮች የዋጋ ውድነት የግብርና ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት ተግዳሮት መሆናቸውን ጠቅሰው ችግሮቹን ለመፍታት የመለዋወጫ መሣሪያዎች በስፋት እንዲገቡና ሀገር ውስጥ እንዲመረቱ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የቅድመ ምርት፤ የድረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው፤ ይህም ተጠናክሮም ይቀጥላል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You