አዲስ አበባ፡- የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ወንድማማችነትና እህትማማችነት የተንፀባረቀበት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። በዓሉ ትውፊቱን ጠብቆ በደማቅ ሁኔታ በመዲናዋ መከበሩን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመገናኛ ብዙኃን ትላንት በሰጡት መግለጫ፤ የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ትውፊቱን ጠብቆ በደማቅ ሁኔታ በመዲናዋ መከበሩን አስታውቀዋል፡፡ በዓሉ እሴቱን በጠበቀ መልኩ
እንዲከበር በማድረግ በኩል በርካታ አካላት አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይም በዓሉ በተረጋጋ መንገድ እንዲከበር አስተዋፅዖ ላደረጉ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ፎሌዎች፣ ለከተማዋ ነዋሪዎች፣ ለበዓሉ ታዳሚዎች፣ ለሆቴል ባለቤቶች፣ ወጣቶች፣ ለከተማዋና ለፌዴራል ተቋማት፣ ለፀጥታ አካላት፣ ለሠላም ሠራዊት፣ ለከተማዋ ወጣቶችና ለአመራሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የሆቴል ባለቤቶች ለበዓሉ ታዳሚያን የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችን በተገቢው ሁኔታ በማቅረብ ሲሠሩ እንደነበር ጠቅሰው፤ ለሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በዓሉ የኢትዮጵያውያንን አብሮነት በሚያጠናክር መልኩ በደማቅ ሁኔታ መከበሩን የተናገሩት ከንቲባዋ፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች በስፋት የተሳተፉበት እንደመሆኑ ወንድማማችነትና እህትማማችነት የተንፀባረቀበት ነው ብለዋል፡፡
የኢሬቻ በዓል የከተማዋ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በርካታ ማኅበረሰቦች ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም ከኦሮሚያ ክልል የሚታደሙበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሕዝቡ ይህንን ባገናዘበ መልኩ በአምስቱም የከተማዋ በሮች በፍጹም ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲሁም በመከባበር እና በአንዱ በዓል ሌላው ኢትዮጵያዊ ያለውን ደስታ በሚገልጽ መልኩ አስተናግዷል ብለዋል፡፡
ሆቴሎች በቂ አለመሆናቸውን በመገንዘብ በየቦታው ድንኳን በማዘጋጀት ሰዎች ማረፊያ እንዲያገኙ በማድረግ በኩልም ሕዝቡ ትልቅ ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል። በዓሉ ለከተማዋ ድምቀትን መጨመሩንና ከተማዋም በኮሪደር ልማት ደምቃ ልዩ ድባብ መፍጠሯን ጠቅሰዋል።
ከተማዋ በርካታ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ፣ ሕዝባዊ የሆኑ በዓላትን በአደባባይ እንደምታስተናግድ፤ ከዚህም አልፎ ሀገር አቀፋዊ፣ አሕጉር አቀፋዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችንም በማስተናገድ በኩል ትልቅ ልምድን ማዳበር እንደቻለች ገልጸዋል፡፡ ይህ ልምድ ብዙ እሴቶችን በውስጡ በማሳደግ በኩል እየዳበረ የመጣ ሁኔታን ያሳያል ነው ያሉት፡፡
ወንድማማችነት፣ እህትማማችነት፣ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ተቀብሎ ማስተናገድን በየጊዜው እየዳበረ የመጣና የከተማዋ ሕዝብም ይህንን በብቃት እየተወጣው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በዓላት ለሕዝቡ ትስስር፣ ለአንድነት መጠናከር ለብዝኃነት ትልቅ ድርሻ ያላቸው መሆናቸውን፤ ከዚህም የተነሳ ኢትዮጵያውያን ጠንካራ ሕዝብ ሆነው የሚቆሙ መሆናቸውን የሚያመላክቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዓላት ወንድማማችነትና እህትማማችነትን ማጠናከር ብቻ ሳይሆን፤ የቱሪዝም መስኅብ እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል። በዚህም ኢኮኖሚው እየተነቃቃ መሆኑን አንስተዋል። ለወደፊቱ በዓላትን እሴቶቻቸውን በማድነቅ ከማክበር ባሻገር በየአጋጣሚው ሁሉ ለቱሪዝም መስሕብነት መዋል እንዲችሉ ማድረግ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በዓላት ኢኮኖሚውን እንዲያነቃቁና ከድህነትና ከኋላ ቀርነት የሚያስወጡ እንዲሆኑ በሚገባ ልንጠቀምባቸው፣ ሕዝቡንም በዚህ መልኩ በማስተሳሰር ልንሠራ እንደሚገባ ትምህርት ተወስዷል ነው ያሉት፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም