ኢሬቻ የወርሐ መስከረም ፈርጥ ነው፡፡ መስከረም ካለ አደይ ኢሬቻም ካለምስጋና አይደምቁም፡፡ ኢሬቻ ከምድር መጨቅየት ንጣት፣ ከሰማይ ጉምጉምታ ፍካት፣ ከውሃ ማማዎችን ንጻት በሰብልና ቡቃያ፣ በእልፍ ከዋክብት የደመቀ፣ በተፈጥሮ አደይ እንዲሁም የኅብረ ቀለም ካባ የደረበ በዓል መሆኑን የበዓሉ ታዳሚዎች ይገልጻሉ፡፡
በኢሬቻ መላው የኦሮሞ ሕዝብ በሆታና እምቢልታ ውዳሴውን ለፈጣሪው ይቸራል፡፡ ሠላምን አሽትቶ አብሮነትን ይተነፍስበታል፡፡ ቂምን ሽሮ አንድነትን ያንጽበታል፡፡ እኩልነትና ፍትሕን አጋምዶ ሰውነት ያዋልድበታል፡፡ ይህ ታዲያ ያለ ልዩነት በአንድነት የሚከበር በዓል ነው፡፡
ለመሆኑ የኢሬቻ በተለይም የኢሬፈና ክዋኔ ባሕላዊ ትውፊት ትርጉሙ ምንድነው? ሲል ኢፕድ ያነጋገራቸው የሜጫ አባገዳ እና የኦሮሚያ አባገዳዎች ኅብረት ሰብሳቢ
አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ፤ ኢሬቻ የምስጋና እንዲሁም የተማጽኖ በዓል ነው፡፡ ኢሬፈና በኦሮሞ ባህል ፈጣሪ(ዋቃ) ከክረምት ጭቃና ጨለማ አውጥቶ ለብራ ላበቃ ፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ባሕላዊ ትውፊት ያለው መሆኑን ይናገራሉ፡፡
የኢሬቻ በዓል በተለይ ኢሬቻ መልካ ከክረምቱ ጨለማ፣ ጭቃ፣ ነጎድጓድና ዝናብ አውጥቶ ለመስከረም አደይ ላሸጋገረ እንዲሁም እርጥበትን ለሰጠ ፈጣሪ (ዋቃ) ምስጋና የሚቀርብበት ነው የሚሉት አባ ገዳ ወርቅነህ፤ ኢሬቻ ሠላም፣ እርቅ፣ ፍቅርና መረጋጋት የሚፈጠርበት ቦታ በመሆኑ ከጥንት ጀምሮ ኢሬፈና ሲካሄድ የመጣ መሆኑን ይገልጻሉ።
ይህንንም መሠረት በማድረግ የበዓሉ ተሳታፊዎች “ከፊታችን ያለው ጊዜ ብርሃን ነው” በማለት አበባና እርጥብ ሣር በመያዝ ለምስጋና ወደ በዓሉ ማክበሪያ ቦታ (መልካው) እንደሚሄዱም ያክላሉ። እንደ አባገዳ ወርቅነህ ገለጻ፤ ኢሬፈና በዓመት ሁለት ጊዜ የሚደረግ ሲሆን በፀደይ እና በበልግ ወቅቶች የሚደረግ ባሕላዊ ክዋኔ ነው፡፡
የበዓሉ ተሳታፊ አቶ በርሲሳ ደበሌ በበኩላቸው ኢሬቻ ለኦሮሞ ሕዝብ መገለጫው ነው ያሉ ሲሆን ፍቅርና አንድነት የሚጎለብትበት እንዲሁም ጥላቻን በመሻር እርቅ የሚያወርድበት ነው ይላሉ፡፡
ኢሬቻ ሠላምን ለማጽናት፣ እኩልነትና ፍትሕ ለማጎልበትና ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት እንዲሁም የመጪውን ጊዜ ብሩህ እንዲሆን የሚለመንበት ነው የሚሉት የበዓሉ ተሳታፊ አቶ በርሲሳ፤ ታዲያ በዚህ ጊዜ ተፈጥሮን ላጤናት ለፈጣሪ በምስጋና የሚያረግድ ስለመሆኑንም ይናገራሉ፡፡
ኢሬቻ አንድነት፣ ሠላም፣ እርቅ እና መተባበር በመሆኑ ከኢሬቻን ሠላም ተጠቃሚ መሆን ይኖርበታል የሚለው ደግሞ አርቲስት ቶኩማ ኩመላ ነው፡፡
በኢሬቻ የተጣላ ሳይታረቅ ወደ ኢሬቻ መልካ አይሄድም የሚለው አርቲስት ቶኩማ፤ ይህም ኢሬቻ የሠላምና የአብሮነት ምልክት ለመሆኑ ማሳያ ነው ባይ ነው፡፡
ወርሐ መስከረም ለኢትዮጵያውያን የግል ስጦታ ናት። የአዲስ ዓመት መባቻ፣ የብሩህ ተስፋ፣ የአዲስ ሕይወት መወጠኛ፣ የአዲስ ምኞት፣ የምሕረትና የቸርነት ደጆች የሚከፈቱባት የወሮች አውራ ናት፡፡ የሰዎች ግንኙነት የሚያይልበትና የሰብዓዊነት ምሕዋር የሚጠነሰስባት ወርሐ በኩር እንደሆነች በብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን ልብ ታትማለች። ከእነዚህም መካከል ኢሬቻ አንዱ ነው፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም