ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በሰላም በመጠናቀቁ ለፈጣሪ (ዋቃ) ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው። መጪው ዘመን መልካም እንዲሆን ፈጣሪን የሚለምንበት እንደሆነም ይገለጻል::
የዘንድሮው 2017 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል ዛሬ በሆራ ፊንፊኔ እና ነገ በሆራ አርሰዲ እንደሚከበር አባ ገዳዎች ገልጸዋል:: በዓሉ ”ኢሬቻ ለባህላችን ሕዳሴ” በሚል መሪ ሃሳብ ሰላምን፣ ይቅርታን፣ አብሮነትንና ወንድማማችነትን በሚያንጸባርቅ መልኩ እንደሚከበር ሲገለጽ ቆይቷል:: ታዲያ ኢሬቻ ከባህል ብዝሃነት አንጻር በተለይ በሀገር ግንባታ ሂደቱ ያለው ፋይዳ ምንድነው ስንል የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግረናል::
በኦሮሚያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የኦሮሞ ባህልና ታሪክ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሀሊማ ኤዶ፤ የኢሬቻ በዓል በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን፤ ኢሬቻ ቱሉና መልካ በመባል ይታወቃል ይላሉ::
ቀደም ሲል ኢሬቻ በኦሮሞ ባህል፣ ቋንቋ ብቻ ይከበር እንደነበር የሚጠቅሱት ወይዘሮ ሃሊማ፤ በአሁኑ ጊዜ ግን ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸውን፣ አለባበሳቸውን፣ ማንነታቸውንና ቋንቋቸውን የሚያንጸባርቁበት መድረክ መሆኑን ይገልጻሉ::
ኢሬቻ በሀገር ግንባታ ውስጥ የራሱን ሚና መጫወት የሚችል ነው የሚሉት ወይዘሮ ሀሊማ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ከወንድም ሕዝቦቹ ጋር በጋራ በመሰባሰብ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ ብዝሀ ባህልን፣ ቋንቋን በሚያንጸባርቅ መልኩ እያከበረው እንደሚገኝ ይናገራሉ::
ለበዓሉ የሀገር ውስጥና የውጪ ቱሪስቶች መሳተፋቸው በኢኮኖሚው ዘርፍ መቀራረብን እንደሚፈጥር ገልጸው፤ በተለይም በብዝሀ ባህል እና ቋንቋ በርካቶችን በአንድ አውድ እያሳተፈ የመጣ መሆኑን ያስረዳሉ::
ኢሬቻ የባህል ነጸብራቅ በመሆኑ በበዓሉ ባህላዊ አልባሳት፣ ምግቦች እንደሚቀርቡበት የሚገልጹት ወይዘሮ ሀሊማ፤ በአሁኑ ጊዜ የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ሰዎችን በሚማርክ መልኩ እየተሠሩ ነው ሲሉም ይገልጻሉ::
ኢሬቻ የኦሮሞን ሕዝብን ጨምሮ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ተሰባስበው የሚያከብሩት በዓል እየሆነ መጥቷል የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ፎክሎር ተመራማሪና መምህሩ ታደሰ ጂራታ (ዶ/ር) ናቸው::
ኢሬቻ የተለያየ ማንነት ያላቸው ሕዝቦች የራሳቸውን ባህል፣ አልባሳት፣ ቋንቋቸውን ይዘው የሚያከብሩት መሆኑ የሚገልጹት ታደሰ (ዶ/ር)፤ በዓሉ ብዝሀ ባህልና ቋንቋ የሚንጸባረቅበት አውድ ነው ሲሉ ይናገራሉ::
እንደሀገር በኢሬቻ ላይ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋ፣ ባህል፣ ማንነትና ብዝሀ ባህል የሚታይበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ተሳታፊዎች በንጹህ ልብ ለማክበር የሚሰባሰቡበት በመሆኑ ወዳጅነትን፣ መቻቻልን፣ በጋራ መቆምንና ሰላምን የሚያሳይ እንደሆነም ይገልጻሉ::
በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በገዳ አስተዳደር የፒኤችዲ ተማሪ የሆኑት ጌታቸው ታደሰ እንደተናገሩት፤ ኢሬቻ ማንኛውም ሰው ሊሳተፍበት የሚችል አንዱ የኦሮሞ ሕዝብ መገለጫ የሆነ በዓል ነው ይላሉ::
ኢሬቻ ለሀገር ሁለንተናዊ አንድነትና ብዝሀነት ትልቅ ሚና መጫወት በሚችል መልኩ ብሔር ብሔረሰቦችን በማሳተፍ የሚከበር መሆኑን ጠቅሰው፤ የራሳቸውን አለባበስ ባህል፣ ጌጣጌጦችን ይዘው በመምጣት ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር እንደሚያከብሩት ይገልጻሉ::
ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ቦታ ላይ ለማክበር የሚሰባሰቡበት በዓል እንደሆነ በመግለጽ፤ አንድነትን፣ ፍቅር፣ ወንድማማችነትንና አብሮነትን የሚያጠናክሩበት አውድ ይፈጥራል ሲሉ ይናገራሉ::
ኢሬቻ በሕዝቦች መካከል አብሮ በሰላም ለመኖር፣ እጣ ፋንታቸውን ለመወሰን፣ ኢኮኖሚያ፣ ባህላዊ፣ ማህበራዊ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችል የገለጹት በዘርፉ የፒኤችዲ ተማሪ የሆኑት ጌታቸው፤ የባህል ትውውቅን፣ ቋንቋ መለዋወጥን፣ መከባበር፣ መቻቻል እንዲኖር በማድረግ በዜጎች መካከል ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው አንድነታቸውን እያጠናከሩ የሚሄዱበት መድረክ መሆኑን ያስረዳሉ::
በዓሉ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ጨምሮ ከውጪና ከሀገር ውስጥ ተሳታፊዎች የሚገኙበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ለሀገሪቱ ገጽታ ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ትልቅ ነው ሲሉ ያስረዳሉ::
የኢሬቻ ዕሴት የሆኑት ሰላም፣ አብሮነት፣ አንድነት፣ ወንድማማችነትና አብሮ መቆም በሕዝቦች መካከል አስተሳሳሪ ገመድ መሆናቸውን በመግለጽ፤ ተሳታፊዎች የኢሬቻን ባህል፣ ትውፊትና ሥርዓት ብቻ በማክበር የሚሳተፉበት እንደሆነም ይገልጻሉ::
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም