«“ኢሬቻ የአንድነታችን ምልክት በመሆኑ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተሠራ ነው”»- ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ፡- ኢሬቻ የአንድነታችን ምልክትና የሰላማችን ምሳሌ በመሆኑ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተሠራ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

6ኛው የኢሬቻ ፎረም በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ “ኢሬቻ ለባህላችን ሕዳሴ” በሚል መሪ ቃል በትናንትናው እለት ተካሂዷል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢሬቻ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበትና ሰዎች ያለምንም ልዩነት የሚሳተፉበት በዓል ነው።

ኢሬቻ የሕዝቦች አንድነት የበለጠ የሚጠናከርበት መሆኑን የገለጹት አቶ ሽመልስ፤ ኢሬቻ የምስጋና፣ የሰላም፣ የይቅርታ፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት እንዲሁም ባህላዊ እሴቶች የሚንጸባረቅበት በዓል መሆኑንም ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ፤ የኢሬቻ በዓል አሁን ላይ ከኦሮሞ ሕዝብ አልፎ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲሆን ጠብቀው ላቆዩት አባገዳዎችና ሀደሲንቄዎች ምስጋና አቅርበው፤ የክልሉ ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በተለይም ባህሉን የሚያከብር ትውልድ ለመፍጠር የገዳ ሥርዓት በክልሉ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተካቶ ትምህርት እየተሰጠበት ይገኛል ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ባህልን ለልማት ሥራዎች ለማዋል በተደረገው ጥረት በርካታ ትምህርት ቤቶች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት መገንባታቸውን ገልጸዋል።

የባህል ፍርድ ቤቶች በክልሉ በስፋት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቁመው፤ የሕዝቡ የመረዳዳት ባህል እየተጠናከረ መምጣቱንም አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ከተለያዩ አካባቢዎች በኢሬቻ ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ እያስተናገደ በመሆኑ ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል።

በፎረሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ የዘንድሮ የኢሬቻ በዓል ልዩ መሆኑን ገልጸው፤ አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት አምራ እና ደምቃ ሆረ ፊንፊኔን ታከብራለች ብለዋል።

አዲስ አበባ ተጨማሪ ውበት ተላብሳ የቱሪዝም መስህብ በመሆን የገቢ ምንጭ ሆናለችም ሲሉ አክለዋል። መንግሥት በገባው ቃል መሠረት ቃሉን አክብሮ እና ቃሉን ወደ ተግባር ለውጦ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ማከናወኑን ያነሱት ከንቲባዋ፤ በዚህም የመንግሥት እና የሕዝቡ መተማመን ማደጉን ተናግረዋል።

ይሁንና አሁንም ብዙ ሥራ እንደሚቀር የገለጹ ሲሆን፤ ባህል እና እሴታችን የቱሪዝም መስህብ ሆኖ ገቢ እንዲያስገኝ እና የሀገርን ኢኮኖሚ በማሳደጉ ረገድ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ማንነት መገለጫ ብቻ ሳይሆን የቱሪዝም መስህብ ወደ መሆን የተሸጋገረበት እና የኢኮኖሚ ምንጭ እስከ መሆን የደረሰበት ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣቱንም ከንቲባ አዳነች አውስተዋል።

የኢሬቻ በዓል ባማረ እና በደመቀ መልኩ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ያሳሰቡት ከንቲባ አዳነች፤ በዓሉ በተሳካ መልኩ እንዲከበር ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

ኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምቢሮ፤ ኢሬቻ የገዳ ሥርዓት አንዱ መገለጫ ሆኖ በዩኔስኮ መመዝገቡን አስታውሰው፤ አሁን ኢሬቻ እራሱን ችሎ እንዲመዘገብ መረጃ እየተሰናዳ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ የኢሬቻ በዓል በተ.መ.ድ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም እንዲመዘገብና ከኢትዮጵያም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቅ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጎን ለጎንም ኢሬቻ ከባህል ባለፈ የቱሪዝም ምንጭ እንዲሆንና ለሀገር ገቢ እንዲያስገኝ እየተሠራ ያለው ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በመርሀ-ግብሩ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደሲንቄዎች፣ ዲፕሎማቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You