ውጤታማ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት እድሜ ላይ መሥራት ያስፈልጋል – አሰልጣኝ ስዩም ከበደ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለሴካፋ ዞን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻ ዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ቡድኑ ከነበረው አጭር ጊዜ አኳያ፤ ተጫዋቾችን ከእድሜና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ለመምረጥ እንደተቸገሩ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ተናግረዋል፡፡

የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የወንዶች ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ከነገ በስቲያ ጀምሮ በታንዛኒያ አዘጋጅነት ዳሬሰላም ላይ ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንም ለውድድሩ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ትናንት ምሽት ወደ ስፍራው አቅንቷል። በውድድሩ የሚካፈለውን ብሄራዊ ቡድን ለማዘጋጀትም ተጫዋቾች ከመስከረም 07/2017 ዓ/ም አንስቶ ተሰባስበው ሲዘጋጁ ቆይተዋል።

ብሔራዊ ቡድኑ ሁለት ግብ ጠባቂዎችን፣ አምስት ተከላካዮችን፣ ስድስት አማካይ፣ አምስት አጥቂዎችን በአጠቃላይ 18 ተጫዋቾችን አካቷል፡፡ ቡድኑን ለማዘጋጀት ትልቅ ፈተና እንደገጠማቸው አሰልጣኙ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት አብራርተዋል፡፡ ምርጥ 11ዱን ለመለየት የተቸገሩ ቢሆንም ከጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን የተደረጉት ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ግን በእጅጉ እንደጠቀሟቸው ጠቅሰዋል፡፡

በመጀመሪያ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫወቾች 33ቱ ሲገኙ፣ አራት ጥሪ የደረሳቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ተጫዋቾች ከመጀመሪያውም ቡድኑን አልተቀላቀሉም፡፡ ማጣሪያው ከተጀመረ በኋላ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ፓስፖርት በማጣራት ሶስት ተጫዋቾች ተካተዋል፡፡ ከውጪ ብሔራዊ ቡድኑን ለመቀላቀል የመጡት 6 ተጫዋቾች ደግሞ ምርጫው ከ95 ከመቶ በላይ ከተጠናቀቀ በኋላ ስለመጡ ሊቀነሱ ችለዋል፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች ከመዘግየታቸው ውጪ ቀልባቸውን የሳቡ ሁለት ተጫዋቾች እንደነበሩም አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡

ከጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን ጋር እስከ ተካሄደው ሁለተኛ የወዳጅነት ጨዋታ ድረስ ለመጨረሻ ዙር የተመረጡት 20 ተጫዋቾች በክለብ ውድድር ምክንያት ከአሰልጣኙ ጋር እንዳልነበሩም ተብራርቷል፡፡ ከመጀመሪያውን የወዳጅነት ጨዋታ ከአንድ ቀን በኋላ የተገኙ ተጫዋቾችም ነበሩ፡፡ በመጨረሻውም የወዳጅነት ጨዋታ ምርጥ 11 ለመመረጥ ጥሩ አጋጣሚ ቢሆንም በውድድር ምክንያት ያልተገኙ ተጫዋቾች በመኖራቸው እንደ ቡድን ለመስራት ተቸግረዋል፡፡ በውድድሩ የሚጠቀሙበትን ቅርጽ ለመለየትና ልምድ ለመቅሰም ግን ሁለቱ የወዳጅነት ጨዋታዎች ጥቅም ነበራቸው፡፡ በተጫዋቾቹ ላይ የተፈለገው የአጨዋወት መንገድ እንዲሰርጽ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ለመተግበር ጥረት መደረጉንም አክለዋል፡፡

ውጤታማ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት እንደ ሀገር ከላይ እስከ ታች መሰራት እንደሚኖርበትም አሰልጣኝ ስዩም ጠቁመዋል፡፡ ለአስር ዓመታት ወጣት ቡድኖችን እንዳሰለጠኑ የገለፁት አሰልጣኙ፣ ትክክለኛ የእድሜ አሰራር በኢትዮጵያ የተለመደ እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡ ከፌዴሬሽኑ ጀምሮ የእድሜ እርከኑ ተጠብቆ እንዲሄድና ትክክለኛ መስመር እንዲከተል፤ ክለቦችም ኃላፊነት መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ በሀገር ደረጃ የማይሰራ ከሆነ የእድሜ ትክክለኝነትን በማጥራት ውጤታማ ብሔራዊ ቡድን መመስረት አስቸጋሪም ነው ይላሉ፡፡ የተመረጡት ተጫዋቾች ከ20 ዓመት በታች ውድድሮች ላይ በ2014፣ 2015 እና 2016 ዓ.ም የተጫወቱ እና ተቀራራቢ እድሜ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለቡድኑ ፈተና የሆነው የውድድሩ የጊዜ ቆይታ ረጅም መሆኑና ብዙ ጨዋታዎች መካሄዳቸው በትንሹ 23 ተጫዋቾችን መያዝ ግዴታ ቢሆንም እድሉ ሊፈጠር አልቻለም ብለዋል፡፡ ከዝግጅቱ አጀማመር፣ ከምዝገባው ህግ አኳያ 18 ተጫዋቾች ብቻ በመመረጣቸው ሁለገብ የሆኑ ተጫዋቾችን ለማካተት ጥረት ተደርጓል፡፡ በውድድሩ ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ ጥረት እንደተደረገና ከዓመታት በፊት በወጣቶች ስልጠና ላይ የነበረው ፈተና አሁንም አልተቀረፈም ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም እድሜ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ትክክለኛ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም፣ ቡድኑ ውስጥ የተካተቱ ተጫዋቾችን ከእድሜ አንጻር ለማመጣጠን የተቀራረበ ምርጫ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ አሰልጣኙ ለውጤታማ ቡድን የሚያመች ሁኔታ ባይፈጠርም ባለው ልምድና በሌሎች ቴክኒኮች ለአፍሪካ ዋንጫ የሚያሳልፍ አቅምን መሰረት አድርገው መዘጋጀታቸውንም አክለዋል፡፡

በውድድሩ ተሳታፊነታቸውን ያረጋገጡት የዘጠኝ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖች በሁለት ምድቦች ተከፍለው የሚፎካከሩ ይሆናል። በመጀመሪያው ምድብ አዘጋጇ ታንዛኒያ ከሱዳን፣ ርዋንዳ፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ጋር የተደለደሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በምትገኝበት ቀጣዩ ምድብ ደግሞ ቻምፒዮና ዩጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እና ብሩንዲ ይገኛሉ። ለሁለት ሳምንታት ያህል የሚደረገው ውድድር ከነገ በስቲያ ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል፡፡ ውድድሩ በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት ለሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ዞኑን ወክለው የሚካፈሉ ሁለት ሀገራትን ለመለየት እንደ ማጣሪያ የሚያገለግልም ነው።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You