የሀገር ተረካቢዎችና ባለውለታዎች አለኝታው ተቋም

ድህነትና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለተንሰራፉባቸው ማኅበረሰቦች፣ የበጎ አድራጎት ተግባራት የማኅበራዊ ፈውስ ሁነኛ መገለጫዎችና መሳሪያዎች ሆነው ያገለግላሉ። የበጎ አድራጎት ተግባራት ገንዘብን፣ ፍቅርን፣ ጊዜንና ሌሎች ሀብቶችን ከራስ ቀንሶ ለሌሎች በማካፈል የሌሎችን ችግር ለማቃለል፤ ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አንድነትን ለማጠንከር እንዲሁም መተሳሰብና መከባበር የሰፈነበትን ማኅበረሰብ ለመፍጠር የማይተካ አወንታዊ ሚና አላቸው።

መረዳዳት የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነና የእርስ በእርስ ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን አጠንክሮ የኖረ ተግባር ነው። መረዳዳት ባይኖር ኖሮ አሁናዊ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አሁን ከሚታየው የተለየ ይሆን ነበር። ይህ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ተግባር በብዙ መንገዶች ይከወናል። በተናጠልና በጥቂት ግለሰቦች ስብስብ ከሚከናወኑ የመረዳዳት ተግባራት በተጨማሪ፣ መደበኛና ሕጋዊ አሰራሮችን ተከትሎ የበጎ አድራጎት ተቋማትን የማቋቋምና የመሥራት ተግባርም በስፋት የሚታወቅ አሰራር ነው።

ችግሮችን ተቋቁሞ ለማለፍ ብርታት የሚያጥራቸው ሕፃናትና አረጋውያን፣ ለብዙ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። አካላቸውና አዕምሯቸው ያልጠናው ለጋ ሕፃናት እና ብዙ ደክመው በማምሻ እድሜያቸው ላይ አቅም የከዳቸው አረጋውያን፣ የቤተሰብና የዘመድ እንክብካቤ በሚፈልጉበት የእድሜያቸው ምዕራፍ ላይ ለችግር ተጋላጭ ሲሆኑ ችግሮችን የሚቋቋሙበት ብርታት አያገኙም። የበጎ አድራጎት ተግባራት እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለማቃለል በዋጋ የማይተመን ሚና አላቸው። ‹‹ዝግባ የሕፃናትና አረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› የተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት የተመሰረተውም የሀገር ተረካቢና የሀገር ባለውለታ የሆኑትን እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘላቂነት ለማገዝ ነው።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ስለሺ ጌታቸው ‹‹ዝግባ›› የሕፃናትና አረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት በዋናነት አረጋውያንንና ሕፃናትን በመርዳት ተግባር ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ ይገልፃሉ። የተመሰረተው በነሐሴ 2000 ዓ.ም ነው። ‹‹ድርጅቱ የተመሰረተው 23 ሕፃናትንና 12 አረጋውያንን በመርዳት ነው። ከውጭ ተረጂነትና ጠባቂነት ነፃ በሆነ መንገድ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ባለሀብቶች የሚደርጓቸውን ድጋፎች እና በተቋሙ የሚከናወኑ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በማቀናጀት የድጋፍና እንክብካቤ ሥራዎችን እንሰራለን ብለን ነው የተነሳነው›› በማለት ስለድርጅቱ አመሰራረት ያወሳሉ።

23 ሕፃናትንና 12 አረጋውያንን በመርዳት የተጀመረው የድርጅቱ ሥራ፣ በአሁኑ ወቅት ለሦስት ሺ ሕፃናትና አረጋውያን ድጋፍና እንክብካቤ ወደ ማድረግ እንዳደገ ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ። ‹‹በአሁኑ ወቅት በድርጅቱ ድጋፍና እንክብካቤ የሚደረግላቸው ሰዎች ብዛት ሦስት ሺ ደርሷል። ምንም ዓይነት የውጭ ርዳታ ሳይኖረው የማህበረሰቡንና የድርጅቶችን ድጋፍ እንዲሁም የራሳችንን የውስጥ ገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በማቀናጀት ሕፃናትንና አረጋውያንን እየደገፍን እንገኛለን›› ሲሉ ያብራራሉ።

አቶ ስለሺ እንደሚሉት፣ ድርጅቱ ርዳታ የሚያደርግላቸው ሕፃናት አንድ ወይም ሁለቱንም ወላጆቻቸውን ያጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ሁለቱንም ወላጆቻቸውን ያጡ ከሆኑ ‹‹ዝግባ›› ድጋፍና እንክብካቤ የሚያደርገው የሕፃናቱ አክስት፣ አጎት ወይም ሌላ የሥጋ ዘመድ የወላጅ መብቶችን ወስደው የማሳደግ እድሉን ካገኙ በኋላ ነው።

የድርጅቱ የድጋፍና እንክብካቤ ተግባራት ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ትኩረት ይደረጋል። ሕፃናቱ ወደ ድርጅቱ የድጋፍና እንክብካቤ ማዕከል ከገቡበት ቀን ጀምሮ ድርጅቱ ግብዓቶችን በማሟላት አሳዳጊዎቻቸው እንደየልምዳቸውና ፍላጎታቸው በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ያደርጋል። ቁጠባን እንዲለምዱ እና የገቢ ማስገኛ ሥራቸው እንዲጎለብት የሚያስችሉ የሙያ ስልጠናዎችና ድጋፎች ይሰጧቸዋል፤ ድጋፍና ክትትሎችም ይደረጉላቸዋል።

ሕፃናቱም የምግብ፣ አልባሳትና የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ እስከ ሰባት ዓመታቸው ድረስ (እስከ KG-3 ተምረው) በማዕከሉ ውስጥ ይቆያሉ። ሕፃናቱ እስከ ሰባት ዓመታቸው ድረስ ቆይተው ከKG-3 ተመርቀው ወደ ማኅበረሰቡ ይቀላቀላሉ። አሳዳጊዎቻቸው ደግሞ በድርጅቱ ድጋፍ ምክንያት ኑሯቸው ተሻሽሎ በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

‹‹ሁልጊዜ እየደገፍን መኖር ሳይሆን ችግሮቻቸውን የሚፈቱበትን መንገድ በማሳየት ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ በማድረግ እና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሌሎች ሕፃናትን በመቀበል ለድህነት ቅነሳው የበኩላችንን አስተዋጽኦ የማበርከት ሥራ እየሰራን ነው›› በማለት አቶ ስለሺ ስለድርጅቱ አሰራር ይገልፃሉ።

አረጋውያንን በተመለከተ ደግሞ ድርጅቱ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ሲያስረዱ ‹‹እድሜያቸው ከ60 በላይ የሆኑ አረጋውያንን እንቀበላለን። ጤናቸው እንዲጠበቅና ቀሪ ዘመናቸውን ደስተኛ ሆነው እንዲያሳልፉ እንሰራለን። ለጤናቸው የሚበጁ ቀለል ያሉ እንቅስቃሴዎችንና የእጅ ሥራዎችን እንዲሰሩም ይደረጋል፤ ከባድ ሥራዎችን አይሰሩም። ይህን በማድረግ አረጋውያኑ ቀሪ እድሜያቸውን ደስተኛ እንዲሆኑ ለማድረግ እንሞክራለን›› ይላሉ።

ድርጅቱ የአረጋውያንና ሕፃናት እንክባካቤ ተግባሩን በማዕከልና ከማዕከል ውጭ ያከናውናል። የቤት ለቤት እንክብካቤውን በ15 እንዲሁም የማዕከል ድጋፉን ደግሞ በ45 በጎ ፈቃደኞችና ሠራተኞች አማካኝነት ያከናውናል። ሥራ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል፤ ለ70 ሰዎችም የሥራ እድል ፈጥሯል።

‹‹ዝግባ›› የሕፃናትና አረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ፣ ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ባሏቸው ማህበረሰብ ተኮር ተግባራት የበርካታ ሰዎች ሕይወት በበጎ ተለውጧል። ሥራ አስኪያጁ እንደሚያብራሩት፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናት አሳዳጊ የማግኘት እድል እንዲሁም ምግብ፣ አልባሳት፣ መጠለያ፣ ትምህርትና ህክምና አግኝተዋል። በአብያተ ክርስቲያናት አካባቢ እና በጎዳናና በየበረንዳው ላይ ይኖሩ የነበሩ እንዲሁም አማራጭ አጥተው በሴተኛ አዳሪነት ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች ከልመና፣ ከሴተኛ አዳሪነት፣ ከጎዳና ተዳዳሪነት ወጥተው ወደተሻለ የሕይወት መስመር ገብተዋል። ድርጅቱ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ሕፃናት በሥነ ምግባር ታንፀው እና ሀገራዊና ባሕላዊ ማንነታቸውን አውቀው እንዲያድጉ የሚያደርግበት ለየት ያለ ሥርዓት አለው። ይህ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።

አንዳንዶቹ በድርጅቱ ድጋፍ አማካኝነት ከተረጂነት ተላቀው ተመልሰው የድርጅቱ አባል ሆነው የአባልነት ክፍያ እየከፈሉ ተቋሙን እያገዙ ይገኛሉ። በድርጅቱ ድጋፍ ተምረው በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች በሙያቸው ድርጅቱን እያገለገሉ ይገኛሉ። ከተረጂነት ተላቀው ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤቶች እያስተማሩ የሚገኙም አሉ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ወላጆች/አሳዳጊዎች ከልመና፣ ጎዳና ተዳዳሪነትና ሴተኛ አዳሪነት ወጥተው ሰርተው ራሳቸውን ችለው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸው ትልቅ ለውጥና ስኬት ነው። ከምንም ተነስቶ ሰርቶ ራስን ማስተዳደር መቻል አስደሳች ነገር ነው። ድርጅቱ ከጠባቂነትና ከልመና ወጥቶ ራስን ማስተዳደር የሚቻልበትን አሰራር ይከተላል። በዚህ ደግሞ በርካታ ውጤቶችና ስኬቶች ተገኝተዋል።

‹‹ሕፃናቱ የሚማሩበት ድርጅቱ የራሱ ትምህርት ቤት አለው። የራሳችን የትምህርት ባሕል አለን፤ የትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን። ማኅበራዊ እሴቶችና ኢትዮጵያዊነት ላይ እንሰራለን። ባሕላዊ እሴቶች ሕፃናት ላይ እንዲቀረጹ እንጥራለን። ሕፃናቱ የሚማሩት ራሳችን ባስተማርናቸው፣ በቀረጽናቸውና ስልጠና በሰጠናቸው መምህራን አማካኝነት ነው። በ45 መምህራንና ተንከባካቢዎች ይህን ሥራ እየሰራን ነው። ሕፃናትና አረጋውያን ድጋፍና እንክብካቤ የሚያገኙት በድርጅቱ መምህራንና ተንከባካቢዎች አማካኝነት ነው። ትምህርት ቤቱ እስካሁን እስከ‹KG-3› ድረስ ያስተምራል። ወደፊት ቀጣይ የትምህርት ደረጃዎችን ለመጀመር አቅደናል›› በማለት አቶ ስለሺ ስለሕፃናት የትምህርት አሰጣጥና የአረጋውያን እንክብካቤ ያስረዳሉ። ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ ከስምንት ሺ 600 በላይ አባላት እንዳሉት ጠቅሰው፣ የአባልነት ክፍያዎችን በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ ለመፈፀም ድርጅቱ ለኢትዮ-ቴሌኮም ጥያቄ ማቅረቡንም ይናገራሉ።

ድርጅቱ ሥራዎቹን ሲያከናውን ስለሚያጋጥሙት ችግሮችም አቶ ስለሺ ያብራራሉ። የማህበረሰቡ ግንዛቤ እጥረት፣ የሚዲያ ሽፋን አለማግኘት፣ የተሽከርካሪ አለመኖር እና ሀገራዊ የፀጥታ ሁኔታ በድርጅቱ ሥራዎች ላይ መሰናክል የፈጠሩ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። የድርጅቱ ሥራዎች የሚዲያ ሽፋን ቢያገኙ በህብረተሰቡ ዘንድ የመታወቅና ተደራሽ የመሆን እድል ይኖረው እንደነበር አመልክተው፣ የፀጥታ ችግሮች ሲፈጠሩም የበጎ አድራጎት ተቋማትን የመጎብኘት ተግባር ስለሚዳከም በተቋማቱ ላይ ብዙ ጫና ይፈጠራል ሲሉ ይገልፃሉ።

ችግር ፈቺ ተግባራት ላይ በመመስረት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ እነዚህ ወገኖች ከችግሮቻቸው ተላቅቀው በማኅበረሰብና ሀገር ግንባታ ሂደት የራሳቸውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የማድረግ ዓላማን ይዞ የሚንቀሳቀሰው ‹‹ዝግባ›› የሕፃናትና አረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ በዜጎች ሕይወት ላይ ዘላቂ ለውጥ ለመፍጠር የሚያስችሉ የረጅም ጊዜ እቅዶች እንዳሉትም ሥራ አስኪያጁ አቶ ስለሺ ይገልፃሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ የጤና አገልግሎት መስጠት የሚችል ክሊኒክ በማቋቋም በድርጅቱ ርዳታ ለሚደረግላቸው ወገኖች አገልግሎት እንዲሰጥና ከውጭ አገልግሎቶች ገቢ እንዲያመነጭ የማድረግ፣ ለሕፃናትና አረጋውያን የሚያስፈልጉ ተሽከርካሪዎችን (ለመጓጓዣ፣ ለህክምና…) የማሟላት፣ ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ህንፃ በማስገንባት ከህንፃው የሚገኘውን ገቢ ለድጋፍና እንክብካቤ አገልግሎት የማዋል እቅዶች አሉት።

ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በየዞኑ በመክፈት አሁን እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት ለሌሎች ማኅበረሰቦች ተደራሽ የማድረግ፣ ሀገር አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን የማዘጋጀት፣ የከርሰ ምድር ውሃ በማስቆፈር ውሃው እየተሸጠ ገቢ እንዲያስገኝና በማዕከል ውስጥ ላሉ ሕፃናትና አረጋውያን እንክብካቤ እንዲውል የማድረግ እንዲሁም ዘመናዊ የወንበርና ድንኳን ኪራይ አገልግሎት የመጀመር እቅዶችም እንዳሉት አመልክተዋል። እነዚህን በማሳካት አሁን እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት በእጥፍ የማሳደግ ትልቅ እቅድ አለን›› በማለት ስለድርጅቱ እቅዶች ያብራራሉ።

‹‹ዝግባ›› የሕፃናትና አረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ፣ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ያሏቸው የበጎ አድራጎት ተግባራትን ሲያከናውን በመቆየቱ ከበርካታ ተቋማት እውቅናዎችን አግኝቷል። ለድርጅቱ እውቅና ከሰጡ ተቋማት መካከል ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ የአማራ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የክልልና አጋር የልማት ተቋማት እና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ይጠቀሳሉ።

አቶ ስለሺ የበጎ አድራጎት ተግባራት ከዕለታዊ ርዳታ ተሻግረው በግለሰቦች ሕይወትና በማኅበረሰብ ገፅታ ላይ ዘላቂ ለውጥ እንዲያስገኙ ኅብረተሰቡ፣ የበጎ አድራጎት ተቋማት፣ ድጋፍ ፈላጊዎችና መንግሥት የየራሳቸው ኃላፊነቶች እንዳሉባቸው ያስገነዝባሉ። ለዚህም ባለሀብቶች፣ የሲቪል ድርጅቶች ባለሥልጣንን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ተቋማትና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ብሎም መላው ኅብረተሰብ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You