የትግራይ ክለቦች ተስፋ ሰጪ የፕሪሚየር ሊግ አጀማመር

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመቱን ከጀመረ ሶስተኛ የውድድር ሳምንቱን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ክለቦች በድሬዳዋ ከተማ ላይ ተሰባስበው ውድድራቸውን እያካሄዱ ይገኛሉ። አራት ዓመታት ከሊጉ ርቀው የቆዩት የትግራይ ክልል ክለቦችም በተመለሱበት ዓመት ጥሩ አጀማመር እያሳዩ ይገኛሉ፡፡

በ19 ክለቦች መካከል እንደሚካሄድ ታቅዶ መጀመሩ ይታወሳል። ወልቂጤ ከተማ ከክለብ ፍቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ማሟላት የሚገባውን ሰነድ ባለማቅረቡ በኢትዮጵያ እግር ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ መሠረት በአወዳዳሪው አካል ከሊጉ መሰረዙን ተከትሎ በ18 ክለቦች መካከል ለመካሄድ ተገዷል። በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከሁሉም ውድድሮች ርቀው የተመለሱት የትግራይ ክልል ሶስት ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ አበረታች እና ተስፋ ሰጪ ጅምር አሳይተዋል፡፡

ክለቦቹ ለአራት ዓመት ከልምምድና ከውድድር ርቀው እንደመቆየታቸው፣ የውድድሩን ጫና መቋቋም ይከብዳቸዋል የሚል ስጋት የነበረ ቢሆንም አጀማመራቸው ከተጠበቀው በላይ መልካም የሚባል ሆኗል። ክለቦቹ በክልሉ ከነበረው ችግር አንጻር በአጭር ጊዜ በመደራጀት ለውድድር መብቃተቸው እራሱ የሚበረታታና የሚደነቅ ነው። ከእግር ኳስ ለአንድ እና ሁለት ወራት መራቅ እንኳን ዋጋ በሚያስከፍልበት በዚህ ዘመን ችግሮችን ተቋቁሞ ወደ ውድደር መመለስ ሌሎቹ ክለቦች ሊማሩበት የሚገባም ትልቅ ማሳያም ጭምር ነው። ከሁሉም በላይ እንደ አዲስ በመተግበር ላይ የሚገኘውን የክለቦች ፍቃድ አሰጣጥንም በማሟላት ለውድድሩ መብቃት እንዲሁ ለአንዳንድ ክለቦች እራሳቸውን መፈተሽ እንደሚገባ የሚያመላክትም ይሆናል።

ለአንድ ክለብ መመዘኛነት መሠረታዊ የሚባሉትን አስገዳጅ መስፈርቶችን አሟልተው እና የክለብ ምዝገባን አከናውኖ ወደ ትልቅ ውድድር መመለስ ተጨማሪ ጉልበት እንደሚሆን እነዚህ ክለቦች ማሳያ ናቸው። አብዛኞቹ የሊጉ ክለቦች የክለብነት መስፈርትን ይዞ ባለመገኘታቸው እንደ ክለብ መወጣት የሚገባቸወን ኃላፊነት ሳይወጡ ቀርተው መነጋገርያ እስከ መሆንም ደርሰዋል። ፈተናዎች ያልበገሯቸው ክለቦቹ ግን አስፈላጊውን የሰው ኃይል እና የቢሮ አደረጃጀት አሟልተው ወደ ሊጉ ተመልሰዋል፡፡

መቐለ 70 እንደርታ፣ ውልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ስሁል ሽረ በሊጉ ጅማሬ ባካሄዷቸው ሁለት እና ሶስት ጨዋታዎች ጥሩ ተፎካካሪ መሆናቸውን አሳይተዋል። ክለቦቹ እስከ አሁን በጥቂት ጨዋታዎች ባስመዘገቡት ጥሩ ውጤት በደረጃ ሰንጠረዡም የተሻለ ቦታን መያዝ ችለዋል። መቐሌ 70 እንደርታ እና ስሁል ሽረ ጠንካራ ተፎካከሪ ሆነው የተመለሱ ሲሆን ከትልልቅ የሊጉ ክለቦች ጋር ባደረጉት ጨዋታ ነጥቦችን እየሰበሰቡም ይገኛሉ፡፡

በሊጉ መክፈቻ መርሃግብር ሃዲያ ሆሳዕናን የገጠሙት የእንደርታ ቀያይ አናብስት በጨዋታው ቢሸነፉም ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ችለው ነበር። ለዓመታት ከውድድር ርቀው እንደመቆየታቸው ከነብሮቹ ጋር ተፎካክረው 1 ለዜሮ በሆነ ጠባብ ውጤት ነበር የተሸነፉት። በሁለተኛ ሳምንት መርሃግብርም ከፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ክለቦች መከካል አንዱ ከሆነው ፋሲል ከነማ ጋር ተመጣጣኝ ፉክክር አድርገው ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየተቀናጁ የመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች በሶስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃግብር ፈረሰኞቹን መርታታቸው ደግሞ ያልተጠበቀ ነበር። የሊጉን ታላቅ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስን 1 ለ 0 የረቱ ሲሆን በአሠልጣኝ ዳንኤል ፀሃዬ እየተመሩ ከውድድር ከመራቃቸው በፊት ወደነበሩበት ጠንካራ ተፎካካሪነት ለመመለስ ጥሩ ጅምር ላይ ይገኛሉ።

ስሁል ሽረ በተመሳሳይ ከዓመታት በኋላ ወደ ውድድሩ በተመለሰበት ዓመት ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን በጥሩ ውጤት መጀመር ችሏል። ሁለት ጨዋታዎችን ከሊጉ ጠንካራ እና ውብ እግር ኳስን የሚጫወቱ ክለቦችን ገጥሞ አራት ነጥቦችን ከሰበሰቡት ክለቦች ተርታ ይገኛል። በመጀመርያ ሳምንት ጨዋታ አዳማ ከተማን አስተናግዶ ሶስት ለ ሁለት በመርታ ሊጉን በድል የጀመረበትን ውጤት አስመዝግቧል። በሁለተኛ ሳምንት ጨዋታቸው ሃዋሳ ከነማን አስተናግደው አንድ አቻ በመለያየት የራስ መተማመኑን ይበልጥ ማጎልበት ችሏል። የክለቡም ድል ምንያህል በጥንካሬ ወደ ሊጉ እንደተመለሱ አመላካች ከመሆኑም በላይ የሊጉ ክለቦች የሚገኙበትን ደካማ አቋም የሚያሳይም ነው። ከሶስቱ ክለቦች እስከ አሁን ድል ያልቀናው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቢሆንም መጥፎ የሚባል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አላደረገም። በሁለት የሊጉ ጨዋታዎች ጥሩ ፉክክር በማድረግ በጠባብ ውጤቶች ተሸንፎ ውድድሩን በተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

በ18 ክለቦች መካከል ተካሂዶ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ የዋንጫ አሸናፊዎች የሚለዩበት 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ከስርጭት፣ ከደጋፊ ድርቅ እና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ማን ዋንጫውን ያነሳል የሚለው እና ከሊጉ የትኞቹ ክለቦች ይወርዳሉ የሚለው በጉጉት ይጠበቃል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You