ታምሜ የማላውቀው ሰው በሃምሳ ዓመቴ አልጋ ያዝኩ..። የበሽታን ጣዕም የማውቀው በቁርጥማት ነው.. ከአፍላነቴ የጀመረ እስከ ጉልምስና እድሜዬ የተከተለኝ ቁርጥማት አለብኝ። የምሽረው በዳበሳ ነው..በልጅነቴ እናቴ ስትዳብሰኝ በወጣትነቴ ደግሞ በሚስቴ ጣቶች። ከሃምሳ ዓመት በኋላ በሌላ ደዌ ተመትቼ ሆስፒታል ስገባ ቁርጥማቴን በስንት ጣሙ እያልኩ ነበር። አንዳንድ የበሽታ ጥሙርሙሮች አሉ ለማንም እንዳይነገሩ ሆነው የተፈጠሩ። ከአልጋ እስክነሳ ድረስ የሆስፒታሉን ቅጥር አዘግቼ ከጠያቂዎቼ ልቆራረጥ ተመኝቼ ነበር..ድህነት አይኑ ይፍሰስና።
ምን ሆኖ ነው ለሚሉ የቅርብና የሩቅ ጠያቂዎች ምንም እንዳይሉ አስታማሚዎቼን አስጠንቅቄ ሆስፒታል ሰነበትኩ። እናቴንና ሚስቴን ከሁለት ልጆቼ ጋር ለአስታማሚነት አጠገቤ አቁሜ ሌላውን ፊት ነሳሁ። እናቴ የበሽታዬን አይነት ከማወቋ በፊት ሆስፒታል ገባ ሲሏት ለቁርጥማቴ መስሏት ነበር። አባቴ ደግሞ መጋኛ ነው…አንጠፍሮት ብሎ ነበር አሉ። አንዳንድ በሽታ አለ..ለሰሚውም ለተናጋሪውም የሚቀፍ..አፍና ጆሮ ላይ እሬት እሬት የሚል። በሃምሳ ዓመቱ ለግርዛት ሆስፒታል ገባ ቢባል ሰው ምን ይላል? ከመገረዜ በፊት ለማንም እንዳታወራ ቢጠይቋትም ምንም እንዳትል እናቴን በምታምነው የጽዋ ታቦቷ አስምያታለሁ።
ጠዋት ወደረፋድ ሲያዘግም የገረዘኝ ዶክተር በወጣበት አንድ የሴት ኮቴ ሰተት አለ። ከእናቴና ከሚስቴ አንዳቸው ይሆናሉ ብዬ ግድም አልሰጠኝ ነበር። ከዚህ በፊት የማውቀው ሽቶ ሲሸተኝ ግን ፊቴን ካዞርኩበት ግድግዳ ወደበሩ አየሁ..ትሩፋት ናት። እዛው አልጋ ላይ ለዘላለም ባሸልብ ተመኝቼ ነበር። እናቴን በታቦቷ፣ ሚስቴን በልጆቿ ያስገዘትኩት እኮ ይቺ ሴት ከጠያቂ ጋር ተቀላቅላ እንዳትመጣብኝ ነበር። ነውሬን ለመሸፈን የሆነ ህመም እንዳገኘው መስዬ የሌለብኝን ማቃሰት ጀመርኩ።
በስስት..በስስት ብቻ አይደለም የሞተ መሽኒያዬን ባነቃቃ የስስት እይታ ለለቅሶ በቀረበ ድምጽ ‹ምን ሆንክብኝ የኔ ጌታ? ስትል ከንፈሬ ላይ ሳመችኝ። እናትና ሚስቴ አለመኖራቸው ከብዙ መከራ እንደታደገኝ አመንኩ። ይሄ ቅጽበት በምድር ላይ ከምንም የከፋ አስጠሊታ እንደሆነ ማንም ያውቀዋል። መቼም የሚነቃ የማይመስለው የተገረዘው መሽኚያዬ በዛ የስስት ድምጽ ከሞተበት ሲነሳ እያፈርኩ ነበር። በመሽኒያዬ ንቅናቄ በፋሻ የተጠቀለለ ጉያዬ የበለጠ ህመም ተሰማው።
ምን ሆንክ? ስትለኝ ምን ሆንኩ እንደምል ግራ ገባኝ። ክንብንቤን ገልቤ ጉያዬን አላሳያት ነገር። በእሷ ምክንያት ልገረዝ ሆስፒታል እንደገባሁ እንዳታውቅ ሁሉንም አይነት ጥረት አድርጌ ነበር። ይሄ የውንብድናዬ ምዕራፍ አንድ ቅጣት እንደሆነ አልጠፋኝም። የትኛው ደመኛዬ ያለሁበትን ነግሯት እንደመጣች ከአልጋ ከተነሳሁ በኋላ አጣራዋለሁ። ከዚች ሴት ውጪ መላው የዓለም ሕዝብ መጥቶ ቢጠይቀኝ የማልሰጋ ነኝ። በእሷ ምክንያት ለዚህ እንደበቃሁ የሚያውቅ ማንም የለም። እሷ ራሷ አታውቅም። ይቺን ሴት ወድጄ ለግርዛት ሆስፒታል እንደገባሁ ቢታውቅብኝ እናቴና ሚስቴ ከአምስት ልጆቼ ጋር ተባብረው እዛው ሆስፒታል አልጋ ላይ ያስቀሩኝ ነበር። ድንገት ነው ትውውቃችን..የመኪና ነዳጅ ልቀዳ ወደነዳጅ መቅጃ ስነዳ ቀድማኝ ከደረሰች ወጣት ሴት ጋር መተዋወቅ ግድ ሆነ። ነዳጅ መቅጃው ስራ ቦታ አቅራቢያ ስለሆነ ባሰኘኝ ሰአት እሄዳለው፣ ከዚህ በፊት የማላውቃት ወጣት ሴት እንደእሷ በቆነጀች መኪናዋ እየመጣች ለብዙ ጊዜ ተገናኘን። ከዚች ሴት ፍቅር ይዞኛል..በሚስቴ ላለውጣት ብርቱ ጥረት ላይ ነኝ። በዚህ ነውሬ እዛች ጋለሞታ ላይ ምን እሆናለሁ ስል ለሽንሸና ሆስፒታል ገባሁ።
ጭንቅ ውስጥ ሳለሁ እናቴ ከተፍ አለች። አስቀድሜ ማንም እንዳይመጣብኝ አደራ ስላልኳት ክፍሌ ውስጥ ሌላ ሴት ማየቷ ከኔ በላይ ሳያስደነግጣት አልቀረም። በምን ብልሀት እንደሆነ እንጃ የሆነ ነገር በጆሮዋ ሹክ ብላት ከክፍሌ አስወጣችልኝ። በምን መላ እንዳስኮበለለቻት ይሄም ስነሳ የምጠይቃት ይሆናል።
የጠያቂዬን እግር ተከትሎ ዶክተሩ ገባ። እሱ ሲገባ እናቴ ወጣች። በህክምና ዓለም አካሚ ሲገባ አስታማሚ እንዲወጣ የሚያደርግ ሥርዓት ይኖር ይሆን? ይሄ ታማሚና አስታማሚ ባለበት የታዘብኩት ትዝብቴ ነው።
የዶክተሩ እጅ ሙቀቴን ሊለካ ግንባሬ ላይ ሲያርፍ ‹ግርዛትና ትኩሳት ምን አገናኘው? እያልኩ ነበር። የእጅ ልስላሴው እንዴት ደስ ይላል መሰላችሁ። ሴት በሆነ ያስብላል። ክፉ ቀን የሚባሉት እንዲህ ያሉ እለቶች ናቸው። ሴትን በወንድ ቀይረው ጉያ ግድም የሚያገድሙ። በብሽቀት ደንቃራ እለተ ሀሙስ አልኩ። ቆንጆ ዶክተር ገርዛኝ ቢሆንና ሙቀቴ የተለካው በእሷ አይበሉባ ቢሆን የሚሆነውን አስባችሁታል? እረ እንኳንም አልሆነ..
አንዳንድ ፊቶች፣ አንዳንድ መዳፎች የመልከ ጸዲቅን ያህል የህይወት ህብስቶች ናቸው። ከህመሜ የማገግመው በዛ ዶክተር መዳፍ ስዳበስ እንደሆነ ሳስብ ሀፍረቴ ይመጣል። አሁን አሁን እንዲመጣ ሌላ ህመም ታክሎብኝ አልጋ ብውል ስል የቂል ሃሳብ አስባለሁ። እንኳንም ሴት አልሆነ..ሴት ሆኖ ቢሆን ኖሮ?
ህክምና እንደተረዳነውና እንደምንረዳው አልመስልህ አለኝ። ከሚታዘዘው መድኃኒት በላይ አይዞህ የታከለበት በአይን የሚገባ የሀኪም ጥቅሻ ዋጋ እንዳለው አሰብኩ። ይሄ ዳሳሽ መዳፍ የሴት ቢሆን ኖሮ ወይ ለዘላለም የአልጋ ቁራኛ ሆኛለሁ አልያም ለሰላሳ ሰባት አመት ሙሉ ደዌ እንዳጠቃው በኋላም መዳን ትሻለህ? በምትል ላመል መጠይቅ አልጋውን ተሸክሞ እንዲሄድ እንደታዘዘው መጻጉ ከነበርኩበት 37 ቁጥር የህሙማን ክፍል በዳንኩ ነበር። እኔ የተኛሁበት እና መጻጉ የተጎሳቆለበት ቁጥር እኩል 37 መሆኑ ሌላ ግርምቴ ነበር። በተሰጠን በጎ እለትና ብሩካን አጋጣሚ ፊት ምኞታችን ፈር ይስታል..እንዴት ላለኝ እንዲህ እለዋለሁ..ዛሬ ነገ ሲሆን፣ ጨረቃ የወጣች እለት ጽልመቶቻችንን የገለጡ ማሾዎቻችን ትዝ አይሉንም። ጸደይ በክረምት ሲፈካ፣ ዘንድሮ ድሮን ሲሽር፣ ጣፋጭ ተረቶቻችን ለአፌን በዳቦ ሲደርሱ ኮቴዎቻችን ተራማጅ ያጣሉ። ወጀቦቻችን ከህልማችን ሲርቁ፣ ደመናዎቻችን ከበላያችን ሲሰወሩ ቁም ነገር እንደቀልድ ያምጣል። አፍላነት ጋለሞታነት ሲያጠቃው፣ ሃሳብና ምኞት ልጅነት ሲከለል፣ ለጋ ቅርንጫፎች አጎጤ ሲያጎጠጉጡ የነበረው ባልነበረ ይዋጣል። መጽናናት የቸረኝን የዚህን ዶክተር መዳፍ ውለታ ሽሬ ከሴት ሀኪሞች የአንዷን በሆነ ብዬ መመኘቴ አለመርባት አይደል?
መሽኒያዬ አገግሞ ከሆስፒታል ወጣው። ቀጣይ ቀጠናዬን ወደማን እንደማደርግ እንጃ። ከዛ ለውጥ በኋላ አእምሮዬ የማይረባ ነገር እያሰበ ራሴን እንድቀየመው አደረገኝ። በሚስቴ ወይስ በትሩፋት አስተማማኝነቱን በማን እንደምሞክረው ልቤ ቆሻሻ ሃሳብ ያስብ ገባ። አንዳንድ ለውጦች ለነውር ካልሆነ ለምንም የማይበጁ ሆነው ወደህይወታችን ይመጣሉ። አስበን ካልተራመድን እንኳን ደስ አላችሁ ተብለን ለገጸ በረከትነት የተሰጡን አበባዎች የቀብራችን እለት ከትራስጌያችን ከሚቀመጡት የአበባ ጉንጉን የማይሻሉ ናቸው።
ህክምና መሰንበቴን የሰሙ ጎረቤቶቼ ስንቅ እየቋጠሩ ቤታችን መጉረፍ ጀመሩ። ይሄን ስለማውቅ ነገሩ እስኪረሳ ለሳምንት ቤተሰቦቼ ቤት አልገባሁም። ‹እንዳው ምን አገኘው? ምኑን ታሞ ነው? ሲሉ ‹ቀላል ነው..የሆነ ነገር አመም አድርጎት› ከሚል የእናቴ ማስመሰል በቀር ሊገረዝ ገብቶ ነው የሚል ጠፋ። ጥያቄው ሲያይልባት እናቴ ‹ቁርጥማቱ ተነስቶበት ነው› ስትል ታብላለች። ክብር ለዛ ዶክተር መዳፍ ይሁንና..በመሽኒያዬ መታደስ ልዩ ፍጡር መስዬ ከረምኩ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)