በየትኛውም ሀገር የስፖርት ዘርፍ ልማት ውስጥ ጠንካራ የስፖርት ፖሊሲ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። የፖሊሲው መኖር ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እና ያንንም ማስፈጸም የሚያስችል ብቃት ያለው አደረጃጀት መኖሩም የግድ ነው። ለአንድ ምዕተ ዓመት የተቃረበ ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ስፖርት፤ ፖሊሲ ተቀርጾለት በሥራ ላይ ከዋለ 27 ዓመታትን አስቆጥሯል። በእነዚህ ዓመታትም ስፖርቱን በማስፋፋት እንዲሁም ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ውጤቶችን ማግኘት ተችሏል። ይሁን እንጂ ስፖርቱ ባሉበት ውስብስብ ችግሮች ምክንያት በሚፈለገው የእድገት ደረጃ ላይ ሊገኝ አልቻለም።
የስፖርቱ ባለሙያዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ስፖርት ዙሪያ የተሠሩ ጥናቶችም ለሦስር አስርት ዓመታት በተጠጋው ጊዜ ሀገር አቀፍ ፖሊሲው በትክክል ሊተገበር ባለመቻሉ ሊሻሻል ወይም ሊከለስ እንደሚገባው ያመላክታሉ። ከጥቂት ዓመታት በፊት የተዘጋጀው ሀገራዊ የስፖርት ሪፎርም ጥናትና ፕሮግራምም ይህንኑ ያመላከተ ነበር። ፖሊሲው እጅግ መሠረታዊ የሆኑ የስፖርት ልማት አጀንዳዎችን ቢያቅፍም የተሠሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲሁም ፖሊሲውን ለማስተዋወቅ የተደረጉ ሙከራዎች ውስን በመሆናቸው አመራሩ፣ አስፈጻሚው አካል እንዲሁም በህዝቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤም አነስተኛ ሊሆን ችሏል። ፖሊሲውን ለማስፈጸም የሚያስችል መንግሥታዊና ሕዝባዊ አደረጃጀትም እስከታችኛው እርከን ማዋቀር መቻሉም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ ነው።
ፖሊሲው ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ የዓለምም ሆነ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በብዙ መልኩ መቀየሩንም ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው። ስፖርት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ በሆነበት በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ፤ የስፖርት ንግድን በዓላማ ደረጃ አለማስቀመጡ ከክፍተቶቹ መካከል ይመደባል። የትኩረት ማዕከሉን በመንግሥታዊና ሕዝባዊ አደረጃጀት ብቻ የወሰነው ይህ ዘርፍ የግል ባለሀብቱን ሚና መዘንጋቱ በእድገቱ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማድረሱም እየተስተዋለ ነው። ስለሆነም ፖሊሲውን ከዓለም አቀፍና ወቅታዊ ሁኔታዎች አንጻር መሠረታዊ ነጥቦችን በመፈተሽ ማስተካከልና መከለስ አስፈላጊ መሆኑን ሪፎርሙ አስገንዝቧል።
በ2012 ዓ/ም በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት የተዘጋጀው ይህ ሪፎርም ያመላከታቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ሳይተገበሩ እስካሁን መቆየታቸው ለስፖርቱ ቤተሰብ ጥያቄ ነው። ከሰሞኑ የተዘጋጀ አንድ መድረክም ለዓመታት ሥራ ላይ የቆየውን የስፖርት ፖሊሲ ለማሻሻል እና አዲስ ረቂቅ የስፖርት አዋጅ የሚመለከት የባለሙያዎች ውይይት ተደርጓል። በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፤ መንግሥትና የሀገሪቱ ሕዝብ የስፖርት ልማትን በማሳደግ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ለማግኘት እንዲቻል በሥራ ላይ ያለውን የስፖርት ፖሊሲ እና አዲስ የስፖርት ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ግብዓት ለማሰባስብ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል። ንቁ ዜጋና አሸናፊ ሀገርን ለመገንባት ዘርፉ የሚመራበትን የሕግ ማዕቀፍ በመተግበር፤ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ መሰል መድረኮች አስፈላጊ እንደሆኑንም አንስተዋል።
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው፣ ‹‹ሀገራችን ስፖርቱን በሚገባ እንዳታለማ በፈተናዎች እየተፈተነች ስለሆነ ከዚህ ችግር በዘላቂነት ለመላቀቅ የስፖርት ፖሊሲና አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል›› ብለዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በቀረቡት ሰነዶች ላይ መካተት አለባቸው ያሏቸውን ሃሳቦች ያነሱ ሲሆን የስፖርቱን ዘርፍ ለማሳደግ የቀረቡ ሰነዶች በታሰበው ልክ ቢሻሻል እምርታዊ ውጤት እንደሚያመጣ መጠቆማቸውን የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር መረጃ ያሳያል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም