በአይጥ መንጋ የተማረረችው የአሜሪካዋ ኒውዮርክ ከተማ ለአይጦች የወሊድ መከላከያ ልትሰጥ ነው

በአይጥ መንጋ የተቸገረችው ግዙፏ ሜትሮፖሊታን ከተማ ኒውዮርክ የወሊድ መከላከያዎችን ለአይጦች ልትሰጥ መሆኑ ተሰምቷል።

በሙከራ ደረጃ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል በተባለው የመፍትሄ ሃሳብ በርካታ አይጦች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የወሊድ መቆጣጠርያ ክኒኖችን በምግብ ውስጥ በመደበቅ አይጦች እንዲመገቡት ይደረጋል ተብሏል።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ በአይጥ መንጋ እየደረሰ በሚገኘው ጥፋት እና በሰዎች ላይ እያስከተሉ ከሚገኙት የጤና እክል ጋር በተያያዘ የከተማዋ ከንቲባ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው እንደነበር ይታወሳል። ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ባለሙያዎች በተካፈሉበት ስብሰባ ላይ የአይጦችን ቁጥር ለመቀነስ በመርዝ እና በተለያዩ መንገዶች ለማጥፋት የመፍትሄ ሀሳብ ቀርቦ ነበር።

ሆኖም ከአይጦቹ ከፍተኛ ቁጥር ጋር በተያያዘ በመርዝ መግደል በጤና እና በአካባቢ ላይ ከሚያስከትለው ብክለት ጋር በተያዘ እንዲሁም የሞቱ አይጦችን በሚመገቡ እንስሳት ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመቀነስ የወሊድ መከላከያው የተሻለ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል።

በዚህ ዙሪያ የሚሰሩ ባለሙያዎች በ2025 12 ወራት ውስጥ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ውስጥ ክኒኖቹን በማስቀመጥ ምን ያህል መድኃኒቶች በአይጦቹ እንደተወሰዱ በመከታተል የመራባት ምጣኔያቸውን ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ ተብሏል።

“ሴኔስ ቴክ” የተባለው የወሊድ መቆጣጠርያ መድኃኒቱን የሚያመርተው ኩባንያ እንዳስታወቀው፤ መድኃኒቱን የሚወስዱ አይጦች ለ45 ቀናት ያህል እንዳይራቡ የሚያደርጋቸው ነው።

በኒውዮርክ የሚርመሰመሱ አይጦች ለነዋሪዎቿ እና ለከተማዋ አስተዳደር ራስ ምታት ከሆኑ ሰነባብተዋል።

የከተማዋ ጤና ተቋማት ከአይጦች እና ከሌሎች ነፍሳት ጋር በተገናኘ የሚከሰተው “ሌፕቶስፓይሮሲስ” የተሰኘው በሽታ እየተበራከተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

“ሌፕቶስፓይሮሲስ” ከአይጦች እና ከሌሎች እንስሳት በሚወጡ ፈሳሾች ከተበከለ ውሀ፣ አፈር እና ምግብ ጋር በሚኖር ንክኪ የሚፈጠር ባክቴርያ ሲሆን፤ ምልክቶቹ የሆድ ህመም፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ራስ ምታት እና የጡንቻ ህመም ናቸው።

በ2023 መጨረሻ የወጡ መረጃዎች በኒውዮርክ ሶስት ሚሊዮን አይጦች እንደሚኖሩ ሲጠቁሙ፤ 7 ሚሊዮን 931 ሺህ ሰዎች በሚገኙባት ከተማ የአይጦች ቁጥር አጠቃላይ የከተማዋን ነዋሪዎች ቁጥር ግማሽ ለመድረስ የተቃረበ ነው።

ሆኖም ኒውዮርክ ከአሜሪካ ከተሞች በአይጦች ብዛት ቀዳሚዋ አይደለችም ፤ ይህን ደረጃ ይዛ የምትገኘው ቺካጎ ስትሆን ሎስአንጀልስ ደግሞ ሁለተኛ ነች።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የህንዷ ዴሽኖክ ከተማ እና የእንግሊዟ ለንደን የቀዳሚ እና ተከታዩን ስፍራ ይዘዋል።

ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ የፍቅር ከተማ ተብላ የምትጠራው የፓሪስ ነገር ነው። በፓሪስ 2 ሚሊዮን 100 ሺህ ሰዎች ሲኖሩ፤ የአይጦች ቁጥር ደግሞ 6 ሚሊዮንን ይሻገራል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You