የየመኑ ሃውቲ በማዕከላዊ እስራኤል በምትገኘው የወደብ ከተማ ጃፋ ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ።
የሃውቲ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ በትናንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ የቡድኑ ድሮኖችን ኢላማቸውን መምታታቸውን ተናግረዋል።
የሃውቲ ድሮኖች “ከእስራኤል የራዳር እይታ ውጪ በመሆን እና ሳይመቱ የጠላትን ወሳኝ ኢላማዎች መተዋል” ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ቡድኑ በቴል አቪቭ ላይም ተመሳሳይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን ያነሱት ቃል አቀባዩ፥ ተመተዋል ስለተባሉት ኢላማዎች ግን ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ከትናንት በስተያ “ቁድስ 5” በተሰኘው ሮኬት እስራኤልን አጥቅተናል ያሉት ያህሳ ሳሪ፣ ቴል አቪቭ በጋዛ እና ሊባኖስ የጀመረችውን ጦርነት ካላቆመች ጥቃታችን ይቀጥላል ሲሉ ዝተዋል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ የሃውቲ ድሮኖች በማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍል አየር ላይ ተመተው መውደቃቸውን በመግለጽ “ኢላማቸውን መተዋል” በሚል በየመኑ ቡድን የወጣውን መግለጫ ውድቅ አድርጓል።
እስራኤል በጋዛ ከሃማስ ጋር ጦርነት ከጀመረች ወዲህ በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የሊባኖሱ ሄዝቦላህ፣ የየመኑ ሃውቲ እና የኢራቅ ታጣቂ ኃይሎች በቴል አቪቭ ላይ ጥቃት ሲያደርሱ ቆይተዋል። የጋዛው ጦርነት አንደኛ ዓመቱን ሊደፍን ቀናት በቀሩበት ወቅት እስራኤል የሄዝቦላህ መሪዎችን በመግደል በሊባኖስ የእግረኛ ውጊያ መጀመሯን ተከትሎም ቡድኖቹ የተቀናጀ እርምጃ በመውሰድ ላይ ናቸው።
በቀይ ባህር በሚጓዙ ከ80 በላይ መርከቦች ላይ የሚሳኤል እና ድሮን ጥቃት ያደረሰው የየመኑ ሃውቲ ከሰሞኑም ጥቃቱን አጠናክሯል።
ከቀናት በፊትም ከኢራቁ “ኢስላሚክ ሬዚስታንስ” ጋር በመቀናጀት በእስራኤሏ ሃይፋ ከተማ ላይ የሚሳኤል ጥቃት ማድረሱን ማስታወቁ ይታወሳል።
እስራኤልም ባለፈው እሁድ ቡድኑ ከኢራን የጦር መሳሪያ ያስገባበታል ባለችው የሆዴይዳህ ወደብ ላይ ጥቃት አድርሳ ስድስት ሰዎች መሞታቸውና ከ57 በላይ መቁሰላቸው አይዘነጋም።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም