አዲስ አበባ፡– ኢሬቻ የገዳ ሥርዓትን መሰረት አድርጎ የሚከበር በመሆኑ ማንኛውንም ፖለቲካዊ መልዕክቶች ማስተላለፍ የተከለከለ መሆኑን የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፤ ኢሬቻ የገዳ ሥርዓትን መሰረት አድርጎ የሚከበር በመሆኑ ማንኛውንም ፖለቲካዊ መልዕክቶች ማስተላለፍ በአባገዳዎችና ሀደሲንቄዎች የተከለከለ ነው።
ኢሬቻ ከገዳ ሥርዓት የተገኘ የእርቅ፣ አብሮነት፣ የሰላም፣ የወንድማችነትና የአንድነት በዓል ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ በዓሉ የሕዝቦችን አንድነት፣ ፍቅርና ወንድማማችነት በሚያጠናክር መልኩ የሚከበር ነው ብለዋል።
ኢሬቻ ወጉን ባህሉንና ዕሴቱን ጠብቆ እንዲከበር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በዓሉ ባህላዊ ዕሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበርም ከበርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተደረገ ውይይት መግባባት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።
የበዓሉ ታዳሚዎች ያለ ሃይማኖትና ፖለቲካ ልዩነት በጋራ መጥተው ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ብቻ ማክበር እንዳለባቸው በመግለጽ፤ ኢሬቻ የአንድነት የጋራና የወንድማማችነት በዓል በመሆኑ ያለምንም ልዩነቶች እንደሚከበርም ተናግረዋል።
በበዓሉ ማንኛውም የፖለቲካ መዝሙሮች፣ ባንዲራዎች፣ ምልክቶችና አርማዎች በቦታው መታየት እንደሌለባቸው የገለጹት ኃላፊዋ፤ በዓሉ የገዳ ሥርዓትን መሰረት አድርጎ የሚከበር በመሆኑ ማንኛውም የፖለቲካ መልዕክቶች አይተላለፉበትም ብለዋል።
አባ ገዳዎች ባስተላለፉት መሠረት የሕዝቦችን አንድነት፣ አብሮነትና ወንድማማችነት የሚያንጸባርቁ መልዕክቶች ብቻ መተላለፍ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
በኢሬቻ በዓል ላይ ከአባ ገዳ ሰንደቅ ዓላማ ውጪ ሌሎችን ይዞ መገኘት የተከለከለ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በተለይም ከገዳ ሥርዓት ዕሴትና ወግ ውጪ የሆኑና እርስ በእርስ የሚያጋጩ መልዕክቶች፣ አልባሳት፣ ዜማዎች የማይፈቀዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዓሉ ባህላዊ ዕሴቱን ጠብቆ የሕዝቦችን አንድነት፣ አብሮነትና ወንድማማችነት በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር በመግለጽ፤ በበዓሉ ላይ ለመታደም ዲያስፖራዎች፣ ብሔር ብሔረሰቦች፣ የውጪ ዲፕሎ ማቶች እንደሚሳተፉበትም ተናግረዋል።
የኢሬቻ በዓል የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከፍ ከማድረግ፣ የቱሪዝም ዘርፍን ከማነቃቃት አኳያ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ በዓሉ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በበዓሉ ለመታደም ለሚመጡ እንግዶች አቀባበል ለማድረግም የአዲስ አበባ፣ ሸገርና በቢሾፍቱ ከተሞች በርካታ የዝግጅት ሥራዎች መሥራታቸውን የገለጹት ኃላፊዋ፤ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን ጨምሮ መላው ሕዝብ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በጋራ በመሆን የሆራ ፊንፊኔን የማጽዳትና ለሥርዓቱ ምቹ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም ጠቁመዋል።
የበዓሉን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ባህልና ዕሴቱን ለማስጠበቅ ሕዝብን በአሳተፈ መልኩ ዝግጅት መደረጉን በመግለጽ፤ በዓሉ ላይ የሚታደሙ እንግዶች ድንገተኛ የጤና እክል የሚያጋጥሙ ከሆነም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም