አዲስ አበባ፡– የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሊመራ የሚችል የሎጂስቲክስ ዘርፍ ለማደራጀት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የባቡርና የመንገድ ሎጂስቲክስ አገልግሎቶች ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ባጠናው ጥናት ላይ ትናንት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ በአፍሪካ ውስጥ ፈጣን እድገት ከሚያስመዘግቡና ለጥቅል ሀገራዊ ምርት አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱ ዘርፎች መካከል አንዱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ነው።
ኢትዮጵያ ከዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ እንድትሆን የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ የሚደረጉ ማሻሻያዎችን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል።
የሎጂስቲክስ ዘርፉ ኢኮኖሚውን መምራት በሚችል በት ሁኔታ የማደራጀት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ አሠራርን የማዘመን፣ የባቡርና የተሽከርካሪ ቁጥር የመጨመር፣ ዘርፉን በቴክኖሎጂ የመደገፍ፣ የገንዘብ እና ቴክኒካል ድጋፍ ማድረግ ከሚሠሩት ሥራዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
መንግሥት አሠራርና መመሪያዎችን የማሻሻል፣ የልማት አጋሮች የገንዘብና ቴክኒካል ድጋፍ የማድረግ እንዲሁም የግሉ ሴክተር በዘርፉ እንዲሰማሩ የማበረታታት ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
የዘርፉን ተግዳሮት በመፍታት ሀገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ በባቡርና በመንገድ የጭነት አገልግሎት ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት ተጠንቶ የመፍትሄ ሃሳብ እንደቀረበበትም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ ወደተግባር የገባው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያም በርካታ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶችን ለማሳካት እና ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ እድገት ተስፋ ሰጪ ውጤት የሚያስገኝ በመሆኑ በአግባቡ መተግበር ይገባል ብለዋል።
ሎጂስቲክስ የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ የደም ስር መሆኑን ገልጸው፤ የውጭ ባለሀብቶች በአንድ ሀገር ኢንቨስት ለማድረግ ሲወስኑ ቀድመው የሚያዩት የሎጂስቲክስ ዋጋን መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ አሠራር ያለመዘመን፣ የመለዋወጫ እጥረት፣ በኢትዮጵያ ባሉት ባቡሮችና መስመሮች በሙሉ አቅም ያለመሥራት፣የግንዛቤ ውስንነት እና ሌሎች ችግሮች መኖራቸው ሀገሪቱ በዘርፉ ተጠቃሚ እንዳትሆን አድርጓታል ብለዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ የኢትዮጵያ የባቡር መስመሮች አጥር ስለሌላቸው እንዲሁም በአብዛኛው የሚያልፉት በአርሶና አርብቶ አደር አካባቢዎች በመሆኑ በእንስሳት ላይ አደጋ ሲደርስ የካሳ ጥያቄው የባቡሩን እንቅስቃሴ እያስተጓጎለው ነው።አንድ ባቡር በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር መጓዝ እያለበት አደጋ ላለማድረስ በሰዓት ከ40 ኪሎ ሜትር በታች እየሄደ ቅልጥፍናውን ገድቧል ነው ያሉት፡፡
የባቡር መስመር ሲገነባ የሎጂስቲክሱን አብዛኛውን ሸክም እንዲሸከም ታስቦ የተገነባ ቢሆንም፤ አሁን ላይ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው ከ14 በመቶ አይበልጥም።ከ84 በመቶ በላይ የሚሆነው በጭነት ተሽከርካሪ የሚጓጓዝ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገ ያለ ሀገር ነች ያሉት አለሙ (ዶ/ር)፤ በዚሁ ልክ የወጪና ገቢ ንግዷ ስላደገ ጂቡቲ ወደብ ላይ የሚደርሱ እቃዎች ቶሎ ያለመጫን፣ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ያለመድረስ እና ሌሎች ተግዳሮቶች እያጋጠሙ ነው ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ የባቡር ቅልጥፍና አለመኖር፣ የመለዋ ወጫ እጥረት፣ እና የተሽከርካሪ ቁጥር ማነስ ለዘርፉ ተግዳሮት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚመራ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ለማደራጀት የመንግሥትን፣ የልማት አጋሮችን፣ የግሉን ሴክተር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንደሚጠይቅ አሳስበዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላ ቸው እንደገለጹት፤ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በዓለም አቀፍ ገበያዎች ለመሳተፍ ወሳኝ በመሆኑ ዘርፉን ለማሳደግ እየተሠራ ነው።
በዘርፉ ከመንግሥት በተጨማሪ የግሉ ሴክተር ንቁ ተሳትፎ ማድረግ፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን ማሳለጥና ማጠናከር እንደሚገባ አስታውቀዋል።
በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ማርያም ሳሊም በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ያለው ተጎታች የሎጂስቲክስ ዘርፍ በወቅታዊ የንግድ ፍሰት እና ለወደፊት የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ ማነቆ መሆኑን የዓለም ባንክ ሪፖርት ይጠቁማል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷ 30 በመቶ የሚሆነውን ለሎጂስቲክስ እንደምታወጣ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ የተሳለጠና የተጠናከረ የሎጂስቲክስ ሥርዓት እንድትገነባ ዓለም ባንክ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም