አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና የፌዴራል ጉምሩክ ኮሚሽን በተለያዩ ጉዳዮች አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
የሁለትዮሽ የመግባቢያ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መሳፍንት ተፈራ እና የፌዴራል ጉምሩክ ኮሚሽን አቶ ደበሌ ቃበታ ፈርመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መሳፍንት ተፈራ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ ኢፕድ በሚዲያና የንግግር ነጻነት ታሪክ ቀዳሚ የሚዲያ ተቋም መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ፈር ቀዳጅ የሆኑ የዘመናዊ ኢትዮጵያ የለውጥ አቀንቃኞች ከመሰረቷቸው ተቋማት መካከልም አንዱ ኢፕድ ነው ብለዋል።ተቋሙ ለዴሞክራሲና ለሀገር ለውጥ እንዲሁም ለንባብ ባህልና ለታሪክ ሰነድነት ትልቅ ድርሻ ያለው እንደሆነም አመላክተዋል።በተመሳሳይ የፌዴራል ጉምሩክ ኮሚሽንም በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ፈር ቀዳጆች ከጀመሯቸው ትላልቅ ተቋማት ውስጥ አንዱ መሆኑን በመግለጽ፤ ታሪክን መነሻ ባደረጉ ጉዳዮች ውጤት ተኮር የሆኑ ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ የብዙ ታሪክ ባለቤት እንደመሆኑ፤ ለኢትዮጵያ እንዳበረከተው አስተዋጽኦ ሕዝቡ እንዲቀ በለውና የሚያከናውናቸው የሀገር ታሪክ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ወደ ሚዲያው እንዲቀርብ ይደረጋልም ነው ያሉት።ኢትዮጵያ የተሠራችው በብዙ መስዋዕትነት መሆኑን ጠቁመው፤ ጉምሩክ ላይ የሚሠሩና ለሀገር ብለው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህን ታሪኮች ለትውልዱ ሰንዶ ማስተላለፍ እንደሚገባም ገልጸዋል።የጉምሩክ ሥራ በዘመናዊ ታሪክ ተጀመረ ቢባልም ጥንታዊም ነው በማለት፤ ኢፕድም ፎቶግራፍና ህትመቶችን ጨምሮ በርካታ የታሪክ ሀብቶች እንዳሉትና ይህንኑ የካበተ ልምድ በመጠቀም ትውልዱ በተቋሙ ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ የበለጠ እንዲያውቅ ከኮሚሽኑ ጋር ይሠራል ነው ያሉት። የፌዴራል ጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ትላልቅ አቅም ካላቸውና ከተመረጡ ተቋማት ጋር መሰል ስምምነቶችን እንደሚያደርግና ከኢፕድ ጋር አብሮ ለመሥራት ያደረገው ስምምነትም ለተቋም ግንባታ ትርጉም ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ዕድሜ ጠገብ ሥርዓተ መንግሥት እንዳላት ሁሉ፤ እውነተኛና ጠንካራ መሠረት ያለውን ረጅም ለትውልድ የሚተላለፍ ተቋም መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።ለዚህ ደግሞ እንደ ኢፕድ አይነት ትልቅ አቅም ካላቸው ተቋማት ጋር አብሮ መሥራት ወሳኝ ነው ብለዋል።የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በውስጡ ረጅም ታሪክና የበለጸገ የዕውቀት ሀብት እንዲሁም የካበተ ልምድ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ልምድ በመጠቀም ለትውልድ የሚበጅ የተናበበ ሥራ አብሮ ለመሥራት አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።የመግባቢያ ስምምነቱ ሀገር አቀፍ የሁነት ዝግጅቶች እና የፎቶግራፍ አውደ ርዕዮችን፣ የፓናል ውይይቶች እና ሀገራዊ ንቅናቄዎችን፣ የህትመት ሥራዎች ማለትም መጽሐፍ፣ መጽሔት፣ ፕሮሲዲንግ ዝግጅቶችና ትምህርታዊ አምድን፣ የዶክመንቴሽን እና የፕሮዳክሽን ሥራዎችን፣ የተለያዩ የክህሎት እና አመለካከት ስልጠ ናዎችን በጋራ ለማከናወን የሚያስችል ሲሆን፤ የግንዛቤ ሥራዎቹ ያመጡትን ውጤቶች ጥናትና ምርምር እንደሚደረግባቸው ታውቋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም