አዲስ አበባ፡– በሕዝቦች መካከል ያለው የባህልና የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከር የቱሪዝምና የሰላም ቁርኝት ወሳኝ ነው ሲል የኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ በዓለም ለ45ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ37ኛ ጊዜ ቱሪዝምና ሰላም በሚል መሪ ሃሳብ የተከበረውን የዓለም ቱሪዝም ቀን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ተወያይቷል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በሕዝቦች መካከል ያለው የባህልና የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከርና ማህበራዊ መስተጋብራቸው እንዲጨምር የቱሪዝምና የሰላም ቁርኝት ወሳኝ ነው፡፡
በየዓመቱ የሚከበረው የዓለም የቱሪዝም ቀን በተለይም ቱሪዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳዎችና ጥቅሞች ዙሪያ በየደረጃው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገቢውን ግንዛቤ እንዲጨብጡ ለማድረግ ዓላማ ያለው ነው ብለዋል፡፡
ቱሪዝም በከተማና በገጠር መካከል የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ትስስር እንዲኖር ከማድረግ አኳያ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጥናቶች ማመልከታቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ የቱሪዝም ዘርፉ የሥራ ዕድሎችን የመፍጠር አቅምና ችሎታ ያለው ዘርፍ ከመሆኑም በላይ ዘርፉ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችን በመንከባከብና በማስተዋወቅ እንዲሁም ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና ያለው ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግሥት በሚከተለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ለሀገሪቱ አስተማማኝ የሀብት ምንጭ ይሆናሉ ተብለው ከተመረጡት አምስት ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ የቱሪዝም ዘርፉ አንዱና ዋንኛው እንደሆነ ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ኢንስቲትዩቱ ሀገራዊ ሪፎርሙን ተግባራዊ በማድረግ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል በማፍ ራት፣ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ በበኩላቸው፤ ቱሪዝም ያለ ሰላም ውጤታማ መሆን አይችልም፤ ቱሪዝምን ለማሳደግ ሰላምን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ቱሪዝምና ሰላም የማይነጣጠሉ ጉዳዮች ስለሆኑ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን ሰላም ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ወቅቱን የጠበቀ ነው ብለዋል፡፡
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም