በሊባኖስ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡በሊባኖስ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየሠራ መሆኑን ብሔራዊ ኮሚቴው አስታወቀ፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ሰብሳቢነት የሚመራ 16 የፌዴራል ተቋማትን ያካተተው ብሔራዊ ኮሚቴ በሊባኖስ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ደህንነታቸው ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይቷል።

የብሔራዊ ኮሚቴው አባላት በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ባለው ዝግጅት ላይ ሰፊ ጊዜ ወስዶ የመከረ ሲሆን፤ በቤይሩት የሚገኘው ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤት እያካሄደ ያለውን የዜጎች ምዝገባ ወቅታዊ ሁኔታ ፈትሿል።

ቆንስላ ጀኔራል ጽህፈት ቤት እያደረገ ያለውን ምዝገባ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ሰፊ ርብርብ እንዲደረግ አቅጣጫ ተቀምጧል።

የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ኮሚቴው በቀጣይ ጊዚያት በሊባኖስ ወቅታዊ ሁኔታ ደህንነታቸው ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የተገኙ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም ለመመለስ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው ብለዋል።

ይህን የአስቸኳይ ጊዜ ሥራ በተሻለ ፍጥነት መከወን እንዲቻል ተጨማሪ የሰው ኃይል ወደ ቤይሩት እንደሚላክም ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ቆንስላ ጀኔራል ጽህፈት ቤቱ ባዘጋጀው አደራሻ በሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎቻችን ምዝገባቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በቀጣይም መንግሥት ለዜጎች በሚደረገው ክትትል እና ድጋፍ ዙሪያ በዋናው መሥሪያ ቤት፣ በቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት እንዲሁም በኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ አደረጃጀቶች በኩል መረጃ እንደሚያደርስ አሳውቀዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You