አዲስ አበባ፡– የጤና ቅድመ ምርመራ ባህልን በማዳበር ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጉዳት ሳያደርሱ አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባ ረዳት ሄልዝ ኬር አስታወቀ።
ረዳት ሄልዝ ኬር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሠራተኞች የነጻ የጤና ምርመራ እና የምክር አገልግሎት በትናንትናው ዕለት ሰጥቷል።
በምርመራ መርሀ ግብሩ ላይ የረዳት ሄልዝ ኬር ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ምስጋና ሰለሞን እንደገለጹት፤ በማህበረሰቡ ዘንድ ቅድመ ምርመራ ላይ ያለ ግንዛቤ አናሳ ነው። ይህንን ለመቅረፍም ረዳት ሄልዝ ኬር በህክምናው ዘርፍ በመሰማራት ቅድመ ምርመራ እና መከላከል ላይ በማተኮር እየሠራ ይገኛል።
በብዙዎች ዘንድ በበሽታዎች ሲያዙ እንጂ ለቅድመ ምርመራ ወደ ህክምና ተቋማት የመሄድ ባህል ዝቅተኛ ነው ያሉት ወይዘሮ ምስጋና፤ ተቋሙ በየጊዜው የህክምና ምርመራ በማድረግ ህመም ሳይፈጠር ለመከላከልና ከተፈጠረም በወቅቱ የማከም ዓላማን ይዞ እየሠራ ነው ብለዋል።
ዓላማውን ለማሳካትም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሠራተኞች የኮሌስትሮል፣ የስኳር፣ የደም ግፊት ጨምሮ ለሴት ሠራተኞች የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ እንዲሁም የሀኪም ምክር አገልግሎት ለሁሉም ሠራተኞች በነፃ እየሰጠ መሆኑን በማሳያነት አንስተዋል።
ከተሰጠው የነፃ ምርመራ ባለፈ ተጨማሪ ህክምና ለሚያስፈልገው ማንኛውም የህክምና ምርመራዎች በቅናሽ የሚሰጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ክፍያውንም በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የሚከፍሉበትን የክፍያ አማራጭ የሚሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል።
የተሰጠው የጤና ምርመራም የተቋሙ ሠራተኞች ካለው የሥራ ባህሪ አንጻር እራሳቸውን እንዲያውቁ ለማድረግና ጤናቸው ላይ ትኩረት እንዲሰጡ በማድረግ በኩል ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
የረዳት ሄልዝ ኬር ከሚሰጠው የህክምና አገልግሎት እና ግንዛቤ ከመፍጠር በተጨማሪ በጥቅምት ወር የሚከበረው የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ምክንያት በማድረግ ለጡት ካንሰር ምርመራ የሃምሳ በመቶ ቅናሽ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በበሽታዎች ከመያዝ በፊት ሆነ በሽታው በጊዜ ሳይደረስበት ስር ከመስደዱ በፊት ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ ቅድመ ምርመራ ማድረግና በየጊዜው ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ወይዘሮ ምስጋና አሳስበዋል።
የኢፕድ የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ክፍል ኃላፊ ወይዘሮ ብርሃኔ ሰለሞን በበኩላቸው፤ የተቋሙ ሠራተኞች ብዙውን ጊዜያቸውን በሥራ ላይ የሚያውሉ መሆኑን አንስተዋል። ለሠራተኛው የጤና ምርመራን ተቋሙ ድረስ የሚያገኝበት ሁኔታ በየዓመቱ በተለያየ መንገድ በማመቻቸት የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከረዳት ሄልዝ ኬር ለተቋሙ ሠራተኞች የተደረገው የሙሉ ነፃ የህክምና ምርመራ አገልግሎት ጊዜን እና ጉልበትን በመቆጠብ እራሱን እንዲያውቅ ብሎም ለተቋሙ ጤነኛ ሠራተኞች እንዲኖሩት ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም እንዲህ ዓይነቱ የጤና ምርመራ አገልግሎት የሚገኝበት ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚ ቀጥል አስታውቀዋል።
ምንም ዓይነት የጤና እክል ከማጋጠሙ አስቀድሞ ወደ ጤና ተቋማት የመሄድ ልምድ እንዳለው የገለጸው የኢፕድ ጋዜጠኛ ሞገስ ተስፋ፤ ከመታመም በፊት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና ቅድመ ምርመራ ማድረግ ይገባል ብሏል።
በተቋሙ የተሰጠው ነፃ የጤና ምርመራ ሠራተኛው ያለበትን የጤና ሁኔታ እንዲገነዘብ እንደሚያስችል ገልጿል። ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ የሚያስፈልገውም ለጤናው ትኩረት እንዲሰጥ የሚያስችል እንዲሁም በግል ህክምና ተቋማት የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ የሚያስቀርና ጊዜን የሚቆጥብ መሆኑን ተናግሯል።
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም