በዓላት የሚገምዷቸው መስተጋብሮች

ዜና ሐተታ

በዓላት የሰው ልጆችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ከማጠናከር አኳያ ያላቸው ፋይዳ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ከሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እና ማህበራዊ መስተጋብር ጎን ለጎንም የዕውቀት መጋሪያ እና የሰብዓዊ ተደጋግፎት ምንጭ ናቸው፡፡ በተለይ በበዓላት ዋዜማ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት እና የዕድሜ ልዩነት ሳይኖር የሚደረግ የበዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ጽዳት ቆሻሻን ብቻ ሳይሆን እኩይ አስተሳሰብንም እያፀዱ ስለመሆናቸው ለመገመት አያዳ ግትም፡፡

በዓላት የሚከበሩባቸውን ቦታዎች በጋራ ማጽዳትና ማስዋብ ከምን ጊዜውም በላይ እያደገ የመጣ መልካም ልማድ ሆኖ ቀጥሏል። የበዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ጽዳት ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከሃይማኖት መሪ እስከ ተከታዩ፣ ከሹማምንት እስከ ሠራተኛው እየተተገበረ የሚገኝ የበዓላት ዋዜማ ትዕይንት ሆኗል።

ታዲያ ይህንንም ምክንያት በማድረግ በመጪው መስከረም 25 ቀን 2017 ዓ.ም በመዲናዋ ለሚከበረው የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ማክበሪያ ቦታ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በተገኙበት የጽዳት መርሃ-ግብር ተከናውኗል። በዚሁ ጊዜም ታዲያ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ እንዲሁም እኩልነትን የሻቱ እጆች የኢሬቻን ማክበሪያ ቦታ ለማጽዳት ማልደው ተነስተዋል። ያለ ልዩነትም ለበዓሉ ድምቀት ጎንበስ ቀና ብለዋል።

በወቅቱ ኢፕድ ያነጋገራቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች ኢሬቻ የአብሮነትና የአንድነት ምልክት ነው ይላሉ። ወጣት ለማ ሚካኤል ይባላል። የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ነዋሪ ሲሆን፤ ከወረዳ ሰባት እስከ ወረዳ 11 የፎሌና ጎቤ ወጣቶች አስተባባሪ ነው። ኢሬቻ የፍቅር የአንድነትና የሰላም ምሶሶ ነው ሲልም ያስረዳል።

ለበዓሉ ከሶስት ወር በፊት ጀምሮ ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል የሚለው ወጣት ለማ፤ በዓሉ ባህላዊ ዕሴቱን በጠበቀና ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉን ይጠቁማል። ከሰላምና ጸጥታ፣ ባህልን ከማስተዋወቅ እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ከማጠናከር ረገድ ሥራዎች መሠራታቸውንም ነው የሚናገረው።

የአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት አምባሳደር አርቲስት ሙሉነህ ዘለቀ በበኩላቸው፤ በከተማው የኢሬቻ መከበርን ምክንያት በማድረግ በዋዜማው በጋራ የጽዳት ዘመቻ መደረጉ ማህበራዊ መስተጋብር ከማሳደጉም በላይ የኢሬቻ ምንነትና ያለው ፋይዳ ሕዝቡ እንዲገነዘብ የሚያደርግ ስለመሆኑንም ያብራራሉ።

በኢትዮጵያ በርካታ ያልታወቁ ቱባ ባህሎች አሉ የሚሉት አርቲስት ሙሉነህ፤ የኢሬቻ በዓል አንድነትንና ሰላምን ከመስበክ ጎን ለጎን ለከተማው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው ባይ ናቸው።

አካባቢ ማጽዳት ብቻ ሳይሆን እኩይ አመለካከትና አስተሳሰብም ማጽዳት እንደሚያ ስፈልግም ያክላሉ።

ኢሬቻ ማህበራዊ መስተጋብሮች ከማጠናከር፣ ቱሪዝምን ከማነቃቃት፣ ኢኮኖሚውን ከመደገፍ እንዲሁም የክልሉና የሀገሪቱ ገጽታ ከመገንባት አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው የሚሉት ደግሞ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ደራራ ከተማ ናቸው።

እንደ አቶ ደራራ ገለጻ፤ ከአስር ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ወደ ማክበሪያው ቦታ ይመጣሉ። ኢሬቻ ለኦሮሞ ሕዝብ የማንነት መገለጫ እንዲሁም ከክረምቱ ጨለማ ወደ ብርሃን ላሸጋገረ ፈጣሪ የሚመሰገንበት ነው።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው፤ የሰላም ምልክት ከሆነው የኢሬቻ በዓል ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ትሩፋት መውሰድ ያስፈልጋል።

ኢሬቻ በዓል ስናከበር ለሰላም ያለንን ጽናት የምናሳይበትና አብሮነት የሚጎለብትበት ነው የሚሉት ኢንጂነር ወንድሙ፤ በዓሉ በሚከበርበት ጊዜ ለሀገሪቱ ሰላምና የሕዝቦች አንድነት በሚጠናክርበት መልኩ ሊሆን ይገባል ባይ ናቸው።

ኢንጂነር ወንድሙ ሁሉም ሕዝቦች ባህላቸውንና ማንነታቸውን የሚገልጹበት ሂደት ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸው፤ በዓሉ ሁሉም በጋራ ቆሞ የሀገሪቱን ሰላም የሚያስጠብቅበት እንዲሆን መሥራት እንዳለበት ይናገራሉ።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You