ዜና ሐተታ
ማመስገን በሳይንስም ሆነ በሃይማኖቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ይነገራል፡፡ የምስጋና ጥበብ በስጋዊ እና በመንፈሳዊ ህይወት ቀዳሚው ዋጋ የሚያስገኝ መሆኑ ደግሞ ዕሙን ነው፡፡ ምስጋና ለተለያዩ አካላት ሊቀርብ ይችላል፡፡ ለፈጣሪ፣ ለሰዎች፣ ለተቋማት ወዘተ፡፡ በተለይ ለፈጣሪ የሚቀርብ ምስጋና ቀዳሚው ዋጋ የሚሰጠው ጥበብ መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም፡፡
ከምስጋና በዓላት መካከል ደግሞ በኦሮሞ ሕዝብ የሚታወቀው እና በድምቀት የሚከበረው የኢሬቻ በዓል አንዱ ነው፡፡ ስለበዓሉ አከባበር ከብሾፍቱ ኡለማ ሀደሲንቄ ዘውዲቲ ጌታቸው እንደሚናገሩት፤ በዓሉ በዋናነት ፈጣሪን ለማመስገን ዓላማ አድርጎ የሚከበር ነው፡፡
በዓሉ የሚከበርበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የክረ ምት ዶፍ እና ዝናብ እንዲሁም የወንዝ ሙላት በሰላም እንድናልፍ የረዳንን እና ምድሪቱን በአበባ እና በሳር ልምላሜ ያለበሰን ፈጣሪ ለማመስገን ወደ ውሃማ ቦታ በህብረት በመሰብሰብ በልዩ ሁኔታ የሚመሰገንበት ቀን መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በዓሉ ሲከበር የራሱ ሥርዓት እንዳለው የጠቀሱት ሀደሲንቄ ዘውዲቲ፤ አባገዳዎች፣ ሀደሲንቄዎች፣ ሀዩዎች፣ ሽማግሌዎች፣ ልጃገረዶች እና ፎሌዎች በየደረጃቸው ሆነው ወደ ወሃማ ቦታ ይሄዳሉ፡፡ በቦታው ላይ እርጥብ ሳር ይዘው የሚመርቁ አባመልካዎች እና አባገዳዎች ውሃውን በምስጋና በመባረክ ሕዝቡን በመርጨት የምስጋና ምርቃት እንደሚያቀርቡ ይገልጻሉ፡፡
ዓመት ተጠብቆ የሚከበረው የምስጋና በዓል በባህላዊ አልባሳት ደምቆ እርጥብ ሳር ተይዞ የሚከበር ሲሆን፤ ሀደሲንቄዎች ማር እና ወተት ይዘው ሀገሩን ወተት አድርግልን፣ ትልቁንም ትንሹንም አንድ አድርገህ አስማማልን እያሉ መልካም ምኞታቸውን በመመኘት ‹‹መሬ ሆ..›› እያሉ እንደሚያዜሙ ይጠቅሳሉ፡፡
በዓሉ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚፈጥረው የአንድነት እና የደስታ ስሜት ከፍተኛ ነው የሚሉት ሀደሲንቄ ዘውዲቱ፤ በተለይ በተለያየ ቦታ ተነፋፍቀው የቆዩት ዘመድ ጓደኞች ከውጭ ሀገር ድረስ ተሰባስበው ሲያመሰግኑ እና ሲመራረቁ በዓሉ ተወዳጅ እና ተናፋቂ እንዲሆን እንደሚያደርገው ይጠቁማሉ፡፡
በዚህ የምስጋና በዓል ላይ ማንኛውም ሰው ገብቶ መሳተፍ እንደሚችል በመጥቀስ፤ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከሩቅም ከቅርብም የሚሰባሰበው ሕዝብ አብሮ ሲበላ እና ሲጫወት እንዲሁም የተጣሉ የሚታረቁበት የገዳ ሥርዓት ትውፊት በመሆኑ ከማመስገን የሚገኘው ደስታ እራሱን የቻለ በዓል መሆኑን ያብራራሉ፡፡
የመጫ አባገዳ እና የኦሮሞ አባገዳዎች ሰብሳቢ አባገዳ ወርቅነህ ደሬሳ በበኩላቸው፤ የኢሬቻ በዓል በኦሮሞ ማህበረሰብ ከሚከበሩ በዓላት ዋነኛ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ምክንያቱም በህብረት በመሆን በፍቅር እና በወንድማማችነት የሚከበር፣ የተቀያየመ የሚታረቅበት እንዲሁም ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት ተወዳጅ በዓል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
የምስጋና በዓል ለማክበር ውሃማ ቦታ የተመረጠበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ ‹‹ውሃ ሰው ተወልዶ እስኪ ሞት ድረስ ለመጠጥና ንፅህና ለመጠበቅ እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ እንዲሁም የሰው ልጅ ልቡን እንደ ውሃ ንፁህ በማድረግ ፈጣሪውን ለማመስገን እና ቀጣዩ ጊዜ ጥሩ እንዲሆን መልካም ምኞት ለመመኘት ነው፡፡›› ይላሉ፡፡
የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ማህበረሰብ በህብረት በመሆን ምስጋና የሚያቀርብበት ቀን ሲሆን፤ በዓሉ በተለያዩ የባህል አልባሳት የሚለበሱበት ሲሆን፤ የጥለት ዓይነቶቹ ደግሞ የሸዋ፣ የጅማ፣ የሀረሪ፣ ቦረና፣ ቡጂ እና በሌሎችም ባህል አልባሳቱ ደምቀው በደስታ የሚያከብሩት በዓል መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በዓሉ ሲከበር ከምስጋናው ባለፈ ጎረቤትና ክልሎች በመታደም ወንድማማችነታቸውን የሚያጠናክሩበት እንዲሁም በዕለቱ የሚፈጠረው ድምቀት ለኢኮኖሚው መነቃቃት እንደሚፈጥር እና ማህበራዊ መስተጋብር ለማጠናከር የላቀ ፋይዳ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ በዓሉ ባህላዊ ይዘቱን አስጠብቆ ሌላ ጊዜያዊ መልእክት ሳይንፀባረቅበት እና ዓላማውን ሳይስት ሁሌ መከበር እንዳለበት ይናገራሉ፡፡
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም