ዓባይ ከሀገር ኢኮኖሚ እስከ ቀጣናዊ ትስስር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የህዳሴ ግድብ 3ኛ እና 4ኛ ተርባይኖች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመራቸውን ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው፡፡ ሌሎቹ ዩኒቶች በተቀመጠላቸው ዕቅድ መሠረት ሥራቸው በመከናወን ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የግድቡን የሥራ ሂደትና ወቅታዊ ቁመናውን አስመልክተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ የግድቡ አራት ተርባይኖች ኃይል በማመንጨት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በታኅሳስ ወር ከ70 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ መያዝ እንደሚችል እና የግድቡ የሲቪል ሥራ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ ጠቅሰዋል፡፡

የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራውም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት መልክ ይይዛል፤ አጠቃላይ የግድቡ ሥራ ደግሞ የዛሬ ዓመት ገደማ የመጠናቀቅ ምዕራፍ ላይ እንደሚደርስ አብራርተዋል።ወደ ኋላ ከ205 ኪ.ሜ በላይ ውሃ መያዙንና ወደታች ጥልቀቱ 133 ሜትር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የዓባይ ግድብ ግንባታ የቀጣናውን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር፣ የቀጣናውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን ከማሳደግ አንጻር ምን ፋይዳ አለው? የኢኮኖሚ ምሁራን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ፍሬዘር ጥላሁን እንደሚሉት፤ ዓባይ ግድብ ለኢትዮጵያና ለቀጣናው ሀገራት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ከባቢያዊ ጠቀሜታዎች አሉት። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰረቱ ግብርና መሆኑ እና በሀገሪቱ ውስን ኢንዱስትሪዎች መኖራቸው የሚታወቅ ነው ያሉት መምህሩ፤ የዓባይ ግድብ መገንባቱ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የኃይል አቅርቦት በማሻሻል በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

በዚህም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት እውን ለማድረግ ጉልህ ሚና እንዳለው ጨምረው ያስረዳሉ።

በዓባይ ግድብ ኤሌክትሪክ ከማመንጨት ባለፈ ለተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻነት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለመስኖ ሥራ፣ ለዓሳ እርባታ እና በርካታ ኢኮኖሚያዊ እድሎችን ለኢትዮጵያ ማስገኘት ችሏል ይላሉ፡፡

ዓባይ ውሃን ተጠቅመን ምን መሥራት እንዳለብን ዝርዝር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን አስተምሮናል የሚሉት መምህሩ፤ በዚህም በዝናብ ጥገኛ የሆነው የግብርና ሥራ በመስኖ ማልማት እንደሚቻል፣ የቱሪ ስት መዳረሻዎችን ማልማት እንደሚቻል፣ የሀገሪቱን ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና ተሰሚነት ማሳደግ እንደሚቻል አስተምሮናል ሲሉ ያብራራሉ፡፡

አቶ ፍሬዘር እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ የምታመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለአንዳንድ ጎረቤት ሀገራት መሸጥ ጀምራለች። በቀጣይ ደግሞ ከታንዛኒያ ጋር ትስስር ለመፍጠር በተቋማት ደረጃ የሚከናወኑ ቴክኒካል ሥራዎች ተጠናቀዋል።ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊ ላንድና ሱማሊያ ጋርም ትስስር ለመፍጠር መታቀዱንና ሀገራቱም የኃይል ግዢ ፍላጎት ማሳየታቸው የሚታወቅ ነው ይላሉ፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ከምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ከሆኑ ሀገራት ጋር የሚኖራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር በጥቅም ላይ የተመሰረተ እና የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ሠጥቶ መቀበል የዓለም የኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መርህ ነው ያሉት መምህሩ፤ ጎረቤት ሀገራት በዓባይ ግድብ ተጠቃሚ መሆናቸው የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጥርባቸው፣ የተሻለ አገልግሎት ለማግኘት በጋራ እንዲያለሙ እና ለፕሮጀክቱ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርጉ ያስችላል ሲሉ ያብራራሉ።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረቧ የተጽዕኖ ፈጣሪነትና ተሰሚነት አቅሟን የሚያሳድግ ነው።

መንግሥት የግድቡን አዋጭነት ከኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊ፣ ከፖለቲካዊና አካባቢያዊ አንጻር በየጊዜው የማጥናት እንዲሁም በዓባይ ግድብ የሚመነጨው ኃይል በሙሉ አቅሙ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን መከታተል እንዳለበት ይናገራሉ፡፡

የዓባይ ግድብ ግንባታን በቀና አይን ለማይመለከቱ አካላት ግድቡ የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ያደረገ መሆኑን ለማስረዳት የሚደረገው ዲፕሎማሲያዊ ሥራ የሚበረታታ ነው።በግድቡ ዙሪያ የሚሰራው የዲፕሎማሲያዊ ተግባር በቀጣይም ያለመሰልቸት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ያመላክታሉ፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያ እና የፖሊሲ አማካሪው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የዓባይ ግድብ መገንባት ለሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ለጎረቤት ሀገራት የሚሸጠውን ኃይል ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ሽያጭ ከፍተኛ ሥራ እየሠራች ነው የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ በዚህም ለኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊ ላንድ፣ ሶማሊያ እና ለሌሎች ጎረቤት ሀገራት ለማዳረስ ጥረት እያደረገች መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንዳስረዱት፤ የዓባይ ግድብ ተገንብቶ ውሃ መጠራቀሙ ግብጽና ሱዳን ተጠቃሚ ያደርጋል።በግብጽ የሚገኘው የአስዋን ግድብ በትነት የሚባክነው ውሃ ለመስኖ ልማት ከሚጠቀሙበት በላይ ነው።በግብጽ የዝናብ እጥረት እንኳን ቢያጋጥም ለሁለት ዓመታት ያህል የሚያገለግል ውሃ የዓባይ ግድብ ያጠራቅምላቸዋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ ውሃውን ቆልፋ አትይዝም እንደዚህ ማድረግም አትችልም ያሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ግድቡ አንዴ ከሞላ ውሃውን የመስደድ እና ተርባይኖችን እያንቀሳቀሰ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ የማድረግ ሥራ ነው እየተሠራ ያለው ይላሉ፡፡

ዓባይ ለቀጣናው ሀገራት የኢኮኖሚያዊ ትስስር መጠናከር ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን በመግለጽ፤ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ውሃና ኤሌክትሪክ መሸጧ በሀገሪቱ የሌሉ ጸጋዎችን ከሌሎች ሀገራት እንድትጠቀም እንደሚያስችል ያስረዳሉ፡፡

ለቀጣናዊ ትስስር መሠረታዊ ነገሩ የኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና ማሰራጫ ነው።ኤሌክትሪክ ከሌለ ኢንዱስትሪዎች አይሰሩም።በመሆኑም በኢትዮጵያ የሚገኙ የታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ ኮይሻ፣ ግቤ እና ሌሎች ግድቦች ማዕከል ሆነው እያገለገሉ መሆናቸውን ያመላክታሉ፡፡

ለኢትዮጵያም ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማልማት፣ ለዓሳ ልማት፣ በአካባቢው የሆልቲካልቸር ምርቶችን ለማምረት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለውሃ ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ለመስኖ ልማት እና ሌሎች በርካታ ጠቀሜታዎችን እያስገኘ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

መንግሥት የግሉን ዘርፍ በቱሪዝም ልማቱ እንዲሳተፍ ማበረታታት እና በአካባቢው ያለውን ሰላም ለማስፈን ሊሠራ እንደሚገባ ያሳስባሉ።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You