የመንግሥት ተቋማት የኑሮ ውድነቱን ለምን ያባብሳሉ?

ኢትዮጵያም ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት በሚታረስ የእርሻ መሬትና በግብርና ምርት ቀዳሚ ሀገር ናት። ሆኖም በተቃራኒው የግብርና ምርቶችና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች እጥረት ካለባቸውና ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከሚታይባቸው ሀገራትም አንዷ ናት።

በአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣምና በተለያዩ ብልሹ አሰራሮች ምክንያት በየቀኑ እየጨመረ የሚሄደውም የሸቀጦች ዋጋ መናር በዜጋው ላይ ከፍተኛ የኑሮ ውድነትን በመፍጠር ህዝቡን ለምሬት እየዳረገው ነው። እንደሽምጥ ፈረስ የሚጋልበው የኑሮ ውድነት በተለይም ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል ከሚሸከመው በላይ ሆኖበታል።

በተለይም ኅብረተሰቡ በዕለት ተዕለት በሚጠቀምባቸው መሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዜጎችን ህይወት እጅግ እየተፈታተነው ይገኛል። በእህል፣ በጥራጥሬ፤ በአትክልት ምርቶች፤ በግንባታ ዕቃዎች እና በመንግሥት አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪው አሳሳቢ ሆኗል። ነገሩን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉት ያለው የመንግሥት ተቋማት መሆናቸው ነው። በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ከተደረገበት ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በርካታ የመንግሥት ተቋማት በየፊናቸው የዋጋ ጭማሪ እየደረጉ ነው።

የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ በተደረገ ማግስት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በአንድ ኪሎ ስኳር ላይ ከ10 ብር ያላነሰ ጭማሪ አድርጓል። የኢምግሬሽንና ስደተኞች አገልግሎት በሁለት ሺ ብር ሲሰጥ የነበረውን የፓስፖርት አገልግሎት እስከ 25ሺ ብር አሳድጓል። ሰሞኑን የትራንስፖርት ባለስልጣን መንጃ ፈቃድ ለማውጣትና እና ለዕድሳት እስከ 100 ፐርሰንት ጭማሪ እስከማድረግ ደርሷል። በቦሎ እድሳት ላይም የተጨመረው ገንዘብ ብዙዎች እጃቸውን እራሳቸው ላይ እንዲጭኙ አድርጓቸዋል።

ይህ አልበቃ ብሎ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በአገልግሎቴ ላይ ቫት ማሰብ እጀምራለሁ ማለቱ ህዝቡ ያስቀመጠውን ገንዘብ እንኳን በተመጣጣኝ ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንደማይችል ያመላከተ ነው። ንግድ ባንክ በአገልግሎትና በአዳዲስ ፈጠራዎች ከሌሎች ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ መሆን ሲገባው በረባ ባልረባው የአገልግሎት ክፍያ መጨመሩ ደንበኞችን የሚያርቅ ነው።

ከመንግሥት አገልግሎት መናር ጎን ለጎን በየቀኑና በየሰዓቱ የሚጨምረው የሸቀጦች ዋጋ በተለይም ዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ኑሮ እንደምርጊት እንዲከብደው ምክንያት ሆኗል። መሽቶ በነጋ ቁጥር ‹‹ከገበያ ጠፍተዋል››፤‹‹ዋጋ ጨምሯል›› የሚሉት አገላለጾች ኅብረተሰቡን በሰቆቃ ውስጥ እንዲኖር እያደረጉት ነው።

በመንግሥት ዘንድ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ ፈተና እየገጠመው ያለው ከዋጋ ግሽበት በተያያዘ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቢሰማም ችግሩን ለመቅረፍ የተኬደበት ርቀት ውጤታማ አለመሆኑ በየሰዓቱ የሚጨምረው የሸቀጦች ዋጋ መናር በቂ ማሳያ ነው። በዚህ ላይ ደግሞ የመንግሥት ተቋማት ችግሩ አባባሽ ሆነው መገኘታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

ምግብ ነክ የሆኑና መሠረታዊነታቸው የታመነባቸው የፍጆታ ዕቃዎች በፍራንኮ ቫሉታ አሠራር ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ እና የመድኃኒት፣ ነዳጅ፣ ማዳበርያ፣ ዘይት እና ሌሎችም መሠረታዊ ሸቀጦች ግዢ አቅርቦት አቅርቦት እንዲቀላጠፍ የማስተካከያ እርምጃ ይወሰዳል ቢባልም የኑሮ ውድነቱን ከመገስገስ ያቆመው አንዳች ምድራዊ ኃይል አልተገኘም።

ከዚሁ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ባለፉት አራት አመታት በተሰሩ የግብርናውን የማዘመን ስራዎች በሀገሪቱ ምርታማነት እንደጨመረ ቢታመንም በተለያዩ ህገወጥ አሰራሮችና የቁጥጥር መላላት ምክንያት ምርቱ ሸማቹ ህብረተሰብ ጋር በቀላሉ ለመድረስ ካለመቻሉም ባሻገር የዋጋ ንረትም እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።

በሂደት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ መሻሻል አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት የታመነበት የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርምን አላግባብ ትርጉም በመስጠት እላፊ ተጠቃሚ ለመሆን የሚሯሯጡ ነጋዴዎችና ተቋማት ታይተዋል። ከማሻሻያው በኋላ በምርቶችና ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል። በመሳለሚያና በመርካቶ አካባቢ ያሉ ነጋዴዎች እንደሚናገሩትም በነሃሴና መስከረም ወራት በጤፍ፤ በዱቄት፤ በፓስታና መኮረኒ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ አስደንጋጭ ነው። ጤፍ በአንድ ወር ብቻ እስከ ሁለት ሺህ ብር ጭማሪ አሳይቷል። ፓስታና መኮረኒ ላይ በአንድ ወር ብቻ እስከ 30 ብር ጭማሪ ታይቷል።

ሆኖም በአሳሳቢ ሁኔታ የኅብረተሰቡን ጫንቃ እያጎበጠ ያለውን የኑሮ ውድነት አሳስቦት ተገቢ የሆነ መፍትሄ ለማፈላለግ የሚተጋ ተቋም ማግኘት በጨለማ ውስጥ ጥቁር ድመትን የመፈለግ ያህል ከባድ እየሆነ መጥቷል። የመንግሥት ኃላፊዎች እና የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶችም የችግሩን አሳሳቢነት ከመቀበል ይልቅ አንዱ ወደ አንዱ እየወረወሩ ችግሩ መፍትሄ አልባ ሆኗል።

የኑሮ ውድነቱ አንዱ የታዳጊ ሀገራት ፈተና ነው። ኢትዮጵያም የዚሁ ችግር ሰለባ ነች። ከወር እስከ ወር ከዓመት እስከ ዓመት በየጊዜው ማሻቀቡና ተባብሶ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየጊዜው የሚያወጣቸው መረጃዎችና በማኅበረሰቡ ላይ የሚታየው የኑሮ ጫና ያመላክታል። በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ወድነት አሁን ላይ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል በእጅጉ እየፈተነ ይገኛል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የኑሮ ውድነት ተከሠተ የሚባለው የማኅበረሰቡ የመግዛት አቅም ወይም ገቢ ማነስ ከዋጋ ግሽበት ጋር ተደምሮ የሚፈጥረው የመግዛት አቅም ሲዳከም ነው። በኢትዮጵያ ከመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች እስከ ሌሎች ቁሳቁሶች ድረስ የዋጋ ግሽበቱ በየጊዜው እያሻቀበ ቢሆንም፣ የአብዛኛው የማኅበረሰቡ ክፍል ገቢ ወይም የመግዛት አቅም ግን ከዋጋ ግሽበቱ እኩል ማደግ አለመቻሉን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ለዋጋ ግሽበት ዋነኛ ምክንያቶች ከሚባሉት መካከል የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የገበያ ምኅዳር ብልሽት ወይም ሕገ ወጥ ደላሎች በገበያ ውስጥ የሚፈጥሩት ጣልቃ ገብነት እና የጥሬ ገንዘብ ሥርጭት መብዛት በቀዳሚነት የሚነሱ መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ እየታየ ላለው የዋጋ ግሽበት ዋና ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው የምግብ ነክ ሸቀጦች፣ በተለይ የእህል ዋጋ መናር ነው። ለዚህ ደግሞ የምርት እጥረት እና ተመርተውም ምርት በጸጥታ እና በግብይት ሰንሰለት መርዘም ወደ ህብረተሰቡ በበቂ ሁኔታ አለመድረስ ተጠቃሾች ናቸው።

በእርግጥ የኢትዮጵያ አመታዊ የምርት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ ነው። ከአምስት አመታት በፊት ከ300 ሚሊዮን ብዙም ከፍ የማይለው አመታዊ ምርት ዘንድሮ ወደ 800 ሚሊዮን አድጓል። ሆኖም አሁንም ቢሆን እያደገ ካለው የህዝብ ቁጥር አንጻር ገና ብዙ መስራት ይጠይቃል።

ለአገሪቱ የዋጋ ግሽበት የምርት እጥረት ብቻ የሚፈጥረው አይደለም:: የዘመናዊ ግብይት ዕጦት እና የደላሎችና ህገወጥ ነጋዴዎች መበራከት ለችግሩ መባባስ መንስዔ ናቸው። የኢትዮጵያ ገበያ 200 እና 300 በመቶ ትርፍ የሚያዝበት ነው። ይህ በዓለም ላይ የለም። ይኼ አካሄድም በፖሊሲ ጭምር ታግዞ ሊስተካከል ይገባል።

የአገሪቷ ገበያ ሥርዓት ዘመናዊ ባለመሆኑ የፖሊሲ ለውጥ አስፈልጎታል:: ይህንን መነሻ በማድረግ ከሁለት ወራት በፊት መንግሥት ወደ ትግበራ ያስገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ስርዓትም ለዚህ ሁነኛ መፍትሄ ይዞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል። በሀገራችን ውስብስብና ኋላ ቀር የሆነ፣ የገበያ ስርጭት ነው ያለው። አንዳንድ ቦታ እንዲያውም በሞኖፖል የተያዘ ይመስላል። በተለይ ሸቀጣ ሸቀጥ ላይ ገበያው በሞኖፖል ተይዟል። ስለዚህ ይህንን በመፍታት አዳዲስ ኩባንያዎችን በማስገባት የውድድር ሜዳውን በማስፋት ረገድ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል። ዘርፉን ለሚቀላቀሉ የሀገር ውስጥና የውጭ አዳዲስ ኩባንያዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ከተደረገ በአንድ ቀን አዳር ዋጋ የተጋነነ ዋጋ በመጨመር ራሳቸውን ሚሊየነር ለማድረግ የሚጥሩት ስግብግብ ነጋዴዎች ከእንግዲህ ወዲያ ቦታ አይኖራቸውም።

ይህ አካሄድም በውድድር ዋጋ የሚቀንስበትን መንገድ በመፍጠር የኑሮ ውድነቱ እንዲረጋጋ ያደርጋል። ቀልጣፋ የሆነ አቅርቦትና ውድድር ከተፈጠረ የዋጋ ግሽበቱን መቀነስ ይቻላል። አዲሱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም ሁሉም ነገር በገበያ እንዲወሰን በር ስለከፈተ በጥቂት ነጋዴዎች ተይዘው የቆዩ ዘርፎችም በርካታ ተዋናዮች እንዲኖሩ በማድረግ ሸማቹ በርካታ አማራጮች እንዲኖሩት ያስችላል።

ግሽበቱን ለመቀነስ በቂ ምርት ሊኖር ይገባል ከተባለ ደግሞ ሸማቾች የሚጠቀሙባቸው ከአገር ውስጥ ሆነ ከውጭ የሚገኝ ምርት በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ከፍ ማድረግ። ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ግሽበቱ የሚታይ ከሆነ በቂ ምርት እንዳይኖር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ሊሆን ይችላልና በቂ የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ እያስተካከሉ መሄድ። አሁን ያለው አሠራር እየፈጠረ ያለው የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የሚቀረፀው ፖሊሲ የውጭ ኩባንያዎችንም በማስገባት እንዲረጋጋ ማድረግንም ይጠይቃል። የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ ስርዓቱም ለዚህ ምቹ ምህዳር ይፈጥራል።

ለዋጋ ግሽበቱ መባባስ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም እንደሀገር ፈተና እየሆኑ ካሉ ችግሮች አንዱ ስግብግብ ነጋዴዎች በአቋራጭ ለማትረፍ የሚያደርጉት ሩጫ ነው። ሰሞኑን መንግስት ይፋ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ መሻሻያን ተክትሎ ከዶላር መጨመር ጋር ተያይዞ በመርካቶና በሌሎች ዋናዋና የገበያ ስፍራዎች የሸቀጦችን ዋጋ ለማናርና በአቋራጭ ለመበልጸግ እየተደረጉ ያሉ ሩጫዎች ማሳያዎች ናቸው።

ይህንኑ ተከትሎ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ፤ ምርትን በደበቁና ባከማቹ በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ስርዓቱን ተክትሎ የተደረገውን የዶላር ዋጋ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ በአቋራጭ ለመክበር ጥረት ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታውቋል። ሆኖም ርምጃው ቀጣይ ሆኖ አላየነውም።

የንግድ ቢሮው እየወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ቢሆንም ድርጊቱ ግን አስተዛዛቢ ነው። መንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ማድረጉን ባስታወቀበት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሸቀጦችን በመደበቅ፤ በማከማቸትና ከልካቸው በላይ ዋጋ በመቆለል የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር እና ኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ለማድረግ ሲሞክሩ ታይተዋል። እነዚህን ስግብግብ ነጋዴዎች ፈር ለማስያዝ የተወሰደው ርምጃ ጥሩ የሚባል ቢሆንም በተቃራኒው የመንግሥት ተቋማት ዋጋ እየጨመሩ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ መደረጉ ከስግብግብ ነጋዴዎች ያመለጠውን ህዝብ ተመልሶ በሌላ ማነቆ ውስጥ እንዲገባ ያደረገ ነው።

የመንግሥት ተቋማት ኑሮ ማረጋጋት እና ኅብረተሰቡንም ከምዝበራ መታደግ ሲገባቸው ራሳቸው እየተሽቀዳደሙ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸው ተቋማቱ የተቋቋሙበትን አላማ እንድንመረምር የሚያደርገን ነው። አብዛኞቹ ህዝብን ለማገልገል የተቋቋሙ ቢሆኑም በሂደት የነጋዴ ባህሪ የተላበሱ እና ትኩረታቸው ሁሉ ከኅብረተሰብ እርካታ ይልቅ ትርፍን የሚያሳድዱ ሆነዋል።

በአጠቃላይ በየቀኑ እንደ ሽምጥ ፈረስ የሚወረወረው የኑሮ ውድነት የአብዛኛውን ድሃ ኅብረተሰብ ወገብ እያጎበጠና ከባድም የኑሮ ፈተና እየሆነ መምጣቱን አምኖ ለችግሩ ትኩረት መስጠት የመፍትሄው አንድ እርምጃ ሊሆን ይገባል። በተጨባጭም ለኑሮ ውድነቱ ተገቢውን ትኩረት መስጠቱን የሚያረጋግጡ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅበታል። ቀጥሎም መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የአቀርቦት ሥርዓቱን ማስተካከልና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ችግሩን ከስሩ ለመንቀል ያስችላል። ከዚሁ ጎን ለጎን ግን የመንግሥት ተቋማት ቢያንስ በዚህ ወቅት የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ ሊቆጠቡ ይገባል።

አሊሴሮ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You