ለበዓሉ ሠላማዊነት ሁላችንም የሚጠበቅብንን ልንወጣ ይገባል

አዲስ አበባ በዚህ ሰሞኑን ውበቷ ጨምሯል። ከከተማዋ የኮሪደር ልማት በተጨማሪ የአዲስ ዓመት እና የመስቀል በዓልን መድረስ የሚያበስሩ መልካም ምኞት መገለጫዎች አሁንም ድረስ ውበታቸው እንደተጠበቀ ነው። ኢሬቻ ደግሞ የበለጠ ለከተማዋ ውበት እያላበሰ፤ አዲስ አበባ ወዘናዋ የደመቀ አዲስ የመስከረም ሙሽራ እያደረጋት ነው።

የከተማዋ በርካታ ህንፃዎች ሁሉ በእርጥብ ሣር ጎዝጓዝ እንደወዙ በአደይ አበባ እንዳሸበረቁም ይገናሉ። የከተማዋ ዓደባባዮች ደግሞ የተለያዩ ድምቀት ያላቸው በንፋስ የተሞሉ ፊኛዎች እና ሰንደቅ ዓላማዎች ሽብርቅ ብለዋል። ባህላዊ ሙዚቃዎች በየሰፈሩ እና በተለያዩ ተቋማት በር ላይ ከፍ ባለ ድምፅ ተለቀዋል።

በከተማዋ የተለያ አካባቢዎችም ወጣቶች እና ልጃገረዶችም የተለያዩ ባህላዊ ውዝዋዜዎችንና ትዕይንቶችን እያሳዩ ነው። ከተማዋ በሠላማዊ ድባብ ሠላማዊ ሰዎች እየተንሸራሸሩባት ነው። አዲስ ዓመት ይዞት ከሚመጣው ተስፋ ጋር ተዳምሮ፤ ከተማዋ በብዙ የተስፋ ጠረን ታውዳለች።

ከተማዋ በየዓመቱ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ለማድመቅ በብዙ ዝግጅት ውስጥ ነች። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንግዶቿን እንኳን ደህና መጣችሁ ብላ በኢሬቻ በዓል አብራ ለመደሰት በሰፊው ደፋ ቀና እያለች ነው። ነዋሪዎቿም እንግዶችን ለመቀበል ፤እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት፤ በቀና መንፈስ የዝግጅቱ አካል ሆነዋል።

የኢሬቻ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ ክረምት ከመግባት በፊት እና ክረምት ከወጣ በኋላ የሚከበር ነው። የመጀመሪያው የኢሬቻ በዓል በተራራማ ሥፍራ ለምስጋና እና ቀጣይ ወራትን ስኬታማ እንዲሆን የሚመኙበት ነው። ሁለተኛው ደግሞ በሃይቅ እና ወንዞች አካባቢ ምስጋና ለማቅረብና ለቀጣይ ስኬትን ለመሻት የጎርፍ እና የጨለማን ወቅት አሻግሮ ለፀደዩ ብርሃን ላደረሰው ፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ነው።

ተደጋግሞ እንደተነገረው፤ በዓሉ ፍቅር፣ ሠላም፣ እርቅ እና አንድነትን የሚሰብክ፤ የኦሮሞ ማህበረሰብ አንድነቱን፣ ወንድማማችነቱን፣ ፍቅሩን፣ ብሔራዊ ኩራቱን፣ ታሪክና ባህሉን የሚገልፅበትና የሚያድስበት መድረክ ነው። ይህም ቢሆን የበዓል ሰሞን ዜማ ሊሆን አይገባም። ይህ ከሕዝቡ ጋር የኖረ እሴት በመሆኑ የበለጠ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። ይሁንና ይህን እሴት የበለጠ ለማጉላት አጋጣሚዎችን መጠቀም አግባብ ነው።

ኢሬቻ ሲከበር ኦሮሞው ብቻ ሳይሆን ሌሎች በዓሉን ለመታደም የሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚገኙበት ነው። በዚህ ሂደት ደግሞ ብዙ ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚጠናከሩበት ነው። ይህም ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ሂደት ውስጥ የሚኖረው ሥፍራ ከፍ ያለ ነው።

በአሁኑ ወቅት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከሚያንቀሳቅሰው ከፍ ያለ ሀብት አኳያ፤ ሀገራት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በስፋት እየተንቀሳቀሱ ነው፤ ሀገራችንን ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን በፖሊሲ የተደገፊ ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራች ነው። ከዚህ አኳያ ኢሬቻን በአግባቡ በማስተዋወቅ ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበት ዕድል ሰፊ ነው።

ይህን በዓል ምክንያት ባደረገ እጅግ አስገራሚ የአልባሳት ዲዛይኖች፣ ባህላዊ ቁሳቁሶች እና የበዓሉ የድምቀት ምክንያት የሆኑ የዕደ ጥብ ውጤቶችን በሰፊው እየተመለከትን ነው። የቱባው ባህል ባለቤት የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ በበዓሉ ወቅት የሚያሳያቸው የተለያዩ ትዕይነቶችም የዚሁ አካል ናቸው።

በዓሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹ኢሬቺ ኢሬ ኬኛ›› ወይንም በአቻ ትርጉሙ ‹‹ኢሬቻ ኃይላችን ነው›› በሚል የበርካቶች መሰባሰቢያ ሆኗል። የበዓሉ ዋነኛ እሴት እንደተጠበቀ ሆኖ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ፋይዳዎችም አሁን አሁን ተገቢውን ግንዛቤ እያገኙ ነው።

ይህ በመሆኑም ቀደም ሲል ስለበዓሉ ግንዛቤው የሌላቸው አካላት እንኳን ሳይቀሩ ሲታደሙ መመልከት ጀምረናል። ይህም የመጣው ስለ በዓሉ ላለፉት ዓመታት

በተሠሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሆነ ይታመናል።

በዓሉ የህብረተሰቡ የቆዩ ታሪካዊ መስተጋብሮች የበለጠ የሚጎለብትበት፣ እርቅና ሠላም የሚወርድበት፣ ሠላም እና አንድነት በፅኑ ቃላት የሚሰበክበትና የሚተገበርበት ከመሆኑ አንጻር፤ የሚመለከታቸው አካላት፤ በዓሉን ከማክበር ባለፈ ለበዓሉ እሴቶች የማስፋትን ሥራ የእያንዳንዷቀን የቤት ሥራ አድርገው ሊወስዱት ይገባል።

በበዓሉ ሰሞን የሚካሄዱ የባህል ሲንፖዚየሞች እና ባዛሮች በዓሉን ለመታደም የሚመጡ ብዛት ያላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች፤ ቆይታቸውን የበለጠ ትርጉም እና ትውስታ እንዲኖረው እያደረጉ ነው ፤ የባዛሮቹ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው እናዳለ ሆኑ እየፈጠሩት ያለው ማሕበራዊ መስተጋብርም ከፍያለ ነው።

በባህል ዘርፍ ላይ ጥናት የሚያካሂዱ ዓለም አቀፍ ምሁራን ሆኑ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎችም በርካታ ግብዓቶችን እያገኙበት ያለ የባህል ሲመንፖዚየሞችም የሀገሪቱን ህብረ ብሄራዊ ገጽታ ከማስተዋወቅ ባለፈ ለምርምር ተነሳሽነትን የሚፈጥሩ ናቸው።

ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ የባህል አምባ ወይንም በባህል የታደለች ሀገር ብቻ ሳትሆን ያላትን ማቆየት የምትችል ሀገር መሆኗም በተጨባጭ ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ለማስተዋወቅ እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ የሚታይ ነው።

ኢሬቻን የሚመስሉ በዓላት ካላቸው ሰፊ ጠቀሜታ በአኳያ መንግሥት መሰል ሕዝባዊ በዓላት በአግባቡ ተከብረው /ተጠብቀው/ እንዲቆዩ ልዩ ትኩረት ሊያደርግ፤ የበዓሉ ውበት የበለጠ እንዲጎለብት አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበታል ።

በዓሉን ሊያከብሩም ሆነ ሊታደሙ የሚሰባሰቡ አካላትም አንዳቸው ከሌላኛው ያልተናነሰ ሀገራዊ ኃላፊነት አለባቸው። በዓሉ የጋራ ሀብት በመሆንም የበዓሉን አከባበር ሠላማዊ እንዲሆን መላው ሕዝባችን በይመለከተኛል መንፈስ በኃላፊነት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።

ለበዓሉ ስኬታማነት እና ሠላሚዊነትም የፀጥታ አካላትን መተባበር ፤ የበዓሉ ታዳሚዎችም እንቅፋት ሳይነካቸው፤ ንፋስ ሳይገባቸው ወደየመጡበት እንዲመለሱ ሁላችንም ትልቅ ኃላፊነት ፤ ይህንን ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ደግሞ በቂ ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅብናል ።

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን  መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You