አዲስ አበባ፡- በጥቅምት ወር የሚኖረው እርጥበት በደቡባዊው የሀገሪቱ ክፍሎች ማሳን ቀድሞ ለማዘጋጀትና ዘር ለመዝራት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት እ.ኤ.አ ከጥቅምት አንድ እስከ ጥቅምት 31/2024 የሚኖረውን የአየር ሁኔታ ትንበያ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በጥቅምት ወር በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚኖራቸውና በሂደትም ወደ ደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ እርጥበት እንደሚኖር ይጠበቃል ብሏል፡፡
ይህም ሁኔታ ወቅታዊ ዝናብ ማግኘት በሚጀምሩትና ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑት የደቡባዊው የሀገሪቱ ክፍሎች ቀደም ብሎ የማሳ ዝግጅት ለማድረግና ዘር ለመዝራት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በአካባቢው ለሚኖሩት አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለግጦሽ ሣርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥሩ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በመግለጫው አብራርቷል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታም በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ እርጥበቱ ቀጣይነት የሚኖረው በመሆኑ ቀደም ብለው ለተዘሩና አልፎ አልፎ ፍሬ በመሙላት ላይ ለሚገኙ፣ በተለያየ ምክንያት ዘግይተው ለተዘሩና በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ለመኸር ሰብሎችም ሆነ ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት መሟላት ጉልህ ሚና እንዳለው ተጠቁሟል፡፡
የእርጥበት እጥረት ላለባቸው አካባቢዎች የዝናብ ውሃን ለማቀብ እና ለማሰባሰብ ምቹ ሁኔታ ስለሚኖር ይህንኑ አጋጣሚ በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ መግለጫው አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በአብዛኛው የበጋ ወቅት እንደሚስተዋለው የሰሜን አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ ፀሐያማ እና ነፋሻማ የአየር ጠባይ ጎልቶ ከመታየቱ አንጻር የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ መጨመር ያሳያል ተብሏል።
በጸሀይ ሃይል በመታገዝ ከሚጠናከሩ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በመነሳት በጥቂት የምዕራብና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ተመላክቷል፡፡
በጥቅምት ወር ከአብዛኛዎቹ ተፋሰሶች ላይ የእርጥበት ሁኔታው በመጠንም ሆነ በስርጭት እየቀነሰ እንደሚሄድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
አብዛኛው ባሮ አኮቦ፣ የታችኛውና የመካከለኛው ዓባይ፣ ኦሞ ጊቤ፣ ስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ላይ እስከ ከፍተኛ የሚደርስ የእርጥበት መጠን ያገኛሉ፡፡ ይህም የከርሰ ምድር እና የገፀ ምድር የውሃ ሀብትን ከማጎልበት አንጻር የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም የመስኖም ሆነ የሃይል ማመንጫ ግድቦችን የውሃ መጠን ከፍ ስለሚያደርግ በመጪው የበጋ ደረቅ ወራት አስተማማኝ የሃይል አቅርቦት እንዲኖር ከማስቻል አንጻር አወንታዊ ሚና ይኖረዋል፡፡
የታችኛውና የመካከለኛው ዋቢ ሸበሌ እና የገናሌ ዳዋ በአንጻሩ መጠነኛ የሆነ እርጥበት እንደሚያገኙም ተገልጿል፡፡
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም