ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን ለማረጋገጥ የአጋር አካላት ቀጣይነት ያለው ትብብር አስፈላጊ ነው

አዲስ አበባ፦ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን ለማረጋገጥ የአጋር አካላት ቀጣይነት ያለው ትብብር አስፈላጊ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ። በኢትዮጵያ ላለፉት ስድስት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የዩናይትድ ስቴትስ የርዳታ ድርጅት «ዩኤስ ኤይድ» የጤና ፋይናንስ ማሻሻያ ፕሮግራም ማጠቃለያ መርሃ ግብር ትናንት ተካሂዷል።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የጤና ፋይናንስ ሥርዓቷን በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ እመርታ ብታሳይም ለሁሉም ዜጎች ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያ ተግዳሮቶች አሁንም ቀጥለዋል።

በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን ለማረጋገጥ የአጋር አካላት ቀጣይነት ያለው ትብብር አስፈላጊ ነው ያሉት ዶክተር አየለ ፤ ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ግብን ለማሳካት በርካታ ሥራዎችን ይፈልጋል። ሁሉም ዜጎች ፍትሃዊ የሆነ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ የጤና ፋይናንስ ሥርዓት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል። አሁንም በተደራሽነት እና በጥራት ላይ ክፍተቶች መኖራቸውንም አንስተዋል።

እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት መንግሥት በሀገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብ፣ የውጭ ሀብት አያያዝ፣ ስትራቴጂካዊ ግዥ እና አጠቃላይ የኢንሹራንስ ሥርዓት መዘርጋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ያሉት ዶክተር አየለ ተሾመ፤ ሆኖም ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ግብን ለማሳካት ከለጋሾች እና ፈጻሚ አጋሮች ጋር ቀጣይነት ያለው ትብብር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ጤናማ እና ፍትሃዊ የጤና ፋይናንስ ሥርዓት ጉዞዋን ስታጠናክር ከፊታችን ያሉ ፈተናዎች አዳዲስ መፍትሄዎችን ይሻሉ ሲሉም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ የርዳታ ድርጅት «ዩኤስ ኤይድ» ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤሌኖር ታንፒንኮ በበኩላቸው፤ የ«ዩኤስ ኤይድ» የጤና ፋይናንስ ማሻሻያ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን አሳድጓል ብለዋል።

የ«ዩኤስ ኤይድ» የጤና ፋይናንስ ማሻሻያ ፕሮግራም በኢትዮጵያ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ገልጸው፤ ፕሮግራሙ የጤና አጠባበቅ ተደራሽነትን በከፍተኛ ደረጃ በማስፋት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የፋይናንስ ጫናዎችን መቀነስ ችሏል ነው ያሉት።

በአሁኑ ጊዜ ከ52 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚ መሆናቸውን ያነሱት ኤሌኖር ታንፒኝኮ፤ በፕሮግራሙ የሕዝብ ጤና አስተዳደርን ከማጠናከር ባለፈ ለጤና ተቋማት ተጨማሪ የቁሳቁስ እና የተለያዩ ድጋፎች መደረጉን ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ የጤና ፋይናንስ ሥርዓት ላይ ጉልህ መሻሻል ቢያደርግም በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን እና በሌሎች ፕሮግራሞችን የሚታዩ ተግዳሮቶች መኖራቸውን አንስተው፤ «ዩኤስ ኤይድ» እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እና የጤና አጠባበቅ ፋይናንስን የበለጠ ለማሻሻል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያለውን ሥራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You