አዲስ አበባ፡– በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው የሕግ የማስከበር ሂደት የሚቆመው የክልሉ ሰላም ሙሉ በሙሉ ሲረጋገጥ መሆኑን የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ገለጹ፡፡
የሕግ ማስከበር ርምጃውን በሚመለከት የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እና የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በመግለጫው እንዳሉት፤ በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት ለማስተካከል ሕግ የማስከበር ርምጃ እየተወሰደ ነው። የኦፕሬሽኑ ዓላማ ሁከትን እና ብጥብጥን አስወግዶ ለክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ ሰላምን ማስፈን ነው፡፡ ሕግ የማስከበር ሂደቱ የሚቆመው የክልሉ ሰላም ሙሉ በሙሉ ሲረጋገጥ ነው።
በክልሉ ያለው የጽንፈኛ ቡድን የመከላከያን የቆየ ቁስል እየነካ እና ትዕግስቱን እየተፈታተነ የመጣ እንደነበር የጠቀሱት፤ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ለሕዝብ ሰላም ሲባል ብዙውን ነገር በዝምታ አልፏል። ለመከላከያ ሠራዊት የሚሰጠው ዝቅ ያለ ግምት፣ ስም ማጥፋት እና ማጠልሸት ከአማራ ሕዝብ ሥነ ልቦና የመነጨ እንዳልሆነ ሠራዊቱ ያውቃል ብለዋል፡፡
ሠራዊቱ ለሕዝብ ሰላም ሲባል ዛሬም ከኢትዮጵያዊነቱ ሳይወርድ ሕግ እንደመኪያስከብር ጠቁመው፤ መከላከያ ሠራዊት በጽንፈኛ ቡድኑ ላይ የሚወስደው ኦፕሬሽን የተጠና፣ አውድን የለየ፣ ጀሌን ከመሪ የነጠለ እና የቡድኑን ሴል በሚበጣጥስ መልክ የሚመራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከሰሞኑ በከተሞች አካባቢ የተፈጸሙት ርምጃዎች ውጤት ያሳዩ ነበሩ። መከላከያ የአማራን ሕዝብ ስለሚያከብር የክልሉ መንግሥት የጀመረው የሰላም ጥረት ዳር እንዲደርስ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። ከመንግሥት ጋር በሰላማዊ መንገድ የሚነጋገሩ ካሉ በሮቹ ያልተዘጉ ቢሆኑም መከላከያ ግን ሕግ ማስከበሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
ወታደራዊ ኦፕሬሽኑ በሚገባ የተጠና ነው ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ንጹሐንን ለመጠበቅ ሲባል በጥንቃቄ ይመራል። የማኅበራዊ ሚዲያው ጩኽት የሚጠበቅ ነው፡፡ በምንም መንገድ ቢሆን ግን መንገድ ዝጉ እና ተማሪዎች አይማሩም ከሚል ጽንፈኛ ቡድን ጋር ከዚህ ያለፈ ትዕግስት አይኖርም ብለዋል።
የአማራ ክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መከላከያ እና የክልሉ መንግሥት ሕግ የማስከበሩን ተግባር በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ተደጋጋሚ የሰላም ጥረቶችን አድርጓል ያሉት ቢሮ ኃላፊው፤ የሰላም በሮችን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ክልሉ ለከፋ ሠብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ተዳርጓል ነው ያሉት።
መንግሥት ሰፊ የሰላም አማራጮችን ዘርግቶ ችግሮችን በውይይት እና በምክክር ለመፍታት ቢሞክርም ምላሹ ግን በሚፈለገው መንገድ እንዳልሆነ ጠቁመው፤ መንግሥት ሳይወድ በግድ ሕግ ለማስከበር እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ተገዷል። መከላከያ እና የክልሉ መንግሥት ሕግ የማስከበሩን ተግባር በቅንጅት እየሠሩ ነው ብለዋል።
የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ እና ግጭቱን ለመቋጨት በርካታ መንግሥታዊ እና ሕዝባዊ ውይይቶች እና ምክክሮች ተካሂደው እንደነበር አስታውሰው፤ የታጠቁ ሃይሎች ምላሽ ግን የሕዝብን ስቃይ እና መከራ አባብሷል።
ይባስ ብሎ የታጠቁት ኃይሎች ከሀገሪቷ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ሳያፍሩ እና ሳይሸማቀቁ አስታውቀዋል ያሉት መንገሻ (ዶ/ር)፤ ጥምረታቸውም በመታዘዝ፣ በሎጀስቲክስ እና በወታደር ድጋፍ እንደተጀመረ መንግሥት ደርሶበታል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሕግ የማስከበር እርምጃ ይወስዳል።
ልሂቃን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የክልሉ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን መቆም እንዳለባቸውም አሳስበው፤ ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም