አዲስ አበባ፡- የኢሬቻ በዓል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከርና የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የከተማው ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ የኢሬቻ በዓል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከርና የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
ኢትዮጵያ የአደባባይ በዓላት ከብዝሃ ባህልና ከህብረ ብሔራዊነት የተገኙ ናቸው ያሉት ኃላፊዋ፤ በዓላቱ ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በህብረት ተሳስበው እንዲኖሩ ያደረጉ ምሰሶዎች ናቸው ብለዋል፡፡
በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የኢሬቻ በዓልም ከኢትዮጵያ የአደባባይ ክብረ በዓላት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዓሉ ህብረትን፣ አንድነት፣ መደጋፍን እና አብሮነትን የሚያጠናክር ከመሆኑም ባሻገር የፍቅር እሴቶች የሚሰበኩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢሬቻ ካለፈው ዘመን ወደ አዲሱ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገርን በማሰብ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት የአደባባይ በዓል መሆኑን የገለጹት ሂሩት (ዶ/ር)፤ ኢሬቻ በተለያየ አልባሳትና ጌጣጌጥ አሸብርቆ የሚከበር በመሆኑ ለጥበብ ውጤቶች ፈጠራና ሽያጭ አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በዓሉ በከተማዋ በርካታ ተሳታፊዎች በተገኙበት የሚከበር በመሆኑ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚረዳ ጠቅሰው፤ ኢሬቻ ለአዲስ አበባ ትልቅ በረከት ያለው በዓል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከተማዋን የቱሪስት መሸጋገሪያ ብቻ ሳይሆን መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችሉ የቱሪስት መስህብ ያለባት መሆኑዋን ጠቅሰው፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ጨምሮ የከተማ ልማትም ለቱሪዝም ዘርፉ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡
ኢሬቻና መሰል የአደባባይ በዓላት ደግሞ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በመግለጽ፤ በተለይም የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ባህልን ለመፍጠር ትልቅ መሠረት እንዳለው ጠቁመዋል።
በሀገር ውስጥ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የኢሬቻ በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ እየተሠራ መሆኑንም ኃላፊዋ ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ሚኤሳ ኤሌማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢሬቻ ሰው ከሰው እንዲሁም ከተፈጥሮ ጋር ሰላምን የሚያሰፍንበትና ስለ ሰላም የሚሰበክበት በዓል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል አዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማትና መልሶ ማልማት ሥራዎች አምራና ደምቃ ባለችበት የሚከበር በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ኃላፊው፤ በከተማዋ አምስቱም መግቢያ በሮች እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።
ለበዓሉ በከተማ ደረጃ የተለያዩ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ጠቅሰው፤ የኢሬቻ ኤግዚቢሽን፣ ፎረምን ጨምሮ በዓሉ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የ2017 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል “ኢሬቻ ለባህላችን ህዳሴ” በሚል መሪ ሃሳብ መስከረም 25 በሆራ ፊንፊኔ እና 26 በሆራ አርሰዲ እንደሚከበር መገለጹ ይታወሳል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም