ተኪ ምርቶች የሚያስገኟቸው ሀገራዊ ጥቅሞች

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለገቢ ምርቶች 18 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ወጪ እንደምታወጣ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ ግን ከአራት ቢሊዮን ዶላር የዘለለ አይደለም፡፡ ይህም የሀገሪቱ የንግድ ሚዛን የተዛባ እንዲሆን አድርጓል ይላሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡

የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማጠናከር እና ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ ኢትዮጵያ የተኪ ምርት ስትራቴጂ ቀርፃ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች። በዚህም በ2016 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለመሆኑ ተኪ ምርቶችን ማምረት ለዘላቂ ኢኮኖሚ እድገት ያለው አስተዋጽኦ ምንድነው? የሀገሪቱን ተኪ ምርት ለማሳደግስ ምን መሠራት አለበት? በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ ላይ የምሁራንን አስተያየት ጠይቀናል፡፡

በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ሙህዲን ሙሐሙድሁሴን እንደሚሉት፤ የአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ዋና ልኬት የሚባለው የምርት እድገት ነው፡፡

የሀገሪቱ የምርት ሂደት፣ ሥርዓት እና ምርትና ምርታማነት እየጨመረ ሲሄድ የኢኮኖሚ እድገት እያሳየች መሆኑን አመላካች ነው፡፡ የአንድ ሀገር ምርት አድጓል ስንል ገቢዋ ጨምሯል ማለት መሆኑን የሚጠቅሱት ባለሙያው፤ ይህም አዳዲስ የሥራ እድል እንዲፈጠር፣ የዜጎች ፍላጎት የሚያሟሉ ሸቀጦችና አገልግሎቶችን ማቅረብ ያስችላል፡፡

የዜጎች ኑሮ እየተሻሻለ፣ ድህነትም እየቀነሰ ይመጣል ይላሉ፡፡ አንድ ሀገር ሁሉንም ነገር አምርታ በራሷ መሸፈን የምትችልበት ሁኔታ አይኖርም የሚሉት አቶ ሙህዲን፤ ምግብና ምግብ ነክ፣ መድሃኒትና የጦር መሣሪያዎችን የመሳሰሉ ስትራቴጂክ ምርቶች ላይ ግን ራሷን ለመቻል መሥራት ይኖርባታል፡፡ ይህን ማድረግ የማትችል ከሆነ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሥርዓቱ ጫና እንዲያሳርፍበት ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ እንደ ሀገር ያለንን አቅም መለየትና ገቢ ምርቶችን መተካት፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆናም ምርቶቿን ለመሸጥ መሥራትም ለኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት የውጭ ምንዛሪ ለማዳን፣ ሠፊ የሥራ እድል ለመፍጠርና ዜጎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል ይላሉ።

ተኪ ምርቶች እንዲጨምሩ የሀገሪቱን የምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደሚገባ የሚገልጹት ምሁሩ፤ መሠረተ ልማትን መዘርጋት፣ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ ፈጠራን ማሳደግ፣ ከዓለም አቀፉ ገበያ ጋር ትስስር መፍጠርና ያሉ እድሎችን አሟጦ መጠቀም እንዲሁም የገበያ ሥርዓቱን ጤናማና ዘመናዊ ማድረግ ይገባል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ኢኮኖሚውን የሚመሩና የሚደግፉ ተቋማትን የመፈጸም አቅም ማሳደግ፣ የሚወጡ ሕግና ደንቦች ለሥራ ያላቸውን ምቹነት መፈተሽ ላይም መሥራት እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ የሚሠሩ ሥራዎች ዘላቂ ልማትን እንዲያረጋግጡ የሥራ አጥነት መቀነስ፣ የኑሮ ውድነቱ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራትና የሀብት ፍትሐዊነትን ማጠናከር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር አቶ ፍሬዘር ጥላሁን በበኩላቸው፤ በሀገር ውስጥ መመረት ሚችሉ በርካታ ምርቶችን ከውጭ እናስመጣለን፡፡ ይህም ሀገሪቱ በውጭ ምርቶች ላይ ጥገኛ እንድትሆን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንድታወጣ ያደርጋታል። እናም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና ለፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን ማምረት አንዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ነው ይላሉ፡፡

የሀገር ውስጥ ምርቶች ተቀባይት እንዲጨምርም ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍ ያለ ቀረጥ መጣልና የኮታ መጠን ማስቀመጥ እንደሚቻል የሚጠቁሙት ባለሙያው፤ ይህን ርምጃ ከመውሰዳችን በፊት ግን ያለውን አቅርቦትና ፍላጎት ማወቅ ያስፈልጋል። ከዚህም በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ሲመረቱ የሚያስወጡት ወጪ ከውጭ ከሚገቡበት የበለጠ ወጪ የሚያስወጣ አለመሆኑንም ማጥናት አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ስናስብ የምርቱን አዋጭነት፣ ቀጣይነትና ጥራቱን በሚፈለገው ልክ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አመላክተው፤ ማህበረሰቡ ሀገራዊ ምርቶችን ገዝቶ መጠቀም ላይ ያለውን ፍላጎት ለማሳደግ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ላይ መሥራት ይጠበቅብናል ባይ ናቸው፡፡ አምራቾችም የሕብረተሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ምርት ማምረት ይኖርባቸዋል ፡፡

እንደ ምሁራኑ ገለጻ፤ ሀገራዊ ምርትና ምርታማነት ስናሳድግ የሥራ እድል እንዲፈጠር፣ ምርቶችን በበቂ ሁኔታና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ያስችላል። የማህበረሰቡ ገቢ እንዲያድግና የኑሮ ሁኔታውም እንዲሻሻል ያደርጋል፡፡

ሀገሪቱ ለገቢ ምርቶች የምታወጣውን ወጪ ለመቀነስ ተኪ ምርቶችን በብዛት፣ በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገበ የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You