ዜና ሀተታ
በአባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች ግንባር ቀደምነት ‹‹መሬ..ሆ›› በተሰኘው ዜማ በሚታጀበው የኢሬቻ በዓል ታዳሚያን ባህላዊ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች እና ቁሳቁሶች ይዘው ደምቀውና ተውበው የሚታዩበት በዓል ነው። በአሁኑ ወቅት በክብረ በዓሉ ዋዜማ ላይ የኦሮሞ ባህላዊ ጭፈራዎች እና መሰል ባህላዊ ትዕይንቶች በተለያዩ አካባቢዎች በደማቅ ሥነ ሥርዓት እየቀረቡ ነው፡፡ በዓሉን አስመልክቶ የተዘጋጀ ባዛር እና ኤግዚቢሽንም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በይፋ ተከፍቷል።
በባዛር እና ኤግዚቢሽኑ የተለያዩ ባህላዊ አልባሳትን ሲሸጡ ያገኘናቸው ወይዘሮ ፋጡማ ሁሴን፤ በመጪው ቅዳሜና እሁድ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል ማድመቂያ የሚሆኑ ባህላዊ አልባሳትን በተሻለ ጥራት ማቅረባቸውን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጸዋል።
በዘንድሮው ዓመት የባሌ፣ የወለጋ፣ የአርሲ፣ የጉጂ፣ የቦረና፣ የሸዋ እንዲሁም በተለያዩ የኦሮሞ አካባቢዎች የተለመዱ ባህላዊ አልባሳት በስፋት ለገበያ ማቅረባቸውን ይናገራሉ። የሁሉንም አካባቢ ባህል ያማከሉ አልባሳት በብዛት ከመቅረባቸው በላይ በጥራትና በዲዛይን የተሠሩ ናቸው ይላሉ።
በጥራትና በዲዛይን አማራጮች ላይ ትኩረት ያደረጉ አልባሳትና ጌጣጌጦች በመኖራቸው ሸማቾች ግብይት እየፈጸሙ መሆኑን ገልጸው፤ የባህል አልባሳቱ ዋጋ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ብዙ ጭማሪ እንዳላሳዩ እና ባህላዊ ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩ በሸማኔ እንዲሁም በአልባሳት ባለሙያዎች ተዘጋጅተው መቅረባቸውን አመላክተዋል።
የወንዶች ባህላዊ ሸሚዞች ከ 700 እስከ አንድ ሺህ 200 ብር ለገበያ መቅረባቸውን አስረድረተው፤ የሴቶች ሙሉ አልባሳት ደግሞ ከሁለት ሺህ 500 እስከ አምስት ሺህ ብር ድረስ ገበያው ላይ እየተሸጠ መሆኑን ገልጸው፤ የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት በወርሃ መስከረም በኢሬቻ በዓል ወቅት ብቻ ሳይሆን ጋብቻ ፈጻሚ ጥንዶችም የባህል አልባሳት ተጠቃሚ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡
ለበዓሉ የሚቀርቡት አልባሳት የኦሮሞን ባህል አጉልተው ከማሳየታቸው በተጨማሪ የባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦችን ለምንሸጥ ነጋዴዎች ከፍተኛ የኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አስገኝተውልናል ብለዋል። ትውልዱ ባህሉ፣ እምነቱንና የቀደምት አባቶቹን የአለባበስ ሥርዓት ጠብቆ በማቆየት ረገድ ኢሬቻን የመሳሰሉ በዓላት የጎላ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
የቄሮን የቀሬን እንዲሁም የአባ ገዳን የአለባበስ ሥርዓት ጠብቀው የሚዘጋጁ የባህል አልባሳት ከጊዜ ወደ ጊዜ በአይነትም በብዛትም እየጨመሩ መጥተዋል ያሉት ደግሞ የኦሮሞ ባህል አልባሳት ነጋዴዋ ወይዘሮ አሻ ሮባ ናቸው፡፡ የለበሱት አልባሳት የኦሮሞ አርሲ አለባበስ መሆኑን ገልጸው፤ ሙሉ ልብሱ ከሁለት ሺህ 500 እስከ ሶስት ሺህ ብር ድረስ እንደሚሸጥ ገልጸዋል።
በየዓመቱ በመስከረም ሦስተኛ ቅዳሜና እሑድ ላይ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ዘንድሮ መስከረም 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ በማግስቱ እሑድ በቢሾፍቱ ከተማ ይከበራል። የአዲስ አበባው በዓል ‹‹ኢሬቻ ሆረ-ፊንፊኔ›› ሲባል፣ የቢሾፍቱው ‹‹ሆረ አርሰዲ›› ይባላል፡፡
የኢትዮጵያን የዓመት መጀመርያ የሆነውን መስከረምን ከሚያደምቁት በዓላት አንዱ የሆነው ኢሬቻ፣ ከክረምት ወደ ብርሃን መውጣትን ምክንያት በማድረግ ምሥጋና የሚቀርብበት ሥነ ሥርዓት መሆኑ ይነገራል፡፡ የሚሞገሰው ልምላሜ ነውና ለምለም ቄጠማና አደይ አበባ እንዲሁም ባህላዊ አልባሳት የበዓሉ ልዩ መገለጫ ሆነው ይታያሉ፡፡
በአዲስ አበባ የተከፈተው ባዛር እና ኤግዚቢሽኑ ከነገ ጀምሮ እስከ መስከረም 24 ድረስ ይቆያል ተብሏል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም