በዘመነ ኢህአዴግ ይቺ ቃል በጣም ታዋቂ ነበረች። በቀልዱም በቁም ነገሩም ‹‹ጀርባው ይጠና›› የሚለው ቃል በተደጋጋሚ አገልግሎት ላይ ይውል ነበር። ቀልዶች የተፈጠሩት የየተቋማቱ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በውሃ ቀጠነ ምክንያት ሁሉ የዓይኑ ቀለም ያላማራቸውን ሠራተኛ ወይም ኃላፊ ‹‹ጀርባው ይጠና›› ይሉ ስለነበር ነው። የተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ይህን ንግግር የወረሱት የበላይ አለቆቻቸው በጋዜጣና መጽሔት ሥርዓቱን ይሞግቱ የነበሩ ሰዎችን ‹‹ጀርባው ይጠና›› ሲሉ ይሰሙ ስለነበር ነው።
የፖለቲካ ባህላችን አሁንም አልተሻሻለም። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሰፊው የምንታዘበው ህፀፅን መናገርን አለመውደድ ነው። እርግጥ ነው ሁሌ ችግርን ብቻ መናገር ጤነኝነት አይደለም፤ የሚደነቁ ነገሮችን በሚገባ አድንቀናል። ዳሩ ግን የሚታዩ ችግሮችን የሚናገርን ሁሉ እንደ ጨለምተኛ ማየትም ጤነኝነት አይደለም፤ ሰዎች ቢያንስ ተናግረው ሊወጣላቸው ይገባል፡፡
በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አንድ የሚገርመኝ ነገር ‹‹ጀርባው ይጠና›› የሚባለው ነገር ነው። ድሮም ሆነ ዛሬ ጀርባ አጥኚዎች የማን ጀርባ መጠናት እንዳለበት አያውቁም። ብዙ ጊዜ ‹‹ጀርባው ይጠና›› ሲባል የምንሰማው በግልጽ እና በድፍረት የሚናገርን ሰው ነው። በግልጽ እና በድፍረት የሚናገር ሰው እኮ ምንም የሚጠና ጀርባ የለውም። በማህበረሰባችን አባባል እንዲህ አይነት ሰው ‹‹የግንባር ሥጋ›› ይባላል። ፊት ለፊት የሚታይ ማለት ነው፤ ነገሩ ሁሉ ግልጽ የሆነ ማለት ነው። ስለዚህ በግልጽ እና በድፍረት የሚናገርን ሰው፤ የተናገረው ነገር ትክክል አለመሆኑን መንገር እንጂ የሚጠና ጀርባ የለውም። የተናገረው ነገር የማይጠቅም መሆኑን መንገር፣ የማያዋጣና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን መንገር እንጂ ‹‹ጀርባህ ይጠና›› ማለት አጉል ፍርሃት ነው።
‹‹የእገሌ ተላላኪ!›› የሚል ስም መለጠፍ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ኋላቀር የፖለቲካ ባህላችን ነው። የጥፋት ኃይሎች ተላላኪ የሆነ ሰው እኮ እየተንጨረጨረ አይደለም የሚናገረው። የጥፋት ኃይሎችን የጥፋት ዓላማ የያዘ ሰው ተመሳስሎና ሳያስነቃ ነው እንጂ ሥራውን የሚሠራ በግልጽ እየተናገረ አይደለም። በአሠራሮች እየተቆረቆረ ‹‹ይህ ይስተካከል›› ሊል አይችልም። ብልሹ አሠራሮችን እየሞገተ ስውር ተልዕኮ ሊይዝ አይችልም።
ከዚህ ይልቅ መንግሥት ብልጥ ከሆነ ማጥናት ያለበት ከልክ በላይ የሚያሽቃብጡ የሥራ ኃላፊዎችንና ባለሥልጣናትን ጀርባ ነው። ሆዳቸው የማይታወቅ ሰዎችን ነው።
በነገራችን ላይ አንድ ሀቅ እንተማመን። አብዛኛው የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ራሱን የሚሸውድ ነው። በሚያወራው ነገር አያምንበትም። እስኪ ማን ይሙት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን በቋሚነት ይከታተላሉ? ከቤታቸው ቢገባ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ተከፍቶ ይገኛል? ጠረጴዛቸው ላይ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ይገኛል? ልጆቻቸው የመንግሥት ትምህርት ቤት ይማራሉ? ዓላማቸውና የረጅም ጊዜ ዕቅዳቸው ከሀገር ውጭ መሆኑን አናውቅም?
ለዚህም ነው አንድ በመንግሥት ተቋም ውስጥ ከሠራተኝነት እስከ ከፍተኛ ኃላፊነት ወይም በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣንነት የቆዩ ሰዎች ከሀገር ከወጡ በኋላ ሲያገለግሉት የነበረውን ተቋም ወይም መንግሥት የሚራገሙት። ጀግና ከሆኑ እነዚያን ችግሮች መናገር የነበረባቸው ባለቡት የሥራ መደብ ወይም ኃላፊነት ላይ ሆነው ነው። አለበለዚያ ራሳቸውን እየሸወዱ ነበር ማለት ነው። ራሳቸውን እየዋሹ ነበር ማለት ነው። እየኖሩ የነበረው የማያምኑበትን ነበር ማለት ነው። አሁንማ እንዲያውም ጭራሽ ባህል ተደርጎ ‹‹እና የመንግሥት ቤት ሆኜ ይሄን ልናገርልህ ነው?›› ይላሉ። አስመስሎና ራስን ሸውዶ መኖር ባህል ሆነ ማለት ነው?
ጋዜጠኛና ደራሲ በረከት በላይነህ ከወራት በፊት በአንድ ፖድካስት ላይ ቀርቦ፤ የመንግሥት ተቋም ውስጥ ገብቶ በኃላፊነት መሥራት እንደሚፈልግ ሲናገር፤ ጠያቂው ‹‹የመንግሥት ቤት ውስጥ የምትፈልገው ነፃነት አለ ወይ?›› ብሎ ጠየቀው። ጠያቂው ሲባል ከሚሰማው ነገር ተነስቶ ይህን ጥያቄ መጠየቁ ትክክል ነው። የበረከት መልስ ግን ብዙዎችን አስገርሞ ነበር።
የበረከት መልስ ሲጠቃለል፤ አንዳንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከልክ በላይ የሚያሸረግዱት መንግሥት በዚያ ልክ ሁኑልኝ እያላቸው አይደለም። በራሳቸው እውደድ ባይነት ባህሪ ነው። በዚያ ልክ መሆን ግዴታ አይደለም ብሎ ያምናል ማለት ነው በረከት በላይነህ፡፡
በእርግጥ እዚህ ላይ አከራካሪ ነገር ይነሳል። መንግሥት ሲባል እስከ የት ድረስ ያለው ነው? የሚለው ያከራክራል። ምክንያቱም ከጥበቃና የጽዳት ሥራ ጀምሮ የመንግሥት አካል ነው። በልማድ ግን መንግሥት የምንለው በዋናነት የሀገሪቱን መሪ እና ሌሎች በከፍተኛ ባለሥልጣን ላይ ያሉትን ነው። እነዚህ አካላት የበታች አመራሮችንና የየተቋማቱን የሥራ ኃላፊዎች በዚያ ልክ እንዲሆኑላቸው ያዝዟቸው አያዝዟቸው ማወቅ አይቻልም። ምናልባት ራሳቸውም ከፍተኛ አመራሮች ወደውት ካልሆነ በስተቀር ‹‹በዚህ ልክ አትሁኑ›› ብለው መምከር ይችሉ ነበር።
ወደ ጀርባ ጥናት እንመለስ።
ብዙ ጊዜ የውጭ ሀገር ዕድል ተሰጥቷቸው ወይም ለሥራ ተልከው ሀገራቸውን ከድተው የሚቀሩት ጋዜጠኞችም ሆኑ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ከልክ በላይ ታማኝ የነበሩ ናቸው። የኮምፒውተራቸውን እና የስልካቸውን ስክሪን ሽፋን የየወቅቱን የሀገሪቱን መሪ ምስል የሚያደርጉ ናቸው። በየንግግሮቻቸው ሁሉ የየወቅቱን መሪ ንግግሮች እያጣቀሱ የሚያወድሱ ናቸው። መጠናት ያለበት የእነዚህ ሰዎች ጀርባ ነው። እነዚህ ሰዎች ዕድሉን ቢያገኙ ሀገራቸውንም ተቋማቸውንም ከመክዳት አይመለሱም። ብዙዎችን አይተናል። ጥገኝነት ለመጠየቅ የሀገራቸውን ችግር መናገር ሲበቃቸው የግለሰቦችን ገመና ሁሉ እያወጡ የሚያብጠለጥሉ ናቸው። ዕድልና አጋጣሚ የሚጠብቁ አስመሳዮች ነበሩ ማለት ነው።
ብልሹ አሠራሮችን በግልጽ እና በድፍረት የሚናገሩ ሰዎች ግን ተቆርቋሪዎች ናቸው። ‹‹ምን አገባኝ!›› በማለት ሀገርና ተቋምን ለመክዳት ዕድልና አጋጣሚ የሚጠብቁ አይደሉም። የተቋማቸውም ሆነ የሀገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል፤ የሚንጨረጨሩትና በብሶት የሚናገሩትም ስለሚያገባቸውና ስለሚቆረቆሩ ነው። እንደማንኛውም ሰው ‹‹ምን አገባኝ!›› ማለት ይችሉ ነበር። በኃላፊነት ላይም ሆነ በተራ ሠራተኝነት ላይ ሆኖ ‹‹ምን አገባኝ!›› ማለት ገለልተኝነት ሳይሆን እልም ያለ ስንፍና ነው።
በእርግጥ የመንግሥት ፍርሃትም ይገባኛል። ብልሹ አሠራሮችን የሚናገሩ ሰዎች ሌሎች ሠራተኞችንም ያነቃቃሉ፤ ወቀሳ ይበዛብኛል ከሚል ፍርሃት ነው። ይህ ግን ራስን መሸወድ ነው። ሰዎች ጤነኛ የሚሆኑት ተናግረው ሲወጣላቸው ነው። አለበለዚያ አለቃ ፊት እየተልመጠመጡ በየኮሪደሩ ግን በሀሜትም ቢሆን መውቀሳቸው አይቀርም። በነገሥታቱ ዘመን ‹‹እረኛ ምን አለ?›› ይባል ነበር አሉ። በአደባባይ የተከለከለ ሕዝብ በእሳት ዳር ጨዋታ መንግሥትን ስለሚያማርር ማለት ነው። በአደባባይ በግልጽ የሚናገር ሰው ግን ሹክሹክታ አይወድም። ተናግሮ ጨረሰ፣ ጆሮ ጠቢ ሰማኝ አልሰማኝ ግራ ቀኙን እያየ ሀሜት አያበዛም። አድርባይና ፈሪ ግን ተጠራጣሪ ይሆናል፤ በዙሪያው ያለ ሰው ሁሉ ሰላይ እየመሰለው በራስ መተማመን ያጣል።
ከፍተኛ አመራሮችም ሆኑ ተራ ሠራተኞች ብግልጽ እንድናገሩ ካልተደረገ፣ በሆነ አጋጣሚ ከሀገር ሲወጡ ያላዩትንና ያላጋጠማቸውን ሁሉ እየጨማመሩ ያወራሉ ማለት ነው። ስለዚህ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ነፃ ውይይቶችን ይፍቀዱ፣ ያመቻቹ። የማን ጀርባ መጠናት እንዳለበትም ልብ ይበሉ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም