“140 የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን ተከታትለናል፣ ፕሮጀክቶቹ ከጊዜና ከዋጋ ጋር በተያያዘ በጣም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው” ኢንጂነር መስፍን ነገዎ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን የኮንስት ራክሽን ኢንዱስትሪውን ውጤታማ ለማድረግ ቁልፍ ዓላማ ይዞ የተቋቋመ መንግሥታዊ ተቋም ነው። የኮንስትራክሽን ዘርፉ በዋጋ፤ በጥራት፤ በጊዜ እና በአካባቢ ደህንነት ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል ትልቅ ተልዕኮ ወስዶ እየሰራ ያለ ነው።

በዛሬው የተጠየቅ ዓምዳችን በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ፣ እያጋጠሙት ባሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ የባለሥልጣኑን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን ነገዎ አነጋግረን በሁለት ተከታታይ ክፍሎች ለአንባቢዎቻችን የምናቀርብ ሲሆን፤ ክፍል አንድ እነሆ፡-

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ በአዋጅ ከተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት አኳያ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ኢንጂነር መስፍን፡- እንደ ተቋም በዋናነት አምስት ሥራዎች አሉን። የመጀመሪያው ጥናት እና ዝግጅት ነው። ጥናትና ዝግጅት ሲባል ኮድና ስታንዳርድ ያጠናል፤ ያዘጋጃል፤ ወደ ሥራ እንዲገባ ያደርጋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የአሰራር ሥርዓቶችና ዘዴዎችን በማጥናት ወደ ሥራ እንዲገባ የሚያደርግ ነው።

ሁለተኛው የምዝገባ እና ሰርቲፊኬሽን ሥራ ነው። በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሳተፉትን ባለሙያዎች፣ ኩባንያዎችና ማሽነሪዎች ይመዘግባል፤ ሰርቲፊኬሽን ይሠጣል፤ በሶስተኝነት የቁጥጥር ሥራ ይሰራል። ስታንዳርዶች ሥራ ላይ እንዴት እንደዋሉ ይቆጣጠራል። ይህ ማለት ሌሎች መሥሪያ ቤቶችና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያወጣውን የሕግ ማዕቀፍ ኮድና እና ስታንደር ጨምሮ እንዴት እንደሚተገበር ይቆጣጠራል።

ተቋሙ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ሬጉላቶሪ ኮምፒልያንስ›› ይሰራል። ሌላው ቁጥጥር ደግሞ በተለይ በኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ላይ ኮድ እና ስታንዳርድን በተመለከተ የፌዴራል ፕሮጀክቶች አሰራሮች ጋር በትክክል ስታንዳርድ ዲዛይን ተደርገው መሰራታቸው ይመረምራል። የሚስተካከል ነገር ካለ እንዲስተካከል ካልሆነ ግን ወደ ተግባር እንዲሄድ የሚያስችሉ ሥራዎችን ይሰራል።

በፌዴራል ደረጃ ያለውን የዲዛይን ክለሳ በተለይ የፌዴራል መንግሥት ስፖንሰር የሚያደርጋቸውን ፕሮጀክቶች እኛ (ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ) እንሰራለን። ይህ ከቁጥጥር አካል አንጻር የሚታይ ነው። ሌላው ደግሞ እነዚህ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ በዲዛይንና በውል መሰረት መፈጸማቸውን ይከታተላል።

በተጨማሪም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚፈጠሩ ውዝግቦችን ይፈታል። ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውዝግብ ይበዛበታል። አንዳንድ ጊዜ የሚፈጠሩ ውዝግቦች ወደ ፍርድ ቤት ይሄድና 15 እና 20 ዓመት ድረስ ይቆያል። በዚህ ወቅት የኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በአማራጭ የውዝግብ አፈታት ሥርዓት ችግሮች እንዲፈቱ ያደረጋል።

ይህ አሰራር በፊት ያልነበረና አዲስ ትግበራ ላይ የዋለ አሰራር ነው። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አሰራሩን ተግባራዊ ለማድረግ ባለፈው ዓመት የማደራጀት እና የአሰራር ሥርዓቶችን የማስተካክል ሥራ ሲሰራ ቆይቷል። አሁን ወደ ሥራ ገብተን አንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳክቶልናል። አንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ ግን ከሕግ ክፍተት አለ፡፡

በባለሥልጣኑ አዋጅ 1237 የሚፈቅደው ለኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርና ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ነው። ስለዚህ መሥሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ አሁን ላይ ዓቃቤ ሕግ መሥራት አትችሉም በማለቱ ሕጉ ላይ ማስተካከያ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ነገር ግን አጠቃላይ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚፈጠሩ ውዝግቦችን የመፍታት ስልጣን ለኮንስትራክሽን ባለስልጣን ተሰጥቷ። በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ካልተፈታ ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳል።

አዲስ ዘመን፡- በ2016 በጀት ዓመት ምን

አቅዳችሁ ምን አሳካችሁ? በ2017 በጀት ዓመት ምን አቅዳችሁ እየሰራችሁ ነው?

ኢንጂነር መስፍን፡- በ2016 በጀት ዓመት በርካታ እቅዶች ነበሩን። ዋና ዋናዎቹ ግን ከዝግጅት እና ጥናት ጋር ተያይዞ ሁለት ክፍተቶች ነበሩ። እነሱም ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባብር ስናጠና ቆይተናል፤ አሁን ላይ ጥናቱ ወደ ማጠቃለያው የደረሰ ሲሆን ይህን ለመተግባር የሚያስችል ሶፍትዌር እየበለጸገ ነው።

የሶፍትዌር ልማት ከምንለው አንደኛው የኮንስትራክሽን ዋጋ ጥናት ነው። ከዚህ ቀደም በነበረው አካሄድ እያንዳንዱን አማካሪ ወይም ‹‹ኮንሶልታንት›› የሚሰራው እንደፈለገ በራሱ መንገድ ነበር። ምክንያቱም በሳይንሱ በርካታ የአሰራር ስልቶች በመኖራቸው እና በሀገራችን እነዚህን ስልቶች የሚመራ አሰራር ስላልነበረ ነው፡፡

አንዳንድ ሀገራት በራሳቸው አሰራሩን የሚመራ አሰራር ይኖራቸዋል። በእኛ ሀገር ግን አሰራሩ ስላልነበረ ልቅ ነበር አማካሪ ድርጅቶች እንደፈለጉ ሲሆኑ ቆይተዋል። አሁን ላይ ግን አስጠንተን መመሪያ እየወጣ ነው። ከጸደቀ በኋላ ወደ ሥራ እንገባለን። ይህም ወጥ የሆነ የኮንስትራክሽን ግምት አሰራር ለማውጣት ያግዛል። የኮንስትራክሽን ዋጋ ተገማችነት እንዲኖር ያስችላል።

ሌላው በባለፈው ዓመት በዋነኝነት የሥራ ነው የፕሮጀክቶች የሥራ ማጠናቀቂያ ጊዜ መገመቻ እና ፐርፎርማንሳቸውን የሚመዝን ሶፍትዌር እየተዘጋጀ ነው። አማካሪዎች ብዙ ጊዜ የሚያደርጉት ትልልቁንም ትንንሹንም ፕሮጀክት በአስራ ስምንት ወር እንደሚጠናቀቅ ይገልጻሉ። ሶስት እና ከዚያ በላይ ዓመት የሚፈጀውን ፕሮጀክት በአስራ ስምንት ወር ይጠናቀቃል ይላሉ። አማካሪዎቹ ፕሮጀክቶች በ18 ወራት እንደማይጠናቀቅ እያወቁ በ18 ወራት እንጨርሳለን የሚሉት በእኛ ሀገር ሕግ ፕሮጀክት ከተጀመረ ከ12 እስከ 18 ወራት በኋላ የዋጋ ማስተካከያ ማድረግ ስለሚፈቀድ ነው። እነዚህ ወራቶች ከመሙላታቸው በፊት ግን የዋጋ ማሻሻያ ለማድረግ ሕጉ አይፈቅድም። በመሆኑም ውል ከታሰረ በኋላ ኮንትራክተሮቹም ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ እንዳይጀመር ምክንያቶችን ይደረድራሉ።

ብዙ ጊዜ ኮንትራክተሮች ሥራ ሲጀምሩ የሥራ መጀመሪያ ጊዜውን በማጓተት ሶስተኛ ወር ወይም ከሶስት ወር በኋላ እንዲጀመር ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ በተባለለት ጊዜ እንዳይጨርሱ ያደርጋቸዋል፤ የዋጋ ማስተካከያም እንዲጠይቁ በር ይከፍትላቸዋል። ይህን ችግር ለመፍታት እንዲቻል የፕሮጀክቶችን ዋጋ እንደሚገምተው ሶፍትዌር ዓይነት እያንዳንዱን ማለትም ጊዜውንም የሚመራ ሶፍትዌርና ማንዋል እየተጠና ነው፡፡

ሌላው ከዚህ ቀደም የሊፍት ስታንዳርድ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ‹‹ኦፕሽናል›› ነበር። አሁን ላይ ራሱን የቻለ ስታንዳርድ በማዘጋጀት ወደ ማስገደድ ልንሄድ ነው። ምክንያቱም አሁን ላይ በአዲስ አበባ የሕንፃዎች ርዝመት እስከ 48 ፎቅ ደርሷል፤ በዲዛይን ደረጃ ደግሞ ከ63 እስከ 73 ድረስ እየመጣ ነው።

እንደሚታወቀው ሊፍት ማለት ‹‹ቨርቲካል ትራንስፖርቴሽን›› ነው። (ወደ ላይ እና ወደ ታች የሚደረግ ትራንስፖርት ዓይነት ነው፡፡) ወደ ጎን ለሚሄዱት ትራንስፖርቴሽን አገልግሎት ለሚሰጡ እንደ ባጃጆችን እና ትናንሽ ተሽከርካሪዎች ሳይቀር አስገዳጅ ቦሎ (አካል ምርመራ) እና ለሹፌሮችም የብቃት ማረጋገጫ እየሰጠን ባለንበት በዚህ ወቅት ለሊፍቶች ግን ምንም ዓይነት የብቃት ማረጋገጫ እና ስታንዳርድ የለንም።

ከሊፍት ጋር ተያይዞ የሌሎች ሀገራትን ስናይ የሊፍቱን ጤንነቱን የሚከታተል ቴክኒሽያን ይኖራል፤ ሊፍቱ ጤነኛ ነው ወይስ አይደለም ለሚለውም ራሱን የቻለ ስታንዳርድ አለው። በስታንዳርዱ መሰረት ጤንነቱ በየዓመቱ እየተፈተሸ ልክ እንደተሽከርካሪ ‹‹ቦሎ›› ይደረጋል። ይህንን እንቅስቃሴ ወደ አስገዳጅነት እንዲሻገር ለማድርግ ከደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር በመነጋገር በጋራ እየሰራን ነው። በጥሩ ሂደት ላይም እንገኛለን ፤ ስታንዳርዱ ለቴክኒክ ኮሚቴ ቀርቦ ለማጸድቅ በሂደት ላይ ነው፡፡

ከምዝገባና ሰርቲፊኬሽን አኳያ ያቀድናቸው እቅዶች አሉ፤ መሻሻል ያለባቸው አንዳንድ ቅሬታዎችን ለመፍታት በ2017 ዓ.ም ላይ እንደ ትልቅ ሥራ ይዘነዋል። ከዲዛይን ክለሳ ጋር በተያያዘ ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የመጡትን ዲዛይኖች ሪቪው አድርገን መልሰናል። የተገኙ ግኝቶችን በሶስት ከፍልን ማየት እንችላለን። አንደኛው ዋጋ ማጋነን አለው። ሁለተኛው ደግሞ በስታንዳርዱ መሰረት ዲዛይን አለማየት ችግር ነው። ሶስተኛው ዲዛይኖቹ ‹‹ናሽናል ኮፒታቲቭ›› መሆን ሲገባቸው ‹‹ኢንተርናሽናል ኮምፒታቲቭ›› ሆነው ቀርበዋል።

ይህ ማለት በፕሮጀክቱ ውስብስብነትና በፕሮጀክቱ የዋጋ ከፍታ የዓለም አቀፍ ጨረታ እንዲሆን ነው። ዓለም አቀፍ ጨረታ ሲሆን ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የእኛን ሀገር ኩባንያዎች መወዳደር ይችላሉ። ስለዚህ ይህን የማስተካል ሥራ ሰርተናል።

ከቁጥጥር አንጻር በሕጎች እና በኮዶቹ አተገባበር ላይ በስፋት የሕግ ጥሰቶች ስለሚፈጸሙ በ10 ከተሞች በርካታ ሥራዎችን ሰርተናል። ችግሩን ከክልል መንግሥታቶች እና ከተማ አስተዳደር ጋር ተነጋግረን የምናስተካክለው ቢሆንም በተለይ አዋጅ 624ን ከመተላለፍ አኳያ ችግሮች በስፋት ይታያሉ።

ለምሳሌ አዲስ አበባን ብትወስዱ ከጂ+5 በላይ የሆኑ ህንጻዎች ሲገነቡ ባለው ሂደት ከሕጉ አንጻር መወጣጫቸው መሆን የሚገባው ከብረት የተሰራ ነው። ነገር ግን አዲስ አበባ ላይ በግንባታ ሂደት ለሚገኙ ህንጻዎች መወጣጫ የባህር ዛፍ አጠናን ይጠቀማሉ። በዚህ የተነሳ በቅርቡ ቦሌ ሁለት ሰዎች ወድቀዋል። በተመሳሳይ ካርል አደባባይ አካባቢ በሊፍት ውስጥ በሚሠራ ሥራ የወደቁ አሉ። በአዲስ አበባ ከመወጣጫ ብረቶች ስታንዳርድ ጋር ክፍተቶች አሉ። ከዚህ በመነሳት ለአዲስ አበባ ቁጥጥር እና ዲዛይን ባለሥልጣን ስለ ስታንዳርዱ ግብረ መልስ ሰጥተን ችግሮቹ እንዲስተካከል ተደርጓል።

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በሕግ ተቆጥሮ ከተሰጡት ሥራዎች መካከል ፕሮጀክቶችን መቆጣጠር ነው። ከዚህ አንጻር ባለፈው ዓመት 140 የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን ተከታትለናል። ለብዙዎቹ ወዲያውኑ ግብረ መልስ ሰጥተናል። በተመለከትናቸው ፕሮጀክቶች ላይ በተለይም ከጊዜና ከዋጋ ጋር በጣም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው። ለዚህም ዋና ምክንያቱ አንደኛው ዋጋ የሚቀያየረው ቶሎ ነው፤ በዚህም የዋጋ ማስተካከያ ይጠይቃሉ። ሁለተኛው ክፍያ ጠይቀው ሶስት እና አራት ክፍያ ሳይከፈላቸው በአሰሪ መሥሪያ ቤት የቆየባቸው በስፋት አሉ። እንደዚህ ዓይነት ግኝቶች ተገኝተዋል።

ባለፈው ዓመት ከሰራናቸው ሥራዎች መካከል የኮንስርሽን ኦዲት ነው። በዚህም በአምስት ፕሮጀክቶች ላይ የኮንስትራክሽን ኦዲት ሰርተናል። ነገር ግን የኦዲት ሥራው ያላለቀ ስለሆነ ውጤቱ ገና ነው። እሱ ካለቀ ግን ወደ ሕግ የሚሄድም ጉዳዮች አሉት። ከአሰራር ሥርዓት ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት ለሽልማት በቅተን ነበር።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የ2016 ዓ.ም የዲጂታል ትገበራ ተቋም (dijitale inablede institution) ኢትዮ ስታንዳርድ ተሸልመናል። ይህም 26 የሚሆኑ አገልግሎቶችን በኦንላይን በመስጠት የተገኘ ሽልማት ነው። የግዥ ሥርዓቱን በተቀመጠው የሀገሪቱ ሕግ መሠረት በማከናወን ካሉት ተቋማት ሁለተኛ ደረጃን ይዘን አጠናቀናል። ‹‹ኢፍ ሚስን›› በመጠቀም ወይም በፋይናንስ ኤሌክትሮኒክስ ሲስተም ሙሉ በሙሉ በመጠቀም በሚል አቢሲኒያም ሽልማት አበርክቶልናል። ይህ ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጥሩ ስኬት ነው።

አዲስ ዘመን፡- በበጀት ዓመቱ በተቋሙ የሥራ እንቅስቃሴ ያጋጠሙ ችግሮች ምንድን ናቸው?

ኢንጂነር መስፍን፡- ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤታችን ኦዲት አድርጎ ነበር። እሱ ላይ የምንቀበላቸውና የማንቀበላቸው ክፍተቶች ነበሩ። ለምሳሌ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት 41 ፕሮጀክቶችን ኦዲት አድርጓል። ከነዚህ ፕሮጀክቶች ግማሾቹ በፍርድ ቤት ቆመዋል፤ ግማሾቹ ደግሞ ፋይናንስ የሚደርጋቸው አካል አቋርጧቸዋል። ገሚሶቹ ደግሞ እኛ ከመመስረታችን በፊት ከ12 እስከ 15 ዓመት የቆዩ ናቸው።

እነሱ እንደ ግኝት የወሰዱት ተፈጠሩ የተባሉ ችግሮችን ለገንዘብ ሚኒስቴር በደብዳቤ ማሳወቅ ነበረባችሁ የሚል ነው። ለገንዘብ ሚኒስቴር አሳወቃችሁ ለፕሮጀክቶቹ አንድም በጀት ተሰጥቶ እንዲቀጥል ካልሆነም እንዲቋረጥ ማድረግ ነበረባቸው በሚል ነው። ይህንን እንደ ግኝት በመቁጠር መንግሥት ለኪሳራ ተዳርጓል በሚል ዋና ኦዲተር ጉዳዩን ፓርላማ አቅርቧል።

ሌላው እንደ ክፍተት የምናየው እንደሚታወቀው የፕሮጀክት ቁጥጥሩን የምናገኘው በምንፈልገው ልክ አይደለም። ለምሳሌ የመገጭን ፕሮጀክት ብንወስድ

20 ዓመት ቆይቷል። በ20 ዓመታት ውስጥ የተከናወኑ ተግባራትን መረጃ ማግኘት በጣም ከባድ ነው። ቢገኝም በጣም የተቆራረጠ መረጃ ነው። አንዳንዶቹ የፐርፎርማንስ ቦንድ ያስያዙ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ የውል ጊዜያቸውም ያለፈባቸው ናቸው።

በዚህ ሳቢያም ርምጃ ለመውሰድ እንደገናም ተጠያቂ ለማድረግ ደንበኛው የሚጠበቅበትን ክትትል ካላደረገ ወደ ፍርድ ቤት በሚሄድበት ጊዜ የሚያሸንፈው ኮንትራከተሩ ነው። በዚህም የተነሳ አንዳንዶቹ ወደ ፍርድ ቤትም ሄደው ገና አላለቁም። ግን የፍርድ ሂደቱ የሚያሳየው ኮንትራክተሮች እንደሚያሸንፉ ነው። ይህ የሚመነጨው መረጃ ባለመኖሩ ነው።

ለዚህ መፍትሔ እንዲኖር ባለፈው ዓመት የመረጃ ቋት እንዲኖር ሥራ ጀምረን ነበር። ነገር ግን መንግሥት በአንድ ቦታ ነው የሚለማው ብሎ ስላቆመው የመረጃ ቋት የማልማት ሂደቱ ተቋረጠ። ይሁንና እንደገና የመረጃ ቋት የማልማት ሂደቱ ባለፈው ዓመት ሰባተኛ ወር ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተፈቀደልን።

ሌላው በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል ትልቁ ክፍተት የአቅም ጉዳይ ነው። አንደኛ ሎጂስቲክስ፤ ሁለተኛ በጀት፤ ሶስተኛ የሰው ኃይል ነው። እኛ ጋር ያለው የሰው ኃይል እንደ እኔ ተሾመ የተቀመጠ ካልሆነ በስተቀር አቅም ያላቸው ባለሙያዎች የተሻለ አማራጭ ሲያገኙ እየለቀቁብን ነው። የመልቀቃቸው መንስኤ ሁለት ነው። የመጀመሪያው እንደ ተሽከርካሪ እና መሰል አቅርቦት ችግር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ደሞዝ ነው።

ለምሳሌ ከእኛ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት የወጡ አስራ ሁለት ባለሙያዎች ሌላ መሥሪያ ቤት የተቀጠሩት ከ70 እስከ 80 ሺህ ብር በላይ ነው። ሰሞኑም እንዲሁ ሁለት ባለሙያዎች ከመሥሪያ ቤታችን ለቀዋል። ሌላ መሥሪያ ቤት ሄደው የተቀጠሩት በሁለት መቶ ሺህ ብር ነው። ስለዚህ እኛ ጋር የሚቀረው ተወዳዳሪ ያልሆነና አቅም ክፍተት ያለበት ነው። በርካታ ባለሙያዎች ከለቀቁ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ከገበያ መሳብ ይኖርብናል፤ ከገበያ ለመሳብ ደግሞ የተሻለ ደሞዝ ማቅረብን ይጠይቃል።

አሁን ላይ ከገንዘቡ እና ከሎጂስቲኩም በከፋ የሰው ኃይል ችግር አለብን። ችግሩን ለመቅረፍ ለሠራተኞቻችን በየጊዜው ስልጠና በመስጠት አቅም ከማሳደግ ሥራዎች በተጨማሪ የተለያዩ የአሰራር ሥርዓቶችንም እየዘረጋን ነው። ለምሳሌ ባለሙያው ሄዶ መረጃ ሰብስቦ በሙያው የሚያደርገውን የቀን ተቀን ሃሳብ መለዋወጥን ባሕል ብናደርግ ችግሩን መቅረፍ እንችላለን የሚል ነው። ሁለተኛ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር ተነጋግረን በአዲሱ ፐብሊክ ሪፎርም ጥያቄዎችን ለመመለስ እየሰራን ነው።

ሌላው ያለብን ችግር ደግሞ የአሰራር አቅም ችግር ነው። እኛ ከመጣን በኋላ የተሰሩ የአሰራር ሥርዓቶች አሉ። ለምሳሌ ከሥራ ባሕልና ደረጃ ጋር ብንወስድ ‹‹ኮንክሪት ካስት›› የሚያደርግ ቡድን ምን ያህል በቀን ያመርታል የሚለውን ስታንዳርድ የተሰራው የዛሬ 35 ዓመት ነው። በዚህ ዘመን ትልቁ ፕሮጀክት ጂ+1 ነው። የአሰራር ሥነ ዘዴውም ቢሆን ከ30 ዓመት በፊትና አሁን አንድ አይደለም። አምና እና ዘንድሮ እንኳን አንድ ዓይነት አይደለም። እኛ እስከምንመጣ ድረስ ኢንዱስትሪው የአረጀ የአሰራር ሂደት ሲጠቀም ነበር። ይህ ደግሞ መንግሥትን ይጎዳል። አሁን ላይ ግን ቴክኖሎጂ ስለ ዘመነ አዳዲስ እና ሥራን የሚያቀሉ እንዲሁም ጥራትን የሚጨምሩ ማሽኖች መጥተዋል። ይህ አሰራራችንን ማዘመን እንድንችል አስችሎናል።

አዲስ ዘመን፡- ስልጠና የሰጣችኋቸው ሠራተኞች የሚለቁ ከሆነ ብቁ ባለሙያ ከማፍራት ረገድ ችግር አይኖርም ወይ? እንዴት ነው ማሳካት የምትፈልጉትን እቅድ እውን ማድረግ የሚቻለው?

ኢንጂነር መስፍን፡- እስከዛሬ አሰልጥነናቸው መሥሪያ ቤታችንን የለቀቁ ሠራተኞች የሉም። ለሠራተኞቻችን አጫጭር ስልጠናዎች ነው የምንሰጠው። ስልጠናዎችን በራሳችን እና ከኮንትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር እንሰጣለን። ከኮንትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የምንሰጠው ስልጠና ፕሮፌሽናል ፕሮጀክት ማኔጅመንት ሰርተፍኬሽን ነው። ይህ ሰርተፍኬት ዓለም አቀፍ ነው። ይህን ስልጠና ከወሰዱ ባለሙያዎቻችን አንዱ ብቻ መሥሪያ ቤታችን ለቋል።

ይሁን እንጂ አሁንም ሌሎቹ ትልቅ ደመወዝ ከእኛ ይጠብቃሉ። እነዚህን ባለሙያዎች ቅጥር ከመከልክሉ በፊት ከገበያ የቀጠርናቸው ናቸው። ከእነዚህ ባለሙያዎች አብዛኛዎቹ የተወሰነ ሰርተው በዚያው የጠፉት ሲሆን ግማሾቹ እንደውም አልመጡም። ክሪላንስ ያዞሩትም በኋላ ነው። አንዳንዶቹ ትርፍ ሥራ የሚሰሩ እና በጊዜ የማይገቡ በመሆናቸው ከሥራ አሰናብናቸዋል። በወር ሁለት ሶስት ጊዜም አይገቡም። ሌሎቹ ግን እኛ ገንዘብ እና ጉልብት ያወጣንባቸውና ሥራ የተለቀቁ የሉም። እንደ ሕግ አንድ ሠራተኛ እንደሚለቅ ከሶስት ወር በፊት ቀድሞ ካሳወቀ መከልክል አይቻልም። አሁን ላይ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከ140 በላይ ሠራተኞችን ይፈልጋል። ከ140 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች ክፍት የሥራ ቦታ አለን።

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ በ2017 በጀት ዓመት ምን ለማሳካት አቅዶ ሥራ ጀመረ?

ኢንጂነር መስፍን፡- ከ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አንጻር ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አምስት ዋና ዋና የትኩረት ነጥቦች አሉት። እነዚህን እቅዶች እውን ለማድረግ ከ100 በላይ ተግባራትን እናከናውናለን። ከእነዚህ ውስጥ አምስቱን ብገልጽ፤ አንደኛው የሙስና ግመታዊ ማመላከቻውን ከፍ ማድረግ ነው። ይህ ሲዘጋጅ ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ 96ኛ ነበረች። ባለፈው ዓመት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ‹‹ኮስት ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ›› ባወጣው መረጃ ከ96 ወደ 94 ዝቅ ብሏል። ይህም የሙስና ወንጀል እንደ ሀገር የተወሰነ መሻሻሉን የሚያሳይ ነው። ነገር ግን እንደ ባለስልጣን መሥሪያ ቤት መሰራት የነበረባቸው እና እኛ በሰራናቸው ጥብቅና ተከታታይነት ያላቸው ሥራዎች ሙስናን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንድችል ረድቶናል።

ለምሳሌ በኦንላይን አገልግሎት አንደኛ በመውጣት እውቅና ያገኘነው ከ46 ተቋም መካከል ነው። ነገር ግን እስካሁን በሲስተሙ እኔ እራሴ ቅሬታ አለኝ። ለምሳሌ በኦንላይን ቀጠሮ ተሰጥቶት ከሩቅ ቦታ የመጣ ደንበኛ ከእኛ የሚፈለገውን አገልግሎት ለማግኘት የተወሰነ ነገር ሲቀር መብራት ሊጠፋ ይችላል። ብዙ ሰዓት ጠብቆ አገልግሎቱን ለመጨረስ የተወሰነ ሲቀረው መብራት ከጠፋ እና ሥራው ከተቋረጠ ደንበኛው ይበሳጫል። በ2017 የበጀት ዓመት ይህን ችግር ለመቅረፍ የአቅም የማሳደግ ሥራ ተሰርቷል።

ቴሌ በጀመረው ክላውድ አገልግሎትም ቅሬታ አለን። የአንዱን ሰው ዳታ አንዱ ጋር ይወስዳል። በዚህ ምክንያት ደንበኞቻችን ተከፍተውብናል። የእኛ ዓላማ ቀጠሮ ላይ ሀሜት ስላለ እዚያው አመልክቶ እዚያው የሚስተናገድበትን መንገድ መፍጠር ነው። እንደ ብሔራዊ መታወቂያ እዚያው በአካባቢው የሚወሰድብት፤ ደንበኛው ማደስም ከሆነ እዚያው ታድሶልሃል እንዲባል፤ አዲስም ከሆነ ‹‹አውተንትኬት›› አድርጎ ዶክመንቱን መውሰድ እንዲችል ነው። ይህም በውጭ ሀገር ያሉ ነገር ግን በሀገራችን ኩባንያ ያላቸው ሰዎች ባሉበት ሀገር ሆነው የፈለጉትን መሥራት እንዲችሉ የሚያደርጋቸው ሲሆን ይህም የደንበኛውን እርካታ ከፍ ያደርጋል።

በዚህ ዓመት ያሰብነው አውቶ ማሽኑን ከመጨረሳችን በፊት ዩኒቨርሲቲዎች ስለሚታወቁ ተማሪ እኛ ጋር መጥቶ የተመረቀበትን ዶክመንቱን እናያለን። በኢንጂነሪንግ ትምህርት የሚያስመርቁትን ሰኔቱ ካፀደቀላቸውና ከምርቃቱ በፊት ሲልኩልን ምላሽ እንልክላቸዋለን። ተማሪዎቹ ወደ ተቋሙ መምጣት ሳይጠበቅባቸው ዩኒቨርሲቲው ሰብስቦ ይልክልናል። ከእነ ፖስታው ከዲግሪያቸው ጋር ይሰጣቸዋል። ይህ አሰራር እዚህ ጋር ያለውን ሰልፍ ያስቀራል፡፡

ሌላው ያሰብነው የኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ፓርት የኮንስትራክሽን ሪጉላይታይዜሽን የመረጃ ቋት ሲሆን የሚለማው ከኢንሳ ጋር በመተባበር ነው። አሁን ላይ ውል ገብተን ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን ፕሮጀክቱ የ11 ወር ነው። ይህ ዘጠኝ ሞጁሎች ያሉት ነው። ከዘጠኙ ሞጁሎች ውስጥ አንደኛው የቁጥጥር ነው። የኮምፒሊየንስ ቁጥጥር እና የፕሮጀክት አስተዳደር ቁጥጥር ነው። ይህ የሚሆነው በየቀኑ ከየፕሮጀክቱ መረጃ የሚይዝ ሲሆን በየጊዜው ደግሞ ሪፖርት አድርግልኝ ሲባል ሪፖርት ያደርጋል። ለምሳሌ ሁለት ሺህ ፕሮጀክቶች ቢኖሩ በወሩ መጨረሻ ላይ የሁለት ሺህ ፕሮጀክት አፈጻጸም በየወሩ እያስቀመጠ ይሄዳል፡፡

ድርጅቶች ግብር ላይ የሚያስመዘግብው ዝቅ ያለ ነው። እኛ ጋር የሚያመጣ ደግሞ ከፍተኛ ስለምንፈልግ ከፍ ያለ ያስመዘግባሉ። ይህን እንዲጣራ የምናደርገው ደብዳቤ በመፃፃፍ ነው። መፃፃፉ ደግሞ ዛሬ ይሄዳል፤ የዛሬ ሳምንት ወይ የዛሬ ሁለት ሳምንት ይመጣል። አገልግሎት ፈላጊው ደግሞ ዛሬ ነው እምፈልገው በሚል ቅሬታ እንዲፈጠር ያደርጋል። ከእኛም ጋር ሳያረጋግጡ እንዳለ ወስዶ የመስጠት ሁኔታ ይስተዋላል። ይህን ሲያደርጉ የያዝናቸው አሉ። ከውጭም ደግሞ እስኪ አጣሩልን ብለው አምጥተው የተያዙ አሉ።

አሁን ላይ በግንኙነት ሞጁል ገቢዎች ሚኒስቴር፤ ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ፤ ዩኒቨርስቲዎች ከእኛ መሥሪያ ቤት እና ከንግድ እና ቀጠናዊ ሚኒስቴር ጋር ይተሳሰራሉ። ለምሳሌ መስፍን ካምፓኒ የሚል አንድ ካምፓኒ ቢኖር የዚህን ሁሉ አጣርቶ እውነተኛ የሆነውን ይሰጠናል። ገቢዎች ጋርም ሆነ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ጋር መዋሸት አይችልም። ዝቅ አድርጎ ያስገባ ከሆነ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣንም ጋር ዝቅ አድርጎ ይመዘግባል። ማሽነሪው ምን ዓይነት አቅም አለው የሚለውን ስለተሳሰረ ያንኑ መረጃ ያመጣል።

ሁለተኛ የዚህ ሲስተም ትልቁ ጥቅም የሞባይል መተግበሪያ አለው። ለምሳሌ መዋቅር ሲወድቅ አንድ ሰው ካየ ሪፖርት ማድረግ ይችላል። አሁን ግን ለምሳሌ ሰው ወድቆ ሰው ሞቶ ሪፖርቱ ቶሎ አይመጣም። ከፖሊስ ምርመራ በኋላ፤ ከዜና በኋላ ነው የምንሰማውና ምርመራ የምንጀምረው። አሁን ግን ማንም ሲሰራ እያንዳንዷ ሁነት ሪፖርት ያደርጋሉ።

ለአብነት የሴቶች ክፍያ ፔሮል ላይ የሚፈርሙት እና በእጅ ላይ የሚቀበሉት እኩል አይደለም ይባላል። ይሄን እራሷ የተጎዳችው ሴት በመተግበሪያው ሪፖርት ታደርጋለች። የእነሱ ደህንነት ይጠበቃል። ለእኛ ግን ሪፖርት ይደርሰናል። የሞባይል መተግበሪያው ገጠራማ በሆኑ አካባቢዎች የፕሮጀክት ማናጀሮች በተለይ ኔትዎርክ የሌለባቸው በሞባይል መተግበሪያው ይጠቀማሉ። ችግሮች ይፈታሉ።

የትኛው ፕሮጀክት የፐርፎርማንስ ቦንዱ የሚቀጥለው ወር ይቃጠላል። መታደስ አለበት። ዛሬ ያላደሰ ማን ነው? የሚለውን ሪፖርት ያደርግልናል። አሁን ግን በቁጥጥር ምናልባት የዛሬ አምስት ዓመት ለቁጥጥር ስንሄድ ይሆናል የምናገኘው። ይሄ ደግሞ ከተበላሸ በኋላ ነው። ይሄ እንደ ትልቅ ግራንድ ፕሮጀክት ነው ዘንድሮ የወሰድነው፡፡

ሌላው ደግሞ 2017 ዓ.ም ግራንድ ብለን የምንወስደው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተፈራረምነው ፕሮጀክት አለ። ማሻሻያውን ጨምሮ የኮድ እና እስታንዳርድ አዲስ ጥናት አለው። ለምሳሌ ታሪኩን ስናይ የዛሬ ሰላሳ አምስት ዓመት የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ደረጃ ብቻ ነበር። ከአስር ዓመት በኋላ ወደ ዘጠኝ አደገ። የዛሬ አስር ዓመት አካባቢ ወደ አስራ ሁለት ያደገ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ሰላሳ ልናሳድገው ነው፡፡

ከአሁን በፊት የነበረው የቴሌፎን እና ኤሌክትሪክ ብቻ ነው። ስለዚህ ኤሌክትሪክ ዲዛይን የሚሰራው አካል የ‹‹ኢንቢዩልት ፋይቨር ኔትዎርክ‹‹ አንድ እስታንዳርድ ይመጣል ማለት ነው። ለምሳሌ አሁን እዚህ ቤዝመንት ስልክ አይሰራም። ለምንድን ነው የማይሰራው፤ መንግሥት መንገድ እና ውጪ ላይ አልምቶታል። የግለሰቦች ህንጻ ውስጥ ግን የለም። አሁን የንግድ ባንክ ህንጻ ላይ ከተወሰኑ ፎቆች በላይ ኔትወርክ አይሰራም። ለእራሱ ኢንስቶል ማድረግ አለበት። ትልልቁ ህንፃ በሚወጣበት የህንጻው ባለቤት አልፈልግም ካለ እዛ ህንጻ ላይ የሚከራይ ሰው ኔትዎርክ አይኖረውም ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ‹‹ኢን ቢዩልት የፋይብር ኔትዎርክ›› አንዱ የኮድ አካል ሆኖ ይመጣል። የእሳት አደጋ በፊት ትልልቅ አልነበረም አሁን ግን የሚጠይቅ ነው። G+73 እና 90 ሲሰራ የራሱ ‹‹ፋየር ፋይቲንግ›› ሲስተም ይፈልጋል። ሁለተኛ ደግሞ የራሱ ድሮን ይፈልጋል።

ለምሳሌ እዚህ ቤት ውስጥ እሳት ቢነሳ ‹‹ኢም ቢሊት›› የሆነ ኢንፍራ ስትራክቸር የለውም። የሌለው እኛ አስገዳጅ ስላደረግነው ነው። ውጭ ሀገር እያንዳንዷ ቦታ ላይ ስፕሬን አለች። እሳት ሲነሳ የትም ሳይሄድ ያጠፋዋል። እነዚህ አስገዳጅ ሆነው ይመጣሉ፡፡

በምርመራና መልካም አስተዳደር ቡድን

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You