አርባ ምንጭ፦ የደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎትን በሚፈለገው ልክ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግና ይበልጥ ለማሳደግ የፋይናስ ሥርዓቱን የማጠናከር ሥራ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ የኢትዮጵያ ደም እና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ።
12ኛው የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንኮች ዓመታዊ ጉባዔ “ዘላቂ ፋይናንስ – ለጠንካራ ደምና ሕብረ ህዋስ አገልገሎት” በሚል መሪ ሃሳብ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።
በጉባዔው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ደም እና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አሸናፊ ታዘበው (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የደምና ሕብረ ህዋስ አገልግሎቱ ከፌዴራልና ከክልል መንግሥታት በሚመደብ መደበኛ በጀት እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ በሚመደብ በጀት የሚሰጥ ነው።
ሆኖም ህብረተሰቡ በሚፈልገው ልክ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ለመሰብሰብና ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ከታቀደው ደምና ህብረ ሕዋስ አንጻር በጀቱ በቂ ነው ተብሎ አይታሰብም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በመሆኑም የደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎትን በሚፈለገው ልክ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግና ይበልጥ ለማሳደግ የፋይናንስ ሥርዓቱን የማጠናከር ሥራ በልዩ ትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ዶክተር አሸናፊ የፋይናንስ ሥርዓቱን ለማጠናከር በተግባር ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸው፤ የደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎቱ የሚጠይቀውን ወጪ (የኮስት አናሊስስ) በመሥራት “ወጪው እንዴት ይተካል” ከሚለው የመፍትሄ ምክረ ሃሳብ ጭምር ለሚመለከተው አካል በዚህ ዓመት ውስጥ በማቅረብ የማጸደቅ ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
እርሳቸውም፤ ደም ከተሰበሰበ በኋላ ሂደቶችን አልፎ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ እስኪደርስ ድረስ ባለው ሂደት ያለውን ወጪ ለመሸፈን የሚያስችል ዘዴዎችን በመንደፍ ለሚመለከተው አካል ምክረ ሃሳቡን የምናቀርብ ይሆናል ብለዋል።
የአገልግሎቱን አስፈላጊነትና ጠቃሚነት በስፋት ለአጋርና ለሚመለከታቸው አካላት የማስተዋወቅና የማስገንዘብ ሥራ በስፋት እንደሚከናወን አመላክተው፤ በዚህም ከአጋርና ከሚመለከታቸው አካላት ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ ምንጮችን ወይም እድሎችን ከፍ የማድረግ ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
ዶክተር አሸናፊ፤ ጤና ሚኒስቴር እንዲሁም የክልል ጤና ቢሮዎች ለአገልግሎቱ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው የበጀት፣ የሰው ኃይል አመዳደብና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንዲሠሩ አሳስበው፤ በ2017 ዓ.ም የፋይናንስ አቅምን ከማጠናከር ባሻገር የአገልገሎት ተደራሽነት፣ ጥራትና ተጨማሪ አገልግሎቶችን ለመጨመር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በመላ ሀገሪቱ ያሉትን 50 ደም ባንኮች ወደ 54 ለማሳደግ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመው፤ ቁጥራቸውን ከማሳደግ ባለፈ ደም ባንኮቹ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ በትኩረት ይሠራልም ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነውን የዐይን ባንክ አገልግሎት ቢያንስ ከመዲናዋ ባሻገር በሌላ አንድ ክልል አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በተመሳሳይ ተባብረን እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
በጉባዔው የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሕዝብ እንደራሴዎች እና የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ በህብረተሰቡ ዘንድ ተጽዕኖ ፈጣሪነትና ተሰሚነት ያላቸው የሃይማኖት አባቶች፣ አርቲስቶች አንዲሁም የገዢውና የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላት እየተሳተፉ ይገኛል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም