አዳማ፦ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሁለተኛ ምዕራፍ የማስፋፊያ ግንባታ በ300 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማከናወን ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ገለጸ።
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ቱፋ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በመጀመሪያው ዙር የተከናወነው የኢንዱስትሪ ፓርኩ አካል በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በባለሀብቶች ተይዟል።
ዘንድሮ ግንባታው የሚጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ከ120 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሚያርፍ መሆኑንም ተናግረዋል።
”የፓርኩ ግንባታ በ300 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚከናወን ነው” ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ ለዚህም ከቻይና ሁናን ግዛት የመጡ ባለሀብቶች ግንባታውን ለመጀመር መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ወሰን የማስከበር ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግንባታውን ለመጀመር የዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የፓርኩ ግንባታ ሲጠናቀቅ ትላልቅ ማሽነሪዎች የሚመረቱበትና ሀገሪቷ ለዚህ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከማስቀረት ባለፈ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሁለተኛ ምዕራፍ የፓርኩ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም አመልክተዋል።
በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመጀመሪያ ምዕራፍ የተገነቡ ሼዶች ሙሉ በሙሉ በባለሀብቶች የተያዙ ሲሆን ከ 13ቱ ባለሀብቶች ውስጥ 11 ባለሀብቶች በምርት ላይ እንደሚገኙ ተመላክቷል።
ፓርኩ ባለፈው ዓመት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው ተኪ ምርቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረቡ የተገለጸ ሲሆን፤ በዘንድሮው ዓመት ለውጭ ገበያ ከሚያመርተው በተጨማሪ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ለማምረትና ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም