አዲስ ዘመን ድሮ

አዲስ ዘመን ዛሬም እንደ ቀድሞው ሁሉ ታሪክን ሊያስኮመኩመን ከተፍ ብሏል። የዛሬው እንደ ምን ጊዜውም የድሮውን አቅርቦ የሚያሳይ ቢሆንም ለየት የሚያደርገው ጉዳይ ግን አለ፤ እሱም እንስትዋን የኮንጎ ዘማችን ገድል ይዞ መቅረቡ ነው።

ብዙ ጊዜ ሲነገር እንደምንሰማው በኮንጎም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያ የተሳተፈችባቸው የሀገራትን ሠላም የማስከበር ሥራዎች የወንዶች ተሳትፎና ኢትዮጵያዊ ጀግንነት እንጂ የሴቶቹ የድል ብስራትና የጦር ሜዳ ውሎ ብዙም ሲነገር አይሰማም። ይሁን እንጂ በአስደማሚ ሁኔታ ግዳጃቸውን የፈፀሙ እንስቶች በርካቶች መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም፣ ለዛሬ ግን አንዷን እናስታውስ፡፡

የፀሐይ ግርዶሽን በተመለከተም ለየት ያለ ታሪክን የምናገኝ ሲሆን፣ ለጉዳዩ ይሰጥ የነበረውን ትኩረት ብቻም ሳይሆን በዛን ዘመን ጉዳዩ እነማንን ይመለከት እንደነበርም ያስገነዝባልና የዛሬው “አዲስ ዘመን ድሮ” ለየት ያለ ነው።

ኪራይ ቤት እፈልጋለሁ

ዛፎች ያሉበት ትልቅ ጊቢ ውስጥ ሰፊ ሳሎን ያለው ቤት እፈልጋለሁ።

ስልክ ቁጥር 2920

(አዲስ ዘመን፣ ሐምሌ 12 ቀን 1951 )

ቆራጥዋ ሻምበል አስቴር አያና በኮንጎ የፈፀመችው ሙያ

የኮንጎን ፀጥታ ለማስከበር በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት መልካም ፈቃድ ከተላኩት የጠቅል ብርጌድ ወታደሮች አንድዋ ቆራጥዋ ሻምበል አስቴር አያና ናት። ሻምበል አስቴር አያና እድሜዋ 25 ሲሆን፣ ወደ ኮንጎ የተላከችውም የህክምና ርዳታ እንድታደርግ ነው። ይህች ወጣት ባለፉት ጊዜያቶች ለፈፀመቻቸው አስመስጋኝ ሙያዎች መሪ የሆናትን የነርስነት ትምህርት የተማረችው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሆስፒታል ነው።

ከዚህም በቀር ወደ ጀርመን ሀገር ሄዳ የአዋላጅነት ትምህርት ተምራለች። በዚሁም ትምህርቷ ተመርጣ የቃኘው ሻለቃ ጦር በሩቅ ምሥራቅ የተናጋውን የኮሬን ሠላም ለመመለስ በዘመተ ጊዜ በመቶ አለቅነት ማእረግ ዘምታ ቁስለኞችን በማከምና በማስታመም ግዳጅዋን ፈፅማለች።

ስለዚህም ያገልጋዮቻቸውን ውለታ ከማያስቀሩት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት እጅ የአገልግሎት ሜዳይ ተሸልማለች። ከኮሬ ጦር ግንባር እንንደ ተመለሰችም በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ሆሰፒታል ውስጥ ሁና ኢትዮጵያውያን ወገኖችዋን ባላት የህክምና እውቀት አገልግላለች።

ይህንን በመሳሰለው ቅን አገልግሎት የፈፀመችው ሲስተር አስቴር አያና በግርማዊነታቸው መልካም ፈቃድና ትእዛዝ ወደ ኮንጎ ሬፐብሊክ ከተላከው ጠቅል ብርጌድ ጋር በሻምበልነት ማእረግ ሄዳ ስለነበር ለንጉሠ ነገሥቷ ክብር፣ ለሀገሯ ኩራት የሚሆን ተግባር ፈፅማለች።

ኮንጎ በሚገኙት የተባበሩት መንግሥታት ወታደሮች ላይ የኮንጎ ወታደሮች በፈፀሙት የግፍ ድብደባ ጊዜ ሻምበል አስቴር አያና ተደብዳቢዎችን የተባበሩት መንግሥታት ወታደሮችን ለማዳንና ፀቡን ለማብረድ የተቻላትን ያህል ከደከመች በኋላ የጠቅል ብርጌድ ወታደሮችን ርዳታ ጠርታ አድናቸዋለች፤ ይህም ሙያዋ ዝነኛነትንና ተደናቂነትን ያተረፈላት ከመሆኑም በላይ፤ የኢትዮጵያውያትን ጀግንነት በውጭ ሀገር ለማስመስከር ምሳሌ ሁናለች።

(አዲስ ዘመን፣ ነሀሴ 25 ቀን 1952 )

የፀሐይ ግርዶሽ

ከዚህ ቀደም ወደ ፊት መስከረም 21 ቀን ስለሚደረገው የፀሐይ ሙሉ ግርጃ ከትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር በደረሰን መሠረት አንባቢዎቻችን ይህን ቀን እንዲያውቁት ገልፀን ነበር።

የዚህም የፀሐይ ኤክሊፕስ ጊዜው ከመድረሱ አስቀድሞ ተመልካቾች የሆኑት ሁሉ ሊያደርጉት የሚገባቸውን ጥንቃቄ በመግለፅ የትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ምክር ሰጥቷል።

የፀሐይን ግርጃ የሚመለከቱ ሰዎች ሁሉ ዘለአለማዊ የአይን ጉዳት እንዳይደርስባቸው በጭስ የጠቆረ መስተዋት አማካይነት ለማየት መጠቀም እንደሚችሉና ይህን ባያደርጉ የአይን ጉዳት የሚያገኛቸው መሆኑን አስጠንቅቋል።

በተለይም በአዲስ አበባና በሻሸመኔ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ግርጃውን ለማየት የሚችሉት በዚህ ዘዴ መሆኑንና መቶ በመቶ የሚሆነውን የፀሐይ ግርጃ ፎቶግራፍ ለማንሳት ደግሞ ጥሩ ጥሩ ፎቶግራፍ ማንሻ ያሉዋቸው ሰዎች ሻሸመኔ ድረስ ቢሄዱ አስረጅነት ያለው ፎቶግራፍ ማንሳት የሚችሉ መሆናቸውን ጭምር ገልፇል።

(አዲስ ዘመን፣ መስከረም 15 ቀን 1952 )

የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኦቭዘርቫቷር አባሎች ወደ ሻሸመኔ ሄዱ

ዛሬ መስከረም 21 ቀን 1952 ዓ/ም ከእኩለ ቀን በላይ ስለሚሆነው የፀሐይ ግርጃ ሁኔታው ሙሉ በሙሉ ወደሚታይበት ወደ ሻሸመኔ ከተማ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኦቭዘርቫቷር መሪና የሥራው ተካፋይ ከሆኑት ኢትዮጵያውያን ጋር አስፈላጊውን የምርመራና የፎቶግራፍ ማንሻ መሣሪያዎች ይዘው መስከረም 20 ቀን 1952 ዓ/ም ትናንት ወደ ሻሸመኔ ሄዱ።

(አዲስ ዘመን፣ መስከረም 21 ቀን 1952 )

መግለጫ

የደግን ሰው ሥራ የሚያስታውስ፣ ህሙማንን ከስቃያቸው የሚፈውስ አንድ ሆስፒታል ለማሠራት የአስተዋፅኦ ገንዘብ ከመላው ኢትዮጵያና ከውጭ ሀገር ሳይቀር በብዛት ሲሰበሰብ ይታያል።

ይህም ለስመ ጥሩ መስፍን ልኡል መኮንን አልጋወራሽ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ፣ ለሕዝብ መጠቀሚያ እንዲሆን ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በፈለቀው በጎ ፈቃድ የሚሠራው ሆስፒታል መሆኑ ግልፅ ነው።

በዚህም መሠረት ለመታሰቢያው መሥሪያ የሚሰበሰበው ገንዘብ ከምን እንደደረሰ በየ ሳምንቱ ከመገለፅ አላቋረጠም፤ አሁንም ይህ ከእለት እለት ከፍ እያለ የሚሄደው የርዳታ ገንዘብ እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 1951 ዓ•ም ድረስ 3,194,750.05 (ሶስት ሚሊዮን አንድ መቶ ዘጠና አራት ሺህ ሰባት መቶ ሃምሳ ብር ከዜሮ አምስት ሳንቲም) የደረሰ መሆኑን እናስታውቃለን።

የልዑል መኮንን መታሰቢያ ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት

(አዲስ ዘመን፣ ግንቦት 3 ቀን 1951 )

ግርማ መንግሥቴ

Recommended For You