በሀገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በግብርናና በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ሲታይ የነበረውን የዋጋ ጭማሪ ተከትሎ የኑሮ ውድነቱም ሲባባስ ቆይቷል። ለእዚህ የዋጋ መጨመር በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም፣ የደላሎችና ሕገወጥ ነጋዴዎች የሚፈጽሙት ሕገወጥ ተግባር ግን በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
መንግሥትም ይህ የኑሮ ውድነት በህብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳያሳድር ለማድረግ ገበያ የሚያረጋጉ ርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱ ይታወቃል። ሕገወጥ ግብይትን በመቆጣጠር እንዲሁም አቅርቦት ላይ በመሥራት ገበያውን ለማረጋጋት ከመሞከሩ በተጨማሪ በፍጆታ ምርቶች ላይ ድጎማ በማድረግ በሸማቾች ማህበራት በኩል ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ አድርጓል።
በዚህ ብቻም ሳይወሰን የእሁድ ገበያዎችንም ለእዚህ ዓላማ በማዋል የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም እንደ ዱቄት ያሉት የኢንዱስትሪ ምርቶች ለህብረተሰቡ በየአቅራቢያው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርሱ ለማድረግ ሠርቷል።
በእነዚህ ጥረቶች በተለይ በሸማቾች ማኅበራት በኩል ዘይትና ስኳር እንዲሁም የዳቦ ዱቄት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርሱ ተደርጓል። በየበዓላቱም የዘይትና የመሳሰሉት የፍጆታ ምርቶችን በእነዚህ ማህበራት በኩል በማቅረብ ገበያውን ለማረጋጋት ተሞክሯል።
በሌማት ትሩፋት እና የከተማ ግብርና ሥራዎችም እንዲሁ እንደ እንቁላል፣ ዶሮና ወተትና የወተት ተዋጽኦዎችን በማምረት ለገበያ ለማቅረብ ተሠርቷል፤ እየተሠራም ነው።
በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ መግቢያ በሮች ላይ አምስት የግብርና ምርቶች የግብይት ማእከላትን በመገንባት ህብረተሰቡ ከአምራቾች በቀጥታ የግብርና ምርቶችን የሚገዛበትን ሁኔታ ፈጥሯል። ይህ ሂደት የደላላውን እጅ በመቁረጥ የረዘመውን የገበያ ሰንሰለት በማሳጠር የግብርና ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ህብረተሰቡ ዘንድ እንዲደርሱ እያስቻለ መሆኑ ይገለጻል።
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ወይም ዋጋን ለማረጋጋት እየተሠራባቸው ከሚገኙት መካከል የእሁድ ገበያዎች (ቅዳሜም ጭምር ይካሄዳሉ) ይጠቀሳሉ። በ2014 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ የዋጋ ንረት ለማረጋጋትና ጤናማ የግብይት ሥርዓትን ለመዘርጋት አምራች ህብረት ሥራ ዮኒየኖችን ከአዲስ አበባ ከተማ ሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በማቀናጀት ዋጋ በማረጋጋት ሥራ እንዲሠማሩ የተደረጉት ሳምንታዊዎቹ የእሁድ ገበያዎች፣ በሂደት እየተስፋፉ እንዲመጡ ተደርጓል፤ ቅዳሜንም ጨምሮ አገልግሎት ወደ መስጠት እንዲሸጋገሩ መደረጉ ይታወቃል።
በወቅቱ ማህበረሰቡ እነዚህን ዋጋን ለማረጋጋት እና አማራጭ የፍጆታ ምርቶችን የሚያገኝባቸው ሁኔታዎች በመፈጠራቸው ደስታውን ሲገልጽም ነበር። አጀማመራቸው ጥሩ እንደመሆኑም የህብረተሰቡ አስተያየት ተገቢ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል። የቅዳሜና እሁድ ገበያ የሚካሄድባቸው ቦታዎች በአንድ በኩል እየሰፉ መምጣታቸው በአዎንታዊነት ቢወሰድም፣ ህብረተሰቡ በገበያዎች በስፋት የሚታይበት ሁኔታ ሲታይ ገበያዎቹ ህብረተሰቡን ያማከሉ ናቸው ብሎ ቢወሰድም ችግር አልነበረባቸውም፤ የለባቸውም ግን አይባልም።
በአሁኑ ወቅት የእሁድ ገበያዎች እንደ አጀማመራቸው ሥራቸውን እየሠሩ ነው ወይ ተብሎ ሲጠየቅ ምላሹ አይደለም የሚል ሆኗል። ገበያን በማረጋጋት በኩል ሃላፊነታቸውን እየተወጡ አለመሆናቸው በሰፊው እየተጠቆመ ነው። በዋጋም በምርት ጥራት በኩልም ቅሬታ እየቀረበባቸው ይገኛሉ።
በገበያዎቹ ህብረተሰቡ የሚፈልጋቸው ምርቶች ተለይተው በበቂ ሁኔታ እየቀረቡ ስላለመሆናቸው ቅሬታዎች ይቀርባሉ። በእነዚህ ገበያዎች በብዛት የሚቀርቡት የግብርና ምርቶች ጥሩ ቢሆንም፣ ምርቶቹ በዋጋም በጥራትም አጠያያቂ እየሆኑ የመጡበት ሁኔታ ግን ዓላማቸውን እያሳኩ አለመሆናቸውን ያመለክታል። በገበያው የሚቀርቡት ምርቶች በአብዛኛው ጥራት የጎደላቸው፣ ዋጋቸውም ከሌላው አካባቢ/ በአቅራቢያቸው ከሚገኙ መደብሮች ዋጋ/ እምብዛም ልዩነት የሌለው ነው እየተባለ ይገኛል፤ የሚያቀርቧቸው እንደ ቲማቲም ያሉት ምርቶችም ቢሆኑ በሌላ ቦታ ፈላጊ ያጡ በአብዛኛው ጠባሳ ያለባቸው፣ የሽንኩርት ምርቶችም እንዲሁ ችግር ያለባቸው መሆናቸው ይገለጻል።
ገበያዎቹ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የፍጆታ ምርቶችን በስፋት መያዝ ሲገባቸው የኢንዱስትሪ ምርቶችን በብዛት ይዘው የሚታዩበት ሁኔታም ዓላማቸውን እየሳቱ ናቸው የሚያሰኛቸው ነው።
ገበያዎቹ የምርቶቹን ዋጋ ዝርዝር በሚሸጡባቸው ድንኳኖች ላይ በግልጽ ቦታ፣ በጉልህ ጽፈው በሚታይ ሥፍራ መለጠፍ ሲገባቸው ይህን ባግባቡ አያደርጉም። አንደኛ በጉልህ አይጽፉም፤ ሁለተኛ ማንኛውም ሸማች ሊያይ በሚችልበት ቦታ ላይ አይለጥፉም። ለይስሙላ ያንን ዝርዝር ለጥፈው፣ የሚሸጡት በመደበኛው ገበያ ወይም ከዚያ ብዙም ባልተለየ ዋጋ ነው። በዚህ የተነሳም ህብረተሰቡ የዚህ የዚህ ለምን ከመደበኛው ገበያ አልገዛም ብሎ ትቶ የሚሄድበት ሁነታ አለ እየተባለ ነው።
የእነሱ ጉድ የሚወጣው ባግባቡ የሚሠሩ ተቆጣጣሪዎቻቸው ሲመጡ ብቻ ነው። እነሱ የመጡ ጊዜ በለጠፉት ዋጋ መሠረት ይሸጣሉ። እነሱ ዞር ሲሉ ደግሞ በፈለጉት ዋጋ ይሸጣሉ። ገበያው የልጅነት ጨዋታው የሌባና ፖሊስ አይነት ሆኗል።
ህብረተሰቡም ስለገበያዎቹ በቂ ግንዛቤ ያለው አይመስልም። ድንኳኑ ላይ የተለጠፈውን የዋጋ ዝርዝር የሚያውቁት እጅግ ጥቂት የሚባለው ሸማች ብቻ ነው። በአጋጣሚ ተቆጣጣሪዎች ሲመጡ ዝርዝሩን ካላዩ በስተቀር የማያውቁት ይበረከታሉ። ዋጋውን ቢያውቁትም በዚያ ዋጋ የሚሸጥላቸው ማግኘታቸውም ያጠራጥራል።
ከዚህ መረዳት የሚቻለው ነጋዴዎች የዋጋና ምርት ዝርዝሩን በጉልህ ጽፈው የሚታይ ሥፍራ ላይ እንዲለጥፉ ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑን ነው፤ ይህን በማያደርጉት ላይም አስተማሪ ርምጃ መውሰድም ይገባል።
ህብረተሰቡም በገበያዎቹ ዓላማና በአሠራሩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግም ተገቢ ይመስለኛል። ህብረተሰቡ በገበያው ዋጋ መሠረት ምርቶቹን እንዲገዛ ለማድረግ የቁጥጥር ሥራው ወሳኝ ይሆናል። መንግሥት ለህብረተሰቡ ሲል የፈጠራቸው ገበያዎች የሕገወጦች ምሽግ እንዳይሆን በማድረግ በኩል የገበያው ዋንኛ ተጠቃሚ መሆን የሚገባው ህብረተሰቡ እንደመሆኑ ተባባሪ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።
ህብረተሰቡ ገበያዎቹን እንደሚፈልጋቸው ይታወቃል። ገበያዎቹ ላይ የሚታየው ትርምስም ይህንኑ ይጠቁማል። የእሁድ ገበያ ነጋዴዎች ጥራት የሌለው ምርት ይዘው፣ ከመደበኛው ገበያ ዋጋ ብዙም ልዩነት ሳያደርጉ እየሸጡ ባሉበት ሁኔታም ገበያዎቹ ጭር ብለው አያውቁም። ይህ ሁሉ እየሆነም አዳዲስ ገበያዎች እየተፈጠሩ ናቸው፤ ከስረው የዘጉ የሉም።
ከዚህ መረዳት የሚቻለው ገበያዎቹ እንደሚያስፈልጉ ነው። እነዚህ ገበያዎች መበራከታቸውም ሆነ መቆየታቸው አስላጊነታቸውን ይጠቁማል። ህልውና የሚኖራቸው ግን ህብረተሰቡን ያማከለ ግብይት ሲያካሂዱ ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት። ነጋዴዎቹም ገዥ ማግኘታቸውን እንደ ጤናማ ሥራ መመልከት አይገባቸውም። ገበያው የተፈቀደበትን ዓላማ በሚያሳካ መልኩ ነው መሥራት አለባቸው።
የመንግሥት አካላትም የቁጥጥር ሥራቸውን ማጠናከር አለባቸው። በግብይት ሥፍራው ባስቀመጡት የዋጋ ዝርዝር መሠረት ስለመሸጥ አለመሸጣቸው በተለያዩ መንገዶች ክትትል መደረግ ይኖርበታል፤ በቂ የምርት አቅርቦት ስለመኖሩም እንዲሁ ክትትል የሚደረግበት ሊኖር ይገባል።
በቅዳሜና እሁድ ገበያ ቦታዎቹ ማሊያ ቀይረው የሚጫወቱ እንዳሉም ይገለጻል። ባለ ትላልቅ መደብሮችም በድንኳኖቹ ገብተው ሲሸጡ ማየት ተለምዷል። ይሄም ሌላው ሕገወጥነት ነው። እነዚህ ነጋዴዎች ህብረተሰቡን ከመጉዳት ባሻገርም የእሁድ ገበያዎቹን ነጋዴዎች በሕገወጥ ተግባራቸው አይበክሉም ተብሎ አይታሰብም። በእነዚህ ላይም ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግና ከገበያው ማስወጣት ያስፈልጋል።
ህብረተሰቡም የተቀመጠውን የዋጋ ዝርዝር በማየት በተቀመጠው ዋጋ መሠረት ሲገዛ አይታይም። በዚህ በኩል ህብረተሰቡ በቂ ገንዛቤ እንዲኖረው የተደረገም አይመስልም። ይህ ሁኔታና ነጋዴዎች የሚፈጽሙት ሕገወጥ ተግባር ሲታይ የሚመለከተው የቁጥጥር አካል ዋጋው በግልጽ እንዲታይ ማድረግ እንዲሁም ገበያውን የማረጋጋት ሥራው በትክክል ሥራ ላይ ስለመዋሉ የመቆጣጠር ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው ማለት ያስቸግራል። የእሁድ ገበያው ዓላማውን እንዳይስት መደረግ ይኖርበታል!
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም